በአሜሪካ የዳዊት ራቁት ሐውልት የፈጠረው ውዝግብ የጣሊያን የሥነ ጥበብ ባለሙያዎችን ግራ አጋባ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአሜሪካ የታዋቂው ሰዓሊና ቀራፂ ማይክል አንጀሎ ራቁት ሐውልት የፈጠረውን ውዝግብ ተከትሎ በጣሊያን የሚገኘው የፍሎረንስ ሙዝየም በፍሎሪዳ የሚገኝ ትምህርት ቤት ተማሪዎችን እንዲጎበኙ ጋበዘ።
በፍሎሪዳ የሚገኘው ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህርት ለተማሪዎቿ የታዋቂውን ሰዓሊ ማይክል አንጀሎን ራቁት ሐውልት በማሳየቷ ከሥራ መባረሯንም ተከትሎ ነው ሙዚየሙ መልዕክቱን ያስተላለፈው።
የ6ኛ ክፍል ተማሪዎች ተመልክተውታል የተባለው ሐውልት ‘ዳዊት’ የተሰኘው የማይክል አንጀሎ ዝነኛ የጥበብ ስራው ነው።
ይህ ‘ዳዊት’ የተሰኘው የሐውልት ቅርጽ የወንድ ብልት ተጋልጦ የሚታይበት በመሆኑ ነው ወላጆች ቅሬታ ያቀረቡት።
‘ለልጆቻችን ልቅ ወሲብ (ፖርኖግራፊ) እንዲመለከቱ ሆነዋል’ በሚል ከአንድም ሁለት ሦስት ወላጆች ቅሬታ የቀረበባት ርዕሰ መምህርት መልቀቂያ እንድታስገባ ተገዳለች።
ጋለሪያ ዴል አካዳሚያ የተባለውና የአርቲስቱን ሥዕልና ቅርጾች የያዘው ሙዝየም ዳይሬክተር ሲሲሊ ሆልበርግ ተማሪዎቹ መጥተው እንዲጎበኙ የጋበዙ ሲሆን ርዕሰ መምህርቷ “መሸለም እንጂ መቀጣት የለባትም” ብለዋል።
“ ዳዊት ታሪካዊውን የዘመነ ህዳሴን (ሬናይሰንስ) ወቅት የደረሰበትን የሚያሳይ ቁንጮ የኪነጥበብ ሥራ መሆኑ አያከራክርም። ይህንን ታላቅ የጥበብ ሥራ ሳያነሱ ስለ ህዳሴ ዘመንም መናገርም ምንም ትርጉም አይኖርም” ብለዋል።
ክስተቱ የፍሎረንስ ከተማን ነዋሪዎችን እንዲሁም የሕዳሴ ዘመን ጥበብ ባለሙያዎችን ግራ እንዲጋቡ አድርጓል።
ዳዊት የጣሊያን የህዳሴ ዘመን ድንቅ ሥራ እና የሰብዓዊነት እሴት ምልክት ተደርጎ የሚወሰድ ሲሆን በሙዝየሙም ከአውሮፓውያኑ 1873 ጀምሮ በዕይታ ላይ ነው ያለው።
“የዳዊት ሐውልት ልቅ የወሲብ ምልክት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል ብሎ ማሰቡ መጽሐፍ ቅዱስን ብቻ ሳይሆን የምዕራቡ ዓለም ላይ የተሳሳተ እሳቤ እንዳለ የሚያሳይ ነው። በጣም አስገራሚ ነው” ብለዋል ዳይሬክተሯ።
“መጀመሪያ ዜናውን ሳይ ሐሰተኛ መስሎኝ ነበር። በእውነቱ እንዲህ ዓይነት ነገር ተከስቷል ብዬ ማመን አልችልም። ይህ የማይረባ ሁኔታ ነው” ብለዋል።"
በእርቃን እና በወሲባዊ ይዘቶች ምስሎች መካከል ያለው ልዩነት ሊታይ ይገባል። የዳዊት ሐውልት ምንም ዓይነት ወሲባዊ ይዘት የለውም። አንድ ታዳጊ ወጣት፣ እረኛ ነው፤ በመጽሐፍ ቅዱስ መሰረት ሕዝቡን በታማኝነት ለመከላከል ያለችውን ወንጭፍ ይዞ የወጣ ነው” ሲሉም አስረድተዋል።
የፍሎረንስ ከተማ ከንቲባ ዳሪዮ ናርዴላ በበኩላቸው ተማሪዎቹን እንዲሁም የዳዊትን ምስል ያሳየችውን ርዕሰ መምህርት ከተማይቱን እና የጥበብ ሥራዎቿን እንዲጎበኙ ጋብዘዋል።
“ጥበብን የወሲብ ይዘት አለው ብሎ ማሳሳት አሳፋሪ ነው ። ጥበብ ስልጣኔ ነው የሚያስተምሩትም ክብር ይገባቸዋል” በማለት በትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል።
ርዕሰ መምህርቷ ሆፕ ካራሳኪላ ስለ ህዳሴ ዘመን ሥዕልና ቅርፅ እያስተማረች በነበረበት ወቅት በ17ኛው ክፍለ ዘመን የተቀረጸው የዳዊት ሐውልትን የሚያሳይ ፎቶም ማሳየቷ ነው ውዝግብ ያስነሳው።
ሦስት ወላጆችም ቅሬታቸውን ለቴላሃሲ ትምህርት ቤት ማቅረባቸውን ተከትሎ ነው የትምህርት ቤቱ ቦርድ ሥራዋን በገዛ ፈቃዷ እንድትለቅ ከፍተኛ ጫና ያደረገባት።
በምዕራቡ ዓለም የሥነ ጥበብ ታሪክ ከፍተኛ ስፍራ የሚሰጠው ይህ ሐውልት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጠቀሰው ዳዊት ጎልያድን በወንጭፍ ሊታገል ሲል የሚያሳይ ነው።
ወላጆቹ ቅሬታቸውን ያቀረቡት እርቃን እንደሚታይ ቀድሞ ስላልተነገራቸው መሆኑን የገለጹ ሲሆን፣ አንደኛዋም ወላጅ ‘ልቅ የወሲብ ይዘት’ ያለው ብለውታል።












