በምዕራብ ሸዋ በርካታ የዳንጎቴ ሲሚንቶ ሠራተኞች በታጣቂዎች ታግተው ተወሰዱ

ታጣቂዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በርካታ ቁጥር ያላቸው የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ሠራተኞች በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን አደአ በርጋ ወረዳ በታጣቂው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ቡድን አባላት መታገታቸውን ምንጮች ለቢቢሲ ገለጹ።

ቢቢሲ ከነዋሪዎች እና ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው ምንጮች እንዳረጋገጠው ከ30 ያላሱ የሲሚንቶ ፋብሪካው ሠራተኞች ትናንት ረቡዕ ኅዳር 21/2015 ዓ.ም. ንጋት ላይ በታጣቂ ቡድኑ አባላት ታግተዋል።

የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ሁለት ኃላፊዎችም በሠራተኞቻቸው ላይ ያጋጠመውን ችግር ለቢቢሲ አረጋግጠው፣ የተከሰተውን ሁኔታ በዝርዝር ለማወቅ ማጣራት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ኃላፊዎቹ ክስተቱ ረቡዕ ማለዳ 12፡30 አካባቢ በፋብሪካው አውቶብስ ሲጓዙ በነበሩ ሠራተኞች ላይ ማጋጠሙንና አስካሁን ባላቸው መረጃ 17 ያህል ሠራተኞች የት እንዳሉ እንደማያውቁ ገልጸዋል።

ምንጮች እንዳሉት እገታውን የፈጸመው መንግሥት በሽብርተኝነት የፈረጀው እና በአካባቢው እንደሚንቀሳቀስ የሚነገረው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ወይም መንግሥት ‘ሸኔ’ ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን ነው።

በአካባቢያቸው ባለው የደኅንነት ስጋት ምክንያት ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱ አንድ ነዋሪ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ ሠራተኞቹ የሲሚንቶ ግብዓት ተቆፍሮ ወደሚወጣበት ስፍራ በድርጅቱ የሠራተኞች ማመላለሽ አውቶብስ እየተጓዙ ሳለ ነው በታጣቂ ቡድኑ አባላት የታገቱት።

ዳንጎቴ ሲሚንቶ በአፍሪካ ቁጥር አንድ ባለሃብት በሆኑት ናይጄሪያዊው አሊኮ ዳንጎቴ ባለቤትነት ስር ያለ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ የሲሚንቶ ገበያ ትልቁን ድርሻ ከሚይዙት ፋብሪካው መካከል አንዱ ነው።

ይህ ሠራተኞቹ በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አባላት የታገቱበት ፋብሪካ የሚገኘው ከአዲስ አበባ በስተ ምዕራብ አቅጣጫ 90 ኪሎ ሜትር ያህል ርቆ ነው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

መንግሥት ሸኔ ብሎ በሚጠራው እና ሽብርተኛ ድርጅት ተብሎ በተፈረጀው ታጣቂ ቡድን ታግተው የተወሰዱ ሰዎች ትክክለኛውን ቁጥር ማወቅ ባይቻልም አንድ ጉዳዩን በቅርበት የሚያውቅ ምንጭ የታጋቾች ቁጥር ከ30 እንደማያንስ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ታጣቂ ቡድኑ የያዛቸውን የሲሚንቶ ፋብሪካ ሠራተኞችን ለመልቀቅ በነፍስ ወከፍ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ መጠየቁን ቢቢሲ ያናገራቸው ምንጮች ገልጸዋል።

የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ የሠራተኞቹን እገታንም ሆነ ተጠየቀ ስለተባለው የማስለቀቂያ ገንዘብን በተመለከተ እስካሁን ያለው ነገር የለም።

የታጣቂ ቡድኑ ቃል አቀባይ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡ ተጠይቀው ምላሽ አልሰጡም። ከዚህ ቀደም ታጣቂዎች በስፋት በሚንቀሳቀሱባቸው ስፍራዎች ሰዎችን አግቶ ገንዘብ የሚጠይቁት የእኔ ጦር አባላት አይደሉም ሲል ነበር።

ቡድኑ ይህን ይበል እንጂ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በሚገኙባቸው ምዕራብ ሸዋ እና ሰሜን ሸዋ ዞኖች የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አባላት ተጠያቂ የሚደረጉባቸው ግድያዎች እና እገታዎች በተደጋጋሚ ይሰማሉ። በተጨማሪም የተያዙ ሰዎችን ለማስለቀቅ የገንዘብ ክፍያ እንደሚጠየቅ በስፋት ሲነገር ቆይቷል።

መንግሥት ሸኔ የሚለው እና እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ የሚጠራው ቡድን በስፋት ከሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች መካከል አንዱ በርካታ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች የሚገኙበት ምዕራብ ሸዋ አድአ በርጋ ወረዳ እና ዙሪያው አንዱ ነው።

በተያዘው ዓመት መስከረም 23/2015 ዓ.ም. የታጣቂ ቡድኑ አባላት በሙገር ሲሚንቶ የሠራተኞች ማመላለሻ አውቶብስ ላይ ተኩስ ከፍተው ሁለት ሰዎች መገደላቸውን እና በርካቶችን ማቁሰላቸው መዘገቡ ይታወሳል።

ባለፈው ዓመት ደግሞ የውጭ አገር ዜጎችን ጨምሮ ወደ 30 የሚጠጉ የኢትዮ ሲሚንት ሠራተኞች ከታገቱ ከሳምንታት በኋላ ተለቀዋል።

ረቡዕ ዕለት የተከሰተው ምንድን ነው?

ሰሜ አይጠቀስ ያሉ አንድ የአከባቢው ነዋሪ ሠራተኞቹ “ደንጋይ የሚፈጭ ማሽን ወዳለበት ወደ በረሃማ ስፍራ” በሠራተኞች ማመላለሻ አውቶብስ እየተጓዙ ሳለ ታግተዋል።

እኚህ ነዋሪ እንደሚሉት ከሆነ ታጣቂዎቹ ተሽከርካሪውን ከተቆጣጠሩ በኋላ ከመካከላቸው ሴቶች እና አዛውንቶችን ለይተው በመልቀቅ የተቀሩትን አፍነው ወስደዋል።

ግለሰቡ ጨምረውም ታጣቂዎቹ ከጥቂት ወራት በፊት በተመሳሳይ የሙገር ሲሚንቶ ሠራተኞችን አፍነው ይዘው ማስለቀቂያ ገንዘብ ተቀብለው እንደለቀቁ ለቢቢሲ አስታውሰዋል።

ከዚህ ቀደም ከነበረው ልምድ ታጣቂዎች ለሚያግቷቸው ሰዎች ከ100 ሺህ እስከ 1 ሚሊዮን ብር የማስለቀቂያ ገንዘብ ይጠይቃሉ።

በቅርቡ መንግሥት ከሲሚንቶ ፋብሪካዎች ጋር ውይይት ካደረገ በኋላ የደኅንነት ችግር ለመቅረፍ ዕቅድ እንዳለው ገልጾ የነበረ ቢሆንም አሁንም ድረስ የታጣቂዎች እንቅስቃሴን ተከትሎ ንጹሃን ሰላባ እየሆኑ ነው።

ሰላማዊ ሰዎች በማንነታቸው፣ ለገንዘብ አልያም ደግሞ ከመንግሥት ጋር ተባብራችኋላ በሚል ዒላማ እንደሚደረጉ እና ለጥቃት እንደሚጋለጡ ነዋሪዎች ይናገራሉ።

የመንግሥት ፀጥታ ኃይሎችም ቢሆኑ ከታጣቂዎች ጋር ተባብራችኋል በሚል ሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ነዋሪዎች ጠቅሰዋል።

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የኦሮሚያ ክልል ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ባለሥልጣን ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ታጣቂ ቡድኑ በተለያዩ አካባቢዎች ከሚፈጽመው ጥቃት ባሻገር ሰዎችን በመያዝ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብን ለማስለቀቂያነት እንደሚጠይቁ ገልጸዋል።

ጨምረውም ታጣቂው ቡድን በተለያየ አካባቢ የተበታተነ እና እርስ በእርሱ ግጭት ውስጥ ያለ ቡድን መሆኑን በመግለጽ፣ ታጣቂዎቹ ምንም አይነት “ፖለቲካዊ አጀንዳ የላቸውም” ብለዋል ባለሥልጣኑ።

በተለይ በምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢዎች በስፋት እንደሚንቀሳቀስ የሚነገር የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በሚወስዳቸው እርምጃዎች የተነሳ አካባቢው ሰላም ከራቀው ዓመታት ተቆጥረዋል።

በተለይ ካለፈው ዓመት ወዲህ የቡድኑ እንቅስቃሴ እና የጥቃት አድማስ እየሰፋ በመምጣቱ ጉዳት የሚደርስባቸው ሰዎች እና የሚፈናቀሉ ነዋሪዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል።

አንዳንድ ወገኖች መንግሥት ከትግራይ ኃይሎች ጋር በመነጋገር የሁለት ዓመቱን ጦርነት ለማብቃት የወሰደውን እርምጃ ከዚህም ቡድን ጋር ቢያደርግ የሚል ሃሳብ ቢሰነዝሩም፣ የኦሮሚያ ክልል ባለሥልጣኑ አቶ ኃይሉ አዱኛ ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ መንግሥት ከታጣቂ ቡድኑ ጋር ለንግግር እንደማይቀመጥ ገልጸዋል።