“የመብረቁ ደርዳሪ”፡ የእማሆይ ጽጌ ማርያም ገብሩ የአንድ ምዕተ ዓመት ጉዞ

እማሆይ ጽጌ ማሪያም ገብሩ

የፎቶው ባለመብት, Emahoy Tsige Mariyam Music Foundation

በድንቅ የፒያኖ የሙዚቃ ሥራዎቻቸው የሚታወቁት እማሆይ ጽጌማርያም ገብሩ ማረፋቸውን በቅርብ የሚያውቋቸው ሰዎች ገለጹ።

እማሆይ ጽጌማርያም በምንኩስና ወደ መንፈሳዊው ሕይወት ከመግባታቸው በፊት ቤተሰቦቻቸው የውብዳር የሚል ስም ነበር የሰጧቸው።

በ1916 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የተወለዱ እማሆይ ጽጌማርያም ገብሩ በኢትዮጵያ በቫዮሊን እና በፒያኖ ሙዚቃዎችን በማቀናበር በቀዳሚነት የሚጠቀሱ ናቸው።

እማሆይ ጽጌማርያም ትምህርታቸውን ስዊትዘርላንድ ውስጥ የተከታተሉ ሲሆን፣ የሙዚቃ መሳሪያዎቹን መጫወት የተማሩትም እዚያው ነበር።

በአስራዎቹ ዕድሜያቸው መጨረሻ ላይ ወደ አገራቸው ሲመለሱም ወደ መንፈሳዊ ሕይወት በማዘንበል በ21 ዓመታቸው ምንኩስናን በመቀበል ዘመናቸውን የኖረዋል።

የፒያኖ ተጫዋች እና አቀናባሪ የሆኑት እማሆይ ጽጌማርያም የምዕራባውያን እና የኢትዮጵያ ሃይማኖታዊ ዜማዎችን የተማሩ ሲሆን፣ ከኢትዮጵያ ባሻገርም በምዕራቡ ዓለም ሥራዎቻቸው ከፍተኛ አድናቆትን አስገኝቶላቸዋል።

የመጀመሪያ የሥራዎቻቸው ስበስብ የወጣው በ1960ዎች ቢሆንም፣ ዓለም አቀፋዊ ዝናን ያገኙት ደግሞ ብቻቸውን በፒያኖ ያቀናበሯቸው ዜማዎች በኢትዮፒክስ አማካይነት በስፋት መደመጥ ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ ነው።

የፒያኖዋ ንግሥት በመባል የሚታወቁት እማሆይ ጽጌማርያም ገብሩ፣ የሙዚቃ ሥራዎቻቸው በኢትዮጵያውያን እና በሌሎችም ዘንድ ተወዳጅ እና ተደማጭ ለመሆን ችሏል።

ከ30 ዓመታት በፊት ደግሞ እማሆይ ጽጌማርያም ወደ እስራኤል በመሄድ ኢሩሳሌም ውስጥ በገዳማት ውስጥ ሲኖሩ ቆይተው በ99 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት የተለይተዋል።

መታሰቢያ በያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት

የእማሆይ ጽጌማርያም ገብሩ ህልፈትን ተከትሎ በያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ውስጥ "ዝክረ እማሆይ ጽጌማርያም ገብሩ" የተሰኘ የመታሰቢያ መረሃ ግብር በቀጣዩ 15 ቀናት ውስጥ እንደሚዘጋጅ መምህር ዕዝራ አባተ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

በዚህ የመታሰቢያ መረሃ ግብር ላይ "በተቻለ መጠን እማሆይን ጽጌማሪያም የሚያስታውስ መሰናዶ በያሬድ ሙዚቃ ትምህር ቤት ይከናወናል" ብለዋል መምህሩ።

ይህ መሰናዶ "ወጣቶች እንዲያስታውሷቸው" ያለመ እንደሆነ ዕዝራ ተናግረዋል።

አያይዘው እንደገለጹት የመሰናዶው ዋነኛ ይዘት የእማሆይ ጽጌማርያም ሙዚቃዊ አበርክቶ ይሆናል።

"በዋነኛነት ትምህርታዊ አበርክቷቸው ላይ የሚያተኩር ይሆናል። በኢትዮጵያ ሙዚቃ ያላቸውን አስተዋጽኦም ይዳስሳል" ሲሉ አስረድተዋል።

በዚህ የመታሰቢያ መረሃ ግብር ላይ ሙዚቀኞች እንዲሁም መምህራን ይሳተፉበታል ተብሎ እንደሚጠበቅም መምህር ዕዝራ አባተ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

* * *

በክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ "ቅድስቲቷ ከተማ" ተብላ በምትጠራው እየሩሳሌም ኑሯቸውን ካደረጉ ከሶስት አስርተ ዓመታት በላይ ተቆጠሩ። አለማዊ ህይወትን ትተው ምንኩስናን የመረጡት ገና በ 19 ዓመታቸው ነበር፤ የቀድሞዋ የውብዳር፣ እማሆይ ጽጌ ማርያም ገብሩ።

ገና በለጋ እድሜያቸው ከቤተሰቦቻቸው ጠፍተው ወደ ግሸን ማሪያም በመሄድ የምንኩስና ሕይወታቸውን የጀመሩት የያኔዋ የውብዳር፣ ከሁለት ዓመት በኋላ ስማቸው ወደ ጽጌ ማርያም ተቀይሮ እማሆይ ተባሉ።

በአዲስ አበባ ከተማ ታኅሣሥ 02/1916 ዓ.ም መወለዳቸውን በስማቸው የተቋቋመው ፋውንዴሽን ድረ ገጽ ቢያስረዳም እማሆይን በቅርብ የሚያውቁ ሰዎች ግን 99 ዓመታቸውን አክብረው ወደ 100ኛው እየገሰገሱ ነው ይላሉ። የየውብዳር ወላጅ አባት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ የነበሩ ሲሆን ቤተሰባቸውም የከፍተኛው ማኅበረሰብ ክፍል አባል ነበሩ።

እማሆይ እና እህታቸው ስንዱ ገብሩ የዘመናዊ ትምህርት እንዲያገኙ ወደ ስዊዘርላንድ በተላኩ ጊዜ ነበር ከሙዚቃ ጋር የተዋወቁት፤ ገና በስድስት ዓመታቸው።

"ስዊዘርላንድ እያለሁ አንድ ማየት የተሳነው ሰው ያቀረበውን ሙዚቃ ኮንሰርት ታደምኩ። እንዴት እንደሆነ አላውቅም በልቤ እና በአዕምሮዬ ውስጥ ቀረ። ከዚያ ወዲህ የሙዚቃ ምርኮኛ ሆንኩ። ስለዚህ የገና አባት ቫዮሊን እንዲሰጡኝ ጠየቅኩኝ፤ ኋላ ክፍሌ ውስጥ ቫዮሊን አገኘሁ። ገና ስምንት ዓመቴ ነበር" ሲሉ እማሆይ ከአምስት ዓመታት በፊት ከቢቢሲ ራዲዮ ፎር ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረው ነበር።

"ክፍሌ አጠገብ ፒያኖ ነበር። ከዚያም ዝም ብዬ እመታው ጀመር። ሰዎች ሲያልፉ "ምንድነው የምትጫወቺው" ብለው ሲጠይቁኝ "መብረቁን" እላቸው ነበር [ሳቅ]፤ ምን ማለት እንደሆነ አላውቅም።

በስዊዘርላንድ ለአራት ዓመታት ከቆዩ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው በእቴጌ መነን ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ሳሉ በሙሶሎኒ የሚመራው የጣሊያን መንግሥት ኢትዮጵያን ወረረ።

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ዋዜማ ጣሊያን በአምስት ዓመቱ የወረራ ቆይታው መጀመሪያ ላይ የእማሆይን ቤተሰብ በምርኮኛነት ይዞ አሲናራ እና መርካሊያኖ በተሰኙት የጣሊያን ደሴቶች እንዲቆዩ አደረገ።

ከጦርነቱ መገባደድ በኋላ ወደ ሙዚቃ ሕይወታቸው የተመለሱት እማሆይ በካይሮ የቫዮሊን ትምህርታቸውን ተከታትለዋል።

ከቢቢሲ ራዲዮ ፎር ጋር በነበራቸው ቆይታም የካይሮ ቆይታቸው በክላሲካል ሙዚቃ ህይወታቸው ውስጥ ስለነበረው ሚና ያስረዳሉ።

የቤቶቨንን፣ የሞዛርትን እንዲሁም የሽትራውዝን ጨምሮ በርካታ የዓለም የክላሲካል ሙዚቃ ቁንጮዎችን ስራዎች ይጫወቱ እንደነበር እማሆይ ይናገራሉ።

ለሁለት ዓመታት በካይሮ ሙዚቃን ሲማሩም በቀን ውስጥ ለአምስት ሰዓታት ፒያኖ ለአራት ሰዓታት ቫዮሊን ያለማቋረጥ ተጫውተዋል።

እማሆይ ጽጌ ማሪያም ገብሩ

ከአፍካ ቀንድ ወደ ለም አደባባዮች

ከሁለት ዓመታት በፊት የወጣውና ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ሩት ነጋ የምትተውንበት 'ፓሲንግ' የተሰኘው የሆሊውድ ፊልም ላይ ሙዚቃቸው ማጀቢያ ነበር። ከአንድ አመት በፊት የወጣው የፔጆ መኪና ማስታወቂያም በእማሆይ ጽጌማርያም ሙዚቃ ነው የተሠራው።

የፒያኖዋ እመቤት እማሆይ ጽጌ ማሪያም የቅርብ ወዳጅ የሆነችው ማያ ዱኔትዝ ኑሮዋ በእስራኤል ነው። እማሆይን የሚኖሩበት ገዳም ድረስ እየሄደች አሁንም ትጎበኛቸዋለች። እርሷም ፒያኖ መጫወትን ጨምሮ በሌሎች የጥበብ ስራዎቿ ትታወቃለች። ወዳጅነታቸውም አሁን ከአስራ አምስት ዓመታት በላይ ሆኖታል።

ከእማሆይ ሥራዎች ጋር የተዋወቀችው የኢትዮፒከስ ሲዲ መታተምን ተከትሎ እንደሆነ ከቢቢሲ አማርኛ ጋር በስልክ ባደረገችው ቆይታ ትናገራለች።

"ፍራንሲስ ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ትልቅ ውለታ ውሏል። ምስጋናዬን ባለበት ይድረሰው" ስትል ማያ አክብሮቷን ትገልጻለች።

ፈረንሳያዊው ፍራንሲስ ፋልሴቶ እማሆይ ጽጌ ማሪያምን ብቻ ሳይሆን በ1960ዎቹ እና 1970ዎቹ ተወዳጅ የነበሩ የኢትዮጵያ ሙዚቃዎችን ለመላው ዓለም ያስተዋወቀ ሚውዚኮሎጂስት እና አቀናባሪ ነው።

በኢትዮፒክስ ስብስቦች ውስጥ ከተካተቱ አንጋፋ ሙዚቀኞች መካከል የሆኑት እና "የኢትዮ ጃዝ አባት" የሚል የክብር ስምን ያተረፉት ሙላቱ አስታጥቄ፣ እማሆይ ጽጌ ማሪያም የኢትዮጵያን አራቱን ቅኝቶች በአንድ ድርሰት ውስጥ መጠቀማቸው ልዩ ከሚያደርጋቸው ነገሮች አንዱ እንደሆነ ይናገራሉ።

"እማሆይ በእውነት እጅግ የማደንቃቸው እና የማከብራቸው ታላቅ ባለሞያም፤ ታላቅ ሰው ናቸው። ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ትልቅ ሥራ ሰርተዋል ብዬ አምናለሁ። እየሩሳሌም ለኮንሰርት በሄድኩበት ግዜ አግኝቻቸው ተጫውተናል" ሲሉ ሙላቱ ለቢቢሲ አማርኛ ተናግረዋል።

ከእማሆይ በኋላ ሴት ኢትዮጵያዊያን የክላሲካል ሙዚቃ ተጫዋቾች እንዲህ ባለ ግዝፈት እንዳይመጡ ምን ማነቆ ሆነ ስንል የጠየቅናቸው ሙላቱ "ችግሩ ራስን አለማወቅ ነው" ይላሉ።

"ኢትዮጵያ ውስጥ እነዚህ አራቱ ቅኝቶች ገና አልተጠኑም። ይህንን መሠረት ባለማወቃችን ነው ታላላቅ ሰዎችን ማፍራት ያልተቻለው" ሲሉ ሙላቱ የችግሩ መሰረት የሙዚቃ ትምህርት እና ምርምር ያለመጠናከር መሆኑን አጽንኦት ይሰጣሉ።

በእርግጥ ራሳቸው አቶ ሙላቱ የፈጠሩት ኢትዮ ጃዝም በአራቱ የኢትዮጵያ ቅኝቶች ላይ ተመስርቶ የጃዝ ሙዚቃ ውስጥ አዲስ ዘውግ ይዞ መውጣት የቻለ ግዙፍ ጥበብ ውጤት ነው።

አቶ ሙላቱ እማሆይ ቀደም ብለው አራቱን ቅኝቶች ማወቃቸው እና መማራቸው ለፈጠራቸው አግዟል ይላሉ።

"የእማሆይ ጽጌ ማርያም ሥራ ተጠንቶ በየትምህርት ቤቱ እንዲቀመጥ፣ እንዲጠና ማድረግ የግድ አስፈላጊ ነው ብዬ አምናለሁ። የሙዚቃ ትምህርት ካሪኩለም ውስጥ እንዲገባ እና ወጣቶቹ እንዲማሩት ማድረግ ያስፈልጋል" ሲሉም ሙላቱ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በዚህ ረገድ ከሚጠቀሱ የእማሆይ የሙዚቃ ስነዳ ሥራዎች ውስጥ ወደ እስራኤል አገር ከሄዱ ከሁለት ዓመታት በኋላ ሙዚቃዎቻቸውን ለመጻፍ እና ለማሳተም እንድታግዛቸው ለማያ ባደረጉላት ጥሪ መሰረት 12 የሚሆኑ የፒያኖ ቅንብሮቻቸው በኖቴሽን ተከትበው በመጽሐፍ መልክ ታትመዋል።

የራዲዮ ፎሯ ጋዜጠኛ ኬት ሞሌሰን "ሙዚቃዎትን እንዴት ለማሳተም ወሰኑ?" ስትል ጠይቃቸው ነበር።

"ምክንያቱም ሙዚቃዬን ለሌሎች ማጋራት ስለምፈልግ ነዋ! ያለኝን ነገር ማጋራት እፈልጋለሁ። ሌላው ሰው ባይረዳኝ ሙዚቀኞች ይረዱታል" ሲሉ መልሰውላታል።

ማያ እንደምትለውም የእማሆይ ሥራዎች በርካቶችን አነሳስተዋል።

"እኔ የማገኛቸው በተለይም አፍሪካዊያን አርቲስቶች ዘንድ ትልቅ ጀግና ተደርገው ነው የሚወሰዱት። በተለያዩ ምክንያቶች ትልቅ የሕዝብ እውቅና ላይ ደርሰዋል ማለት ባልችልም ነገር ግን የእማሆይ ሙዚቃዎች ድብቅ የአፍሪካ ሙዚቃ ቅርስ ነው ብዬ አስባለሁ።

"እማሆይ ያሳረፉት ጫና ከምናስበው እንዲሁም እስከዛሬ ከተባለው በላይ ነው" ስትልም ማያ ዱኔትዝ ትናገራለች።

እንዲሁም በተለያዩ ቋንቋዎች የተዘጋጁ በርካታ ለሕዝብ ያልቀረቡ ሥራዎች እንዳሏቸው የምትገልጸው ማያ የእማሆይ ሙዚቃ በጥቂት አርቲስቶች ሳይሆን በበርካታ ትውልዶች ላይ ጫና የፈጠረ ነው ትላለች።

የእማሆይ ጽጌ ማሪያም ገብሩ ፒያኖ እየተጫወቱ

የፎቶው ባለመብት, Screen Grab from Labyrinth of Belonging

የእማሆይ ጽጌ ሰብዕና

በጀርመን የሞዛርት ፒያኖ ላይ ተጫውተዋል። ስኬታቸው ቀላል የሚባል አይደለም። በ1967 የታተመውን የመጀመሪያ አልበማቸው ጀምሮ የአልበም ሽያጮቻውን አልበሉም። ይልቁንም ለህጻናት እርዳታ አውለውታል። በግሸን ማሪያም ገዳም ለአስር ዓመታት ያለ ጫማ በባዶ እግራቸው ተጉዘዋል።

"እኔ ታዋቂ መሆን አልፈልግም ነበር። እግዚአብሔርን ስሜ በገነት እንጂ በምድር ላይ ይጻፍ ብዬ ጠይቄው አላውቅም። ግን ሙዚቃውን እንዳላጣው ፈለገ። ሁሉም በእርሱ ሞገስ ነው የሆነው" ሲሉ ለራዲዮ ፎሯ ኬት ነግረዋት ነበር።

ወደ ጎንደር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሙዚቃን ለመማር በሄዱበት፣ ህጻናት ልጆች ከቤተ ክርስቲያን ደጅ ወድቀው እና የእለት እንጀራቸውም ሲለምኑ ከተመለከቱ በኋላ ቀጣይ የሙዚቃ ሕይወታቸው ተቀየረ።

"አኔ እንግዲህ ሌላ ምንም የለኝም። ያለኝ ሙዚቃ ስለሆነ በእርሱ ተጠቅሜ እነሱን ለመርዳት ወሰንኩ" ሲሉ የመጀመሪያው አልበማቸው ውጥን መነሻ መሆኑን ለቢቢሲ ራዲዮ ፎር እ.ኤ.አ. በ2017 ተናግረዋል።

ከዚያም ንጉሡን (ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ) ሙዚቃቸውን ለማሳተም እንዲያግዟቸው ጠይቀው ወደ ጀርመን ተልከው የመጀመሪያ አልበማቸው እ.ኤ.አ. በ1967 በጀርመን ታትሞ ገቢውም በጦርነት ወላጆቻቸውን ላጡ ህጻናት ድጋፍ ዋለ።

"ሙዚቃን የምጫወት ብቸኛዋ መነኩሴ ሳልሆን እቀራለሁ? [ሳቅ]" ሲሉ እማሆይ ከራዲዮ ፎር ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ይነገራሉ።

"አንዳንድ ሰዎች ይቃወሙታል። ነገር ግን ሁሉም ነገር በእግዚአብሔር ፈቃድ ነው የሚሆነው። ይሄ የክላሲካል ሙዚቃ ነው። እግዚአብሔርንም በተለያዩ የሙዚቃ መሳሪያዎች ማወደስ ይቻላል" ሲሉ እማሆይ ለራዲዮ ፎር ተናግረው ነበር።

እማሆይ በፆታ እኩልነት የሚያምኑ ሲሆን ሴቶች ከወንዶች እኩል ናቸው ብለው ያምናሉ። ምንም እንኳን ከልሂቃን ቤተሰብ መገኘታቸው በርካታ በሮችን እንደከፈተላቸው እሙን ቢሆንም እድሎቻቸውን ተጠቅመው በርካታ ስኬቶችን አግኝተዋል፤ እንዲሁም የቅንጦት ሕይወታቸውን ወደ ጎን ብለው ያገኙትን ሁሉ መልሰው ሰጥተዋል።

በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ የመጀመሪያዋ ሴት የአስተዳደር ሠራተኛ እንዲሁም ወደ እየሩሳሌም የደርግ መንግሥትን ሽሽት ከተሰደዱ በኋላ በኢትዮጵያ ገዳም ውስጥም የመጀመሪያዋ ሴት አስተርጓሚ ሆነው ገብተዋል።

እማሆይ ፌሚኒስት ናቸው ወይ ስንል ማያን ጠይቀናታል።

"ይሄን ጥያቄ እንዴት እንደምመልስ አላውቅም። አዎ ፌሚኒስት ይመስሉኛል። ሴቶችን የማብቃት እይታዎች አሏቸው። ሴት ጋዜጠኞችም ሆኑ አርቲስቶች ሲመጡ ሲያበረታቷቸው እና ህልማቸውን ተከትለው እውን እንዲያደርጉ ሲመክሩ አያለሁ።

"ሴቶች በቤት እና በቤተሰብ ውስጥም ይሁን ከዚያ ውጪ ባለው ሰፊ ዓለም ውስጥ እንዲጠነክሩ ያበረታታሉ። ቢያንስ ለእኔ እንደሚሰማኝ ጠንካራ የሆነ ሴቶችን የማብቃት አቀራረብ አላቸው" ስትል ማያ ለቢቢሲ አማርኛ ተናግራለች።

የእማሆይ ጽጌ ማሪያም ገብሩ

የፎቶው ባለመብት, Screen Grab from Labyrinth of Belonging

ማያ ከእማሆይ አሳዛኝ ቅንብሮቻቸውን እንደምትወድ ብሎም ሦስቱን ለይታ እንደምትወዳቸው ትናገራለች።

"በእርግጥ ይሄ አሁን ላይ ያለ እንጂ እንደጊዜው፣ እንደ አየር ሁኔታው እና እንደ ስሜቴ ሊቀያየር ይችላል (ሳቅ)" ትላለች ማያ።

ዘ ጋርዲያንስ ኦፍ ጌትሰማኔ፣ ጎልጎታ እና ጄሩሳሌም አሁን ላይ የምትወዳቸው እና የምታዳምጣቸው የእማሆይ ቅንብሮች ናቸው።

"ዘ ጋርዲያንስ ኦፍ ጌትሰማኔ በሕብረ ቀለማት የተንቆጠቆጠ፣ ኮርድስ እና ፎልስ ሩር ኤግዞቲክ ፍላወር። እያየሁት ቀለሙን የሚቀያይር ቅንብር ነው" ስትል ማያ ትገልጸዋለች።