የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ምንድን ነው? ዩክሬንስ ልትቀላቀል ትችላለች?

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኃያላን አገራት ወታደራዊ ትብብር ጥምረት የሆነውን የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅትን (ኔቶ) ዩክሬን እንደማትቀላቀል ተናግረዋል።
እአአ በ2008 ኔቶ ዩክሬን ከጊዜ በኋላ ድርጅቱን እንደምትቀላቀል የተናገረ ሲሆን፤ ሩሲያ በ2022 አገሪቱን ከወረረች ወዲህ ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ የአባልነት ሂደቱ እንዲፋጠን ጥሪ ሲያቀርቡ ከርመዋል።
ሩሲያ ዩክሬን ጥምረቱን መቀላቀሏን በፅኑ የምትቃወም ሲሆን፤ የቀድሞው የኔቶ ኃላፊ ዩክሬን ጥምረቱን "ከረጅም ጊዜ በኋላ" መቀላቀል ብትችልም፤ ጦርነቱ ሳይቋጭ ግን የሚታሰብ አይደለም ብለዋል።
ይህ ድርጅት ምንድን ነው? ዩክሬንስ አባል ለመሆን የፈለገችው ለምንድን ነው?
የኔቶ አባል አገራት የትኞቹ ናቸው?
ኔቶ እአአ በ1949 በዋሽንግተን በ12 አገራት የተመሰረተ ጥምረት ነው።
መስራች አገራቱ ቤልጂየም፣ ካናዳ፣ ዴንማርክ፣ ፈረንሳይ፣ አይስላንድ፣ ጣሊያን፣ ሉክሰምበርግ፣ ኔዘርላንድስ፣ ኖርዌይ፣ ፖርቹጋል፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና አሜሪካ ናቸው።
ድርጅቱ ሁለት ይፋዊ ሥራ ቋንቋዎች አሉት፤ እንግሊዘኛ እና ፈረንሳይኛ።
በፈረንሳይኛ ድርጅቱ 'ኦታን' ተብሎ ይጠራል።
በአሁኑ ወቅት በመላው አውሮፓ እና ሰሜን አሜሪካ 32 አባል አገራት አሉት።
አገራቱ የሚጠቁ ከሆኑ እርስ በእርስ ለመረዳዳት ስምምነት አላቸው።
የኔቶ የመጀመሪያው ግብ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የሶቪየት ሕብረትን መስፋፋት መከላከል ነበር።
እአአ በ1991 ሶቪየት ኅብረት ሲትወድቅ በርካታ የምሥራቅ አውሮፓ አገራት ጥምረቱን ተቀላቅዋል።
አልቤኒያ፣ ቡልጋሪያ፣ ሀንጋሪ፣ ፖላንድ፣ ቼክ ሪፐብሊክ፣ ስሎቫኪያ፣ ሮማኒያ፣ ሉቲኒያ፣ ላቲቪያ እና ኢስቶኒያ የጥምረቱ አባል ሆነዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዩክሬን የኔቶ አባል ትሆናለች?
እአአ በ2008 ኔቶ ዩክሬን ወደፊት ድርጅቱን እንደምትቀላቀል ቢናገርም መስከረም 2022 አባልነቷን እንዲያፋጥን ስትጠየቅ ግን ውድቅ አድርጎታል።
በኔቶ ቻርተር አንቀፅ 5 መሠረት አንድ አባል የሚጠቃ ከሆነ ሌሎች አባላት አገሪቱን ለመከላከል ይሰለፋሉ።
ዩክሬን እየተካሄደ ባለው ጦርነት ወቅት ኔቶን ተቀላቅላ ቢሆን ሁሉም የኔቶ አባል አገራት በሩሲያ ላይ ጦርነት ያውጃሉ።
እአአ ሐምሌ 2023 በሉትኒያ መዲና ቪለኒየስ በተረገው የኔቶ ጉባዔ ድርጅቱ ዩክሬን አባል እንድትሆን "አገራት ሲስማሙ እና ቅድመ ሁኔታዎች ሲሟሉ" ግብዣ እንደሚያቀርብ አስታውቋል።
ዩክሬን በአባልነት ሂደቱ ደረጃዎችን አልፋ አባል እንደምትሆንም ተናግሯል።
ይሁን እንጂ በዶናልድ ትራምፕ እና በቭላድሚር ፑቲን መካከል በተደረገው የአላስካው ጉባዔ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ትርዝ በተባለው ማኅበራዊ ትስስር ገፃቸው በሰላም ስምምነቱ አካል "ዩክሬን ኔቶን አትቀላቀልም" ብለዋል።
የዶናልድ ትራምፕ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ አሜሪካ እና አውሮፓውያን ለዩክሬን "ጠንካራ" የደኅንነት ዋስትና የሰላም ስምምነቱ አካል አድርገው እንደሚሰጡ ሩሲያ ተቀብላለች ብለዋል።
ይህ ዋስትና ምን ዓይነት ቅርፅ እንደሚኖረው እስካሁን ግልፅ አይደለም።
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ የአሜሪካን የደኅንነት ዋስትናን "ታሪካዊ" ሲሉ ገልፀውታል።
ሩሲያ በግዛቷ አቅራቢያ ኔቶን የሚያመጣ ነው በሚል የዩክሬንን የኔቶ አባል የመሆን ሀሳብ በተደጋጋሚ እና በጥብቅ ስትቃወም ቆይታለች።

በቅርብ ዓመታት የትኞቹ አገራት ኔቶን ተቀላቀሉ?
ስዊድን ከፊንላንድ ጋር ኔቶን ለመቀላቀል እአአ ሚያዚያ 2022 አመልክታለች።
ፊንላንድ 1,340 ኪ.ሜ የሚሸፍን ድንበር ከሩሲያ ጋር አላት። ሁለቱም አገራት የዩክሬንን ወረራ ተከትሎ እየጨመረ የመጣው የሩሲያ ጠብ አጫሪነት አሳስቧቸው ነበር።
ፊንላንድ እአአ ሚያዚያ 2023 ኔቶን ስትቀላቀል ቱርክ እና ሀንጋሪ የስዊድንን ማመለከቻ ለመቀበል ለበርካታ ወራት አቅማምተዋል።
ቱርክ አገሪቱን ባልንጣዎቿን የኩርድሽ ቡድኖችን አስጠልላለች በሚል ትከሳለች።
ይሁን እንጂ ከቪለኒየሱ ጉባዔ አስቀድሞ የኔቶ ዋና ፀሐፊ ጀንስ ስቶልትንበርግ ስዊድን የቱርክን "ተገቢ የሆነ የደኅንነት ስጋት" በመፍታቷ የቱርክ መንግሥት አባልነቷን ለማፅደቅ ማመልከቻውን ወደ እንደራሴዎች ምክር ቤት ይወስደዋል ብለዋል።
ዋና ፀሐፊው ሀንጋሪም ተመሳሳይ እርምጃ ትወስዳለች ብለዋል።
ስዊድን የአዲስ አባልነት ሂደቱን ካጠናቀቀች በኋላ መጋቢት 2024፣ በይፋ 32ተኛዋ የኔቶ አባል አገር ሆናለች።
5.5 ሚሊዮን ሕዝብ ያላት ፊንላንድ እንደ አነስተኛ የሕዝብ ቁጥሯ ሳይሆን የሰለጠኑ ወታደሮች እና ግዙፍ ኃይል አላት።
በየዓመቱ 21 ሺህ አዲስ ወታደሮችን መልምላ የምታሰለጥነው አገሪቱ፤ 900 ሺህ ተጠባባቂ ወታደሮች ያላት ሲሆን፤ የጦርነት አቅሟ 280 ሺህ ወታደሮች ነው ተብሎ ይገመታል።
የስዊድን ወታደራዊ አቅም ግን በጣም አነስተኛ ሲሆን፤ 57 ሺህ ወታደሮች ብቻ አሏት።
እአአ በ2010 ወታደራዊ ምልመላዋን ካቋረጠች በኋላ በ2018 ዳግም በመመለስ አሁን ላይ በየዓመቱ ስድስት ሺህ ወታደሮችን ትመለምላለች።

የኔቶ አባላት ለዩክሬን ምን ዓይነት መሣሪያዎችን እያስታጠቁ ነው?
አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም ሩሲያ ወደ ኪየቭ ስትገሰግስ ጦርነቱን የቀለበሱ 'ጃቭሊን' እና 'ንላው' የተባሉ ፀረ ታንኮችን ለዩክሬን አቅርበውላታል።
አሜሪካ 31 'አብራምስ' ታንኮችን ሰጥታለች። ዩናይትድ ኪንግደም ደግሞ 14 'ቻሌንጀር 2' ታንኮችን ስትሰጥ፣ ጀርመን እና ሌሎች የኔቶ አገራት በርካታ 'ሊዮፖርድ 2' ታንኮችን አቅርበዋል።
'ስትራይከር' እና 'ብራድሊስ' የተባሉ በርካታ ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎች ወደ ዩክሬን ተልከዋል።
አሜሪካ ለዩክሬን ሰፊ ርቀት የሚያካልሉ ፈንጂዎችንም ልካለች።
ፈንጂዎቹ አወዛጋቢ ሲሆኑ በተለይም ፍንዳታቸው ሰፊ ሽፋን ስላለው ሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት ያስከትላሉ በሚል ይተቻሉ።
አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም በሩሲያ የጦር ግንባር ዒላማዎችን ለመምታት ጥቅም ላይ የዋሉት እንደ 'ሒማርስ' የመሰሉ ሚሳዔሎችንም ለዩክሬን አቅርበዋል።
አሜሪካ ዘመናዊ የዒላማ ስርዓት የተገጠመላቸውን የረጅም ርቀት ሚሳዔሎችንም ሰጥታለች።
እነዚህ ሚሳዔሎች እስከ 300 ኪ.ሜ. ዒላማ መምታት የሚችሉ በመሆናቸው ለዩክሬን ወሳኝ ናቸው።
ዋሽንግተን በመጀመሪያ ጦርነቱን ያባብሳል በሚል ዩክሬን ሚሳዔሎችን እንዳትጠቀም አሻፈረኝ ብላ ነበር።
ይሁን እንጂ ኅዳር 2024 የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ክልከላውን በማንሳት ሚሳዔሎቹ ወደ ሩሲያ ግዛት እንዲተኮሱ ፈቅደዋል።
ዩናይትድ ኪንግደም እና ፈረንሳይ እስከ 250 ኪ.ሜ. የሚወነጨፉ 'ስቶርም ሻዶው' የተባሉ ሚሳዔሎችን ለዩክሬን የሰጡ ሲሆን፤ ኪየቭ እነዚህን ሚሳዔሎች ወደ ሩሲያ ግዛት ተኩሳለች የሚሉ ሪፖርቶች አሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኔቶ አባል አገራት የሩሲያን 'ክሩዝ' ሚሳዔል እና የድሮን ጥቃቶች የሚከላከሉ የአየር መቃወሚያ ስርዓቶችንም እያቀረቡ ነው።
ይህም የዩናይትድ ኪንግደም 'ስታርስትሪክ' ከተባለው የአጭር ርቀት ፀረ አየር መቃወሚያ መሣሪያ ጀምሮ የአሜሪካው 'ፓትሪዮት' የሚሳዔል ስርዓት ድረስ ይሸፍናል።
ባለፈው ዓመት ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ 'ኤፍ-16' ተዋጊ ጀቶችን ከምዕራቡ ዓለም ማግኘታቸውን አስታውቀዋል። ተጨማሪ ተዋጊ ጀቶች እንደሚያስፈልጋቸውም ተናግረዋል።
ቤልጂየም፣ ዴንማርክ፣ ኔዘርላንድስ እና ኖርዌይን ጨምሮ የኔቶ አባል አገራት ከአየር ኃይላቸው ሊያነሷቸው ያሰቧቸውን 85 አሜሪካ ሰራሽ አውሮፕላኖችን እንደሚሰጡም ቃል ገብተዋል።
ነሐሴ 2023 አሜሪካ 'ኤፍ-16' ተዋጊ ጄቶች ወደ ዩክሬን እንዲላኩ ፈቃዷን ሰጥታለች። ከዚህን ጊዜ ጀምሮ የምዕራባዊያን አገራት የዩክሬንን አብራሪዎች ጀቶችን እንዲያበሩ እያሰለጠኑ ነው።
የኔቶ አባላት ወታደሮችን ወደ ዩክሬን መላክም ሆነ የአየር ክልላቸው ላይ የበረራ እግድ አልጣሉም።
የኔቶ አዛዦች የሩሲያን ግስጋሴ ለመቀልበስ አዲስ እቅድ ላይ ተስማምተዋል።
እቅዱ ሩሲያ በሦስት ዞኖች ማለትም በአርቲክ፣ ሰሜን አትላንቲክ እና ማዕከላዊ አውሮፓ ወይም በሜድትራኒያን ክልል ጥቃት ከሰነዘረች የኔቶ ኃይሎች እንዴት እንደሚሰማሩ ይዘረዝራል።
የኔቶ ምላሽ ሰጪ ኃይል (ኤአርኤፍ) "የሚያጋጥም ስጋትን ለመቀልበስ በፍጥነት ለመሰማራት ከፍተኛ ዝግጅት ያለው እና ስልታዊ እንዲሆን ተደርጎ የተደራጀ ነው"።
በአደረጃጀቱ በአጭር ጊዜ (በ10 ቀናት) 100 ሺህ ወታደሮችን ማሰማራት፣ ከ10 እስከ 30 ቀናት 200 ሺህ ወታደሮች ማዘጋጀት እና ከ30 እስከ 180 ቀናት ደግሞ 500 ሺህ ወታሮችን ለውጊያ ማዘጋጀት ይችላል።
የኔቶ አባል አገራት ወታደራዊ ቁሳቁሶቻቸውን እንዲያሻሽሉ፣ ተጨማሪ ተተኳሾችን እንዲያከማቹ እና ከጠቅላላ አገራዊ ምርታቸው ሁለት በመቶውን ለመከላከያ ወጪ እንዲመድቡ ይፈልጋል።
በቅርብ የተደረገ የኔቶ ግመታ ዘጠኝ አባል አገራት በ2024 ሁለት በመቶ በጀት መመደብ የተሳናቸው ሲሆኑ ስፔን ዝቅተኛ በጀት የምትመድብ አገር ሆናለች።
በሰኔ ወር 2025 በሄግ በተካሄደው የኔቶ ጉባዔ 32ቱም አባል አገራት እስከ 2035 ድረስ ከጠቅላላ አገራዊ ምርታቸው አምስት በመቶ ለመከላከያ በጀታቸው ለመመደብ ተስማምተዋል።















