በዋይት ሃውስ ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪን ለመቀበል እየተዘጋጁ ያሉት ትራምፕ ዩክሬን የኔቶ አባል እንደማትሆን ተናገሩ

ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ እና ፕሬዝዳንት ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የዩክሬን ፕሬዝዳንት " ከፈለገ" ከሩሲያ ጋር ሚደረገውን ጦርነት መቋጨት እንደሚችል፤ በሚደረሰው የሰላም ስምምነት አማካኝነት ግን "ዩክሬን ወደ ኔቶ እንደማትገባ" ተናገሩ።

ትራምፕ፤ የዩክሬኑን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘሌንስኪን በዋይት ሃውስ ከመቀበላቸው ከጥቂት ሰዓታት በፊት ባስተላለፉት መልዕክት፤ ሞስኮ ከስምንት ዓመት በፊት እ.አ.አ በ2014 በህገወጥ መንገድ ቆርጣ የወሰደችውን የክሬሚያ የባህር ሰርጥ መሬት "መመለስ አይቻልም" ብለዋል።

ትራምፕ ይህንን የተናገሩት በአላስካ ከሩስያው መሪ ቭላድሚር ፑቲን ጋር ያደረጉትን ስብሰባ ተከትሎ ነው። ይህ ስብሰባ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ሲያቀርቡ የነበሩትን የተኩስ አቁም ጥያቄ በመተው በምትኩ ዘላቂ የሰላም ስምምነት እንዲደረግ ጥሪ እንዲያቀርቡ ያደረገ ነው።

ዜሌንስኪ እሁድ ምሽት ወደ አሜሪካ ከገቡ በኋላ ዩክሬን ውጤታማ የደህንነት ዋስትና እንድታገኝ አጋር ሀገራት በድጋሚ ጥሪ አቅርበዋል።

አንድ የአሜሪካ ልዑክ እሁድ ዕለት እንደተናገሩት ፑቲን ለዩክሬን የኔቶ አይነት የደህንነት ስምምነት ሊኖር እንደሚችል ተስማምተዋል።

የሩሲያ ፕሬዝዳንት ፑቲን፤ ዩክሬን የእነ አሜሪካን ወታደራዊ ጥምረት እንዳትቀላቀል በተከታታይ ሲቃወሙ ቆይተዋል።

ትራምፕ እሁድ ምሽት ትሩዝ ሶሻል በተባለው ማህበራዊ ሚዲያ ባሰፈሩት ፅሁፍ "የዩክሬን ፕሬዝዳንት ዜለንስኪ ከሩሲያ ጋር የሚደረገውን ጦርነት ወዲያውኑ ማቆም ይችላሉ፤ ወይም ደግሞ ውጊያውን መቀጠል ይችላሉ" ብለዋል።

"እንዴት እንደተጀመረ አስታውሱ። ኦባማ (ከ 12 ዓመታት በፊት፣ አንድ ጥይት ሳይተኮስ) የሰጠውን ክሬሚያን መመለስ አይቻልም፤ ዩክሬንም ወደ ኔቶ መግባትም አትችልም። አንዳንድ ነገሮች በጭራሽ አይለወጡም!" ሲሉም አክለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ትራምፕ ጥር ላይ ወደ ስልጣን ከመመለሳቸው በፊት የኔቶ ሃገራት ኪየቭ አባል ለመሆን የጀመረችውን እና "የማይቀለበስ መንገድ" ሲሉ የገለጹትን ሂደት በተመለከተ ስምምነት ላይ ደርሰው ነበር።

የኔቶ ዋና ጸሀፊ ማርክ ሩተ፣ ከዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ኬር ስታርመርን እና የአውሮፓ መሪዎች ጋር በመሆን የዩክሬን የወደፊት እጣ ፈንታ ላይ ለመወያየት ሰኞ በዋሽንግተን ዜሌንስኪን ይቀላቀላሉ።

በተጨማሪም የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን፣ የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ፣ የጀርመን ቻንስለር ፍሪድሪክ ሜርዝ፣ የፊንላንድ ፕሬዚዳንት አሌክሳንደር ስተብ እና የአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ኡርሱላ ቮን ደር ሌየን ይሳተፋሉ።

ትራምፕ ከቆይታ በኋላ ባሰፈሩት ሌላ ጽሁፍ "ነገ በዋይት ሀውስ ትልቅ ቀን ነው። በአንድ ጊዜ ብዙ የአውሮፓ መሪዎች በጭራሽ [ተቀብለን] አናውቅም። እነሱን ማስተናገድ ለእኔ ታላቅ ክብር ነው!" ብለዋል።

ዜሌንስኪ በበኩላቸው በማህበራዊ ሚዲያ ገጻቸው በለጠፉት ጽሁፍ ትራምፕ ላቀረቡላቸው ግብዣ "አመስጋኝ" እንደሆኑ ገልእጸዋል። "ሁላችንም ይህንን ጦርነት በፍጥነት እና በአስተማማኝ ሁኔታ ለማቆም ጠንካራ ፍላጎት አለን" ሲሉም ጽፈዋል።

ከዩክሬን አጋሮች የሚጠበቀውን ውጤታማ የደህንነት ዋስትና አስፈላጊነት ላይ አጽንኦት በመስጠትም "ከዓመታት በፊት እንደነበረው አይደለም... በ1994 ዩክሬን 'የደህንነት ዋስትናዎች' በሚል ተሰጥቷት ነበር ነገር ግን አልሰራም" ሲሉ ፍላጎታቸውን ገልጸዋል።

አክለውም "እርግጥ ነው፤ ክራይሚያ በዚያን ጊዜ መተው አልነበረባትም" ብለዋል። "ዩክሬናውያን ኪየቭን፣ ኦዴሳን ወይም ካርኪቭን ከ2022 በኋላ እንዳልተዉት ሁሉ" ሲሉም አክለዋል።

ዜሌንስኪ የካቲት ላይ በዋይት ሃውስ በተገኙበት ወቅት በጋዜጠኞች ፊት በፕሬዝዳንት ትራምፕ እና በምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ ተዘልፈው ነበር።

ይህንን ተከትሎ ትራምፕ ቀድሞውንም ከፑቲን ጋር በከተደረገው ውይይት የተገለሉት ዜሌንስኪ በስምምነት ነጥቦች ላይ እንዲስማሙ ጫና ሊያደርጉባቸው ይችላል የሚል ስጋት በአውሮፓ ባለስልጣናት ዘንድ እንደተፈጠረ የዲፕሎማቲክ ምንጮች ተናግረዋል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ግን ዜሌንስኪ በሚቀርብላቸው የሰላም ስምምነት እንዲስማሙ በትራምፕ ጫና ሊደረግባቸው እንደሚችል የሚጠቁሙ አስተያየቶች በሙሉ "የሞኝ መገናኛ ብዙሃን ትርክት" ነው በማለት በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር ለሆነው ሲቢኤስ ተናግረዋል።