በሶሪያ የገና ዛፍ መቃጠሉን ተከትሎ ተቃውሞ ተነሳ

ተቃውሞ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ተቃዋሚዎች የሶሪያን ሰንደቅ አላማና መስቀል ይዘው አደባባይ ወጥተዋል

በሶሪያዋ ሐማ ከተማ አቅራቢያ የገና ዛፍ መቃጠሉን ተከትሎ ተቃውሞ ተነሳ።

ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተዘዋወረ ቪድዮ እንደሚያሳየው የፊት ጭምብል ያጠለቁ ታጣቂዎች በሱቃይላቢያህ አደባባይ የገና ዛፍ አቃጥለዋል።

ከተማው በብዛት ክርስቲያኖች የሚኖሩበት ነው።

ፕሬዝዳንት ባሻር አል-አሳድን ከሥልጣን ያስወገደው ዋነኛው ኢስላሚስት ቡድን፣ የገና ዛፉን ያቃጠሉት የውጭ ተዋጊዎች እንደሆኑና በቁጥጥር ሥር እንደዋሉ ገልጿል።

በሺዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች በመላው ሶሪያ አደባባይ ወጥተዋል። አዲሱ ኢስላሚስት መንግሥት የሃይማኖች እኩልነትን እንዲያስጠብቅና ከለላ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

ሶሪያውያን የገና በዓለን ለማክበር በሚዘጋጁበት የዋዜማ ዕለት ሁለት የፊት ጭንብል ያጠለቁ ታጣቂዎች የገና ዛፍ ሲያቃጥሉ የሚያሳየው ቪድዮ ወጥቷል።

አሳድን ከሥልጣን ያስወገደው አማጺ ቡድን ሐያት ታሕሪር አል-ሻም (ኤችቲኤስ) የገና ዛፉ መልሶ በከተማው አደባባይ እንደሚቆም ቃል ገብቷል።

የኤችቲኤስ ቡድን የሃይማኖት መሪ የሆኑትና ይህንን መልዕክት ያስተላለፉት መሪ በእጃቸው የመስቀል ምልክት በማሳየትም ድጋፍ ገልጸዋል። እንዲህ ያለ ድጋፍ ከአክራሪዎች በብዛት አይስተዋልም።

በደማስቆ ካሳ መንደር የሚኖሩ ተቃዋሚዎች በአገሪቱ ያሉ የውጭ ተዋጊዎችን አውግዘዋል።

"ሶሪያ ነጻ ናት። ሶሪያዊ ያልሆኑ አገሪቱን ለቀው ይውጡ" ብለዋል።

በደማስቆ ባብ ቶማ መንደር ተቃዋሚዎች የሶሪያን ሰንደቅ አላማና መስቀል ይዘው አደባባይ ወጥተዋል።

"ለመስቀላችን ነፍሳችንን እንሰዋለን" ሲሉም ተቃዋሚዎቹ ድምጻቸውን አሰምተዋል።

ኤኤፍፒ የዜና ወኪል እንደዘገበው አንድ ተቃዋሚ "በአገራችን ክርስቲያን ሆነን መኖር ካልቻልን የትም መኖር አንችልም ማለት ነው" ብለዋል።

በሶሪያ ኩርዶች፣ አርመናውያን፣ ክርስቲያኖች፣ ድሩዚእ፣ አለዋይት ሺዓዎች እና አረብ ሱኒዎች ይኖራሉ። አብዛኞቹ ነዋሪዎች ሙስሊሞች ናቸው።

አሳድን ከሥልጣን ያስወገደው አማጺ ቡድን እንዴት አገሪቷን እንደሚመራ የሚታይ ይሆናል።

መነሻው ጂሃዲስት ቡድን ሲሆን አሁን ግን ከዚህ በተለየ መንገድ እንደሚሄድ ገልጿል።

የአማጺ ቡድኑ መሪ ደማስቆን ሲይዝ ሶሪያን ለሁሉም ሶሪያውያን ለማድረግ ቃል ገብቷል።

በሃይማኖትና ጎሳ የተጨቆኑ ቡድኖችን መብት ለማስጠበቅ እንደሚሠሩም ገልጸዋል።

አሜሪካ ከቡድኑ መሪ አሕመድ አል-ሻራ ጋር ከተወያየች በኋላ ያለበትን ለሚጠቁም ሰው እሰጣለሁ ብላ የነበረውን 10 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት ሰርዛለች።