በምሥራቅ ወለጋ በምዕመናን ላይ በተፈጸመ ጥቃት 15 መገደላቸውን መካነ ኢየሱስ ቤ/ክ ገለጸች

የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ ፕሬዝዳትነትቄስ ዶ/ር ዮናስ ይገዙ

የፎቶው ባለመብት, EECMY/FB

የምስሉ መግለጫ, የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ ፕሬዝዳትነትቄስ ዶ/ር ዮናስ ይገዙ መግለጫ በሰጡበት ጊዜ

በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ታጣቂዎች በአምልኮ ላይ በነበሩ ሰዎች ላይ በፈጸሙት ጥቃት 15 ሰዎች መገደላቸውን የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ ገለጸች።

ቤተክርስቲያኗ እንዳለችው ጥቃቱ የተፈጸመው ባለፈው እሁድ ጥቅምት 27/2015 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል በምሥራቅ ወለጋ፣ ሳሲጋ ወረዳ በጋሎ ቀበሌ ውስጥ ባሉት የሙለታ ጌላ መካነ ኢየሱስ ምዕመናን ላይ ነው።

የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ የተፈጸመውን ጥቃት አስመልክታ ባወጣችው መግለጫ ላይ እንዳመለከተችው፣ ጥቃቱ በዕለቱ ለአምልኮ በተሰበሰቡት ምዕመናን ላይ በርካታ ቁጥር ባላቸው ከሌላ አካባቢ በመጡ ታጣቂዎች የተፈጸመ ነው።

ጥቃት አድራሾቹ በሙለታ ጌላ መካነ ኢየሱስ ማኅበረ ምዕመናን ላይ በፈጸሙት በዚህ ጥቃት 15 ሰዎችን ሲገድሉ በርካቶችን ማቁሰላቸውን፣ የሞቾቹን ስም በመጥቀስ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ ባወጣችው መግለጫ ላይ ገልጻለች።

ቤተ ክርስቲያኗ ለጸሎት በተሰበሰቡ ምዕመናን ላይ በምሥራቅ ወለጋ ውስጥ የተፈጸመውን ጭፍጨፋ አጥብቃ ያወገዘች ሲሆን፣ በአካባቢው ያለው የመንግሥት የፀጥታ ኃይል ጥቃቱ ከመፈጸሙ በፊት ለመከላከል እና ከተፈጸመ በኋላም ፈጻሚዎቹን በመያዝ ለሕግ በማቅረብ ረገድ “የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ባለመወጣቱ” የተሰማትን ሐዘን ገልጻለች።

ጨምራም የሕዝብን ደኅንነትን የመጠበቅ ኃላፊነት ያለበት መንግሥት “ሰላማዊ ሰዎች በግፍ ሲጨፈጨፉ ተገቢውን ክትትል አለማድረግ፣ ለክስተቱም ዕውቅና ለመስጠት አለመፈለግ ወይም በቸልታ ማለፍ መንግሥት ለሕዝብ ያለው ኃላፊነትና የተጠያቂነት ግዴታን ከጥያቄ ላይ የሚጥል ነው” በማለት ቤተ ክርስቲያኗ በመግለጫዋ ላይ ቅሬታዋን አስፍራለች።

ይህ ለአስራ አምስት የሙለታ ጌላ ማኅበረ ምዕመናን ሞት እና ለበርካቶች መቁሰል ምክንያት የሆነው ጥቃት “የዜጎች ደኅንነት ዋስትና ምን ያህል አደጋ ላይ እንደሆነ እንድናስብ ያደርገናል” በማለትም፣ ጥቃት ፈጻሚዎቹ እንዲሁም በጥቃቱ ሂደት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተባባሪ የሆኑት ለሕዝብ ይፋ እንዲሆኑና ለሕግ እንዲቀትቡ ቤተ ክርስቲያኗ ጠይቃለች።

በተጨማሪም በአካባቢው ባለው አለመረጋጋት የበርካታ ንጹሃን ዜጎች ሕይወት እየጠፋ መሆኑን የገለጸችው የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ፣ በተለያዩ አካባቢዎች ባለው የፀጥታ ሁኔታ ሰዎች ላይ ጉዳት እየተደረሰ ነው ብላለች።

ከዚሁ ጋር በተያያዘም በቅርቡ በምዕራብ ወለጋ ውስጥ በምትገኘው በመንዲ ከአምልኮ በመመለስ ላይ የነበሩ “የቤተክርስቲያኗ 14 ምዕመናን፣ መሪዎች እና የወንጌል አገልጋዮች” በቅርቡ ለሞት መዳረጋቸውን መግለጫው ጨምሮ አመልክቷል።

በአጠቃላይ በኦሮሚያ ክልል ያለውን የፀጥታ ችግር በሰሜን የአገሪቱ ክፍል እንደተደረገው በሰላማዊ መንገድ በውይይት እንዲፈታ መንግሥት ጥረት እንዲያደርግ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ ባወጣችው መግለጫ ላይ ጥሪ አቅርባለች።

ባለፉት ዓመታት በምዕራብ ኢትዮጵያ በሚገኙ የኦሮሚያ አካባቢዎች ውስጥ በታጣቂዎች በሚፈጸሙ ጥቃቶች እና የመንግሥት ኃይሎች በሚወስዷቸው እርምጃዎች ሳቢያ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸው ሲዘገብ ቆይቷል።

በተጨማሪም በርካቶች ለአካል ጉዳት ከመዳረጋቸው በተጨማሪ በሺዎች የሚቆጠሩት ደግሞ ጥቃቶችን በመሸሽ ከቀያቸው ለመፈናቀል ተዳርገዋል።