ኢራን ወሳኙን የነዳጅ መተላለፊያ፣ የሆርሙዝ ሰርጥን ከመዝጋት ቻይና እንድታስቆማት አሜሪካ ጠየቀች

ማርኮ ሩቢዮ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ኢራን የዓለማችን አንድ አምስተኛው የድፍድፍ የነዳጅ ዘይት መተላለፊያ የሆነውን የሆርሙዝ የባሕር ሰርጥ ከመዝጋት ቻይና እንድታስቆማት የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ጥሪ አቀረቡ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት አሜሪካ በኢራን ላይ የፈጸመቸውን ጥቃት ተከትሎ በኢራን እና በኦማን መካከል የሚገኘው የሆርሙዝ ሰርጥ እንዲዘጋ የአገሪቱ ፓርላማ መወሰኑን የኢራን መንግሥታዊ ሚዲያ ፕሬስ ቲቪ መዘገቡን ተከትሎ ነው።

ሆኖም የመጨረሻው ውሳኔ የኢራን ጠቅላይ ብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ነው ተብሏል።

በዚህ ወሳኝ የመተላለፊያ መስመር የነዳጅ አቅርቦት መስተጓጎል ለዓለም ምጣኔ ኃብት ከፍተኛ መዘዝ ያስከትላል የተባለ ሲሆን፣ የዓለም አቀፉን የነዳጅ ዋጋ እንዲያሻቅብም ያደርገዋል።

ቻይና የኢራንን ነዳጅ በመግዛት በዓለም ቀዳሚ ስትሆን ከአገሪቱም ጋር የጠበቀ ግንኙነት አላት።

አሜሪካ በኢራን የኒውክሌር ይዞታዎች ላይ የፈጸመችውን ጥቃት ተከትሎ የነዳጅ ዋጋ ጨምሯል፤ የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ በአምስት ወራት ውስጥ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ አሳይቷል።

"የቻይና መንግሥት በዚህ ጉዳይ ላይ ተጽእኖ እንዲያደርግ አበረታታለሁ። ምክንያቱም እነሱም ቢሆኑ ነዳጅ ለማግኘት በሆርሙዝ ሰርጥ ላይ በእጅጉ ጥገኛ ስለሆኑ" ሲሉ ሩቢዮ ከፎክስ የዜና ወኪል ጋር ባደረጉት ቆይታ ተናግረዋል።

"የባሕር ሰርጡን ከዘጉት ለእነሱም ቢሆን ኢኮኖሚያዊ ራስን ማጥፋት ነው። ይህንን ለመቋቋም አማራጮችን ይዘን እንቀርባለን፤ ነገር ግን ሌሎች አገራትም ይህንኑ መመልከት አለባቸው። ከእኛ በከፋ የሌሎች አገራት ምጣኔ ኃብትን ይጎዳል" ብለዋል።

የምድራችን አንድ አምስተኛው ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት በዚህ 40 ኪሎ ሜትር ብቻ ስፋት ባለው፣ በጣም ጠባብ በሆነው የባሕር ሰርጥ በኩል ነው የሚያልፈው።

በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙ የነዳጅ እና ጋዝ አምራቾች ይህንን ሰርጥ እንደ መተላለፊያ ይጠቀሙበታል።

በባሕር ሰርጡ ላይ የሚከሰት ማንኛውም ዓይነት መስተጓጎል በዓለም አቀፍ ደረጃ የነዳጅ አቅርቦት ላይ ከፍተኛ መዘግየቶችን ሊያስከትል ይችላል፤ ይህም ወዲያውኑ የዋጋ ንረት እንዲፈጠር ያደርጋል።

ሰኞ [ዛሬ] ዕለት የነዳጅ ግብይት ሲጀመር የአንድ በርሜል የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ ወደ 81.40 ዶላር ከፍ ብሏል። ሆኖም ትንሽ ቆይቶ ወደ 78 ዶላር አካባቢ ቢመለስም 1.4 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱ ተዘግቧል።

"አሜሪካ በአሁኑ ወቅት ኢራን ለምታደርገው አጸፋዊ ምላሽ ለመስጠት በጣም ጥሩ አቅም ላይ ትገኛለች። ሆኖም የነዳጅ ዋጋ የሚንር ከሆነ ሁኔታዎች በከፋ ሁኔታ ሊባባሱ ይችላሉ" ሲሉ ኤምስቲ ፋይናንሻል በተሰኘው ተቋም የኃይል ምርምር ኃላፊ ሳውል ካቮኒክ ገልጸዋል።

ቻይና የኢራንን ነዳጅ በመግዛት በዓለም ቀዳሚዋ ስትሆን ባለፈው ወር በቀን የምታስገባው ከ1.8 ሚሊዮን በርሜል መብለጡን የመርከብ ጭነቶችን ክትትል ከሚያደርገው ቮርቴክሳ የተገኘ መረጃ ያሳያል።

ሕንድ፣ ቻይና እና ደቡብ ኮሪያን ጨምሮ ሌሎች ዋና ዋና የእስያ ታላቅ ምጣኔ ኃብት አገራት በባሕር ሰርጡ በሚያልፈው ድፍድፍ ነዳጅ ላይ ጥገኛ ናቸው።