አሜሪካ በኢራን የኒውክሌር ተቋማት ላይ ስለፈጸመችው ጥቃት ምን እናውቃለን?

የፎርዶ የኒውክሌር ተቋም ሳተላይት ምስል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ የጦር አውሮፕላኖች ኢራን ውስጥ የሚገኙ ሦስት የኒውክሌር ተቋማትን በቦምብ መደብደባቸውን አሳውቀዋል።

ይህም በኢራን እና በእስራኤል መካከል እየተካሄደ ያለው ጦርነት በከፍተኛ ደረጃ መባባሱን ያሳያል።

ፕሬዝዳንቱ ለአሜሪካ ሕዝብ ባደረጉት አጭር የቴሌቭዥን ንግግር "አስታውሱ፣ ብዙ ዒላማዎች ቀርተዋል። የዛሬ ምሽቱ ከሁሉም በጣም ከባዱ እና ምናልባትም በጣም አደገኛው ነበር" ብለዋል።

"ሰላም በፍጥነት የማይመጣ ከሆነ ግን ወደ ቀሪዎቹ ዒላማዎች በፍጥነት፣ የሰላ እና በብቃት የተሞላ ጥቃት እንፈጽማለን።"

አሜሪካ ጥቃት ከፈጸመችባቸው የኒውክሌር ተቋማት መካከል ፎርዶ የተባለው የዩራኒየም ማበልፀጊያ አንዱ ነው።

ይህ በተራራማ አካባቢ ከመሬት በታች ተሸሽጎ የሚገኘው የኢራን የኒውክሌር ተቋም አገሪቱ ላላት ከፍተኛ የኒውክሌር ፍላጎት ወሳኝ ነው።

በተቋሙ ላይ የደረሰው የጉዳት መጠን እስካሁን አልታወቀም።

የእስራኤል ባለሥልጣናት እነዚህን ጥቃቶች በማቀድ ከአሜሪካ ጋር "በሙሉ ትብብር" ሲሠሩ እንደነበር ተናግረዋል።

የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር የሆነውን ሲቢኤስ ኒውስ ቴሌቪዥን ያነጋገራቸው የአሜሪካ ባለሥልጣናት እንዳሉት ከሆነ አሜሪካ ኢራንን በዲፕሎማሲያዊ መንገዶች የአየር ጥቃቱ አንደሚፈጸም ቅዳሜ ዕለት አሳውቃለች።

ኢራን በአካባቢው የሚገኙ የአሜሪካ ወታደራዊ ሠፈሮችን በማጥቃት ምላሽ ልትሰጥ ትችላለች።

የአገሪቱ ባለሥልጣናት ማንኛውም የአሜሪካ ጥቃት ቀጠናውን አደጋ ላይ እንደሚጥል እና አጸፋውን እንደሚወስዱ ቀደም ሲል አስጠንቅቀዋል።

እስካሁን ድረስ ስለ ጥቃቱ ምን እናውቃለን?

አሜሪካ ሠራሹ የእስራኤል ኤፍ 35 የጦር ጄት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አሜሪካ ሠራሹ የእስራኤል ኤፍ 35 የጦር ጄት

የእስራኤል እና ኢራን ግጭት እንዴት ተጀመረ?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሰኔ 6/2017 ዓ.ም. ንጋት ላይ እስራኤል በርካታ የኢራን የኒውክሌር እና ወታደራዊ ዒላማዎች ላይ ድንገተኛ ጥቃት ፈፀመች።

ዓላማው የኢራንን የኒውክሌር መርሃ ግብር ማውደም መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የገለፁ ሲሆን፣ ይህም በቅርቡ የኒውክሌር ቦምብ ለማምረት ተቃርባለች ያለችውን የኢራንን ዓላማ ማደናቀፍ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብሯ ለሰላማዊ አገልግሎት እንደሆነ ትናገራለች።

ቴህራን በምላሹ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሮኬቶችን እና ድሮኖችን ወደ እስራኤል አስወንጭፋለች።

ሁለቱ አገራት ከሳምንት በላይ በፈጀው ጦርነት በርካታ ሚሳዔሎች መለዋወጣቸውን ቀጥለዋል።

ትራምፕ ኢራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ መታጠቋን እንደሚቃወሙ ሲናገሩ ቆይተዋል።

ምንም እንኳ እስራኤል ይህንን በይፋ ባትናገርም ወይም ባታስተባብልም የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎች እንዳሏት በሰፊው ይታመናል።

በመጋቢት ወር የአሜሪካ ብሔራዊ መረጃ ዳይሬክተር ቱልሲ ጋባርድ ኢራን የዩራኒየም ክምችቷን ወደ ማይታወቅ ደረጃ ብታሳድግም "የኒውክሌር ጦር መሳሪያ እየገነባች አይደለም" ብለው ነበር።

ትራምፕ በቅርቡ ይህንን መረጃ "ስህተት ነው" ብለዋል።

የእስራኤል እና የኢራን ግጭት በቀጠለበት በዚህ ወቅት ትራምፕ ያለፉት የአሜሪካ አስተዳደሮች በመካከለኛው ምሥራቅ "የማያልቁ ጦርነቶች" ውስጥ ገብተዋል ሲሉ ተችተው ነበር።

አክለውም አሜሪካንን ከሌላ አገራት ግጭቶች ለማስወጣት ቃል ገብተዋል።

እስራኤል በኢራን ላይ ድንገተኛ ጥቃት በፈጸመችበት ወቅት አሜሪካ እና ኢራን የኒውክሌር ድርድር ላይ ነበሩ።

ከሁለት ቀናት በፊት ትራምፕ ኢራን ላይ ጥቃት ከመሰንዘራቸው በፊት ድርድር እንዲደረግ የሁለት ሳምንት ጊዜ እንደሚሰጡ ተናግረው ነበር።

ያ የጊዜ ሰሌዳ ግን ሳይታሰብ በጣም አጥሯል።

ምሥል

አሜሪካ የትኞቹን ተቋማትን ደበደበች? ምን ዓይነት መሣርያስ ተጠቀመች?

አሜሪካ ሦስት የኢራን የኒውክሌር ተቋማትን መምታቱን ተናግራለች። እነዚህም ፎርዶ፣ ናታንዝ እና ኢስፋሃን ናቸው።

ፎርዶ ከዋና ከተማዋ ቴህራን በስተደቡብ በሚገኝ ተራራማ አካባቢ የሚገኝ ከመሬት በታች በጥልቅ ዋሻዎች ውስጥ የተሸሸገ እንደሆነ ይታመናል።

ፎርዶ ከምድር በታች ያለው ጥልቀት እስራኤል ባሏት የጦር መሳሪያዎች ለመድረስ አስቸጋሪ ነው።

ፎርዶን ለማውደም የሚያስችል ጠንካራ እና ትልቅ "ምሽግ ደርማሽ" ቦምብ እንዳላት የሚታመነው ዩናይትድ ስቴትስ ብቻ ናት።

አሜሪካ ያላት ቦምብ ጂቢዩ-57 ማሲቭ ኦርዲናንስ ፔኔትሬተር (ኤምኦፒ) ይባላል።

ክብደቱ 13,000 ኪ.ግ ሲሆን ባለሙያዎች ከመፈንዳቱ በፊት ወደ 18 ሜትር ኮንክሪት ወይም 61 ሜትር መሬት ውስጥ ዘልቆ መግባት ይችላል ይላሉ።

የፎርዶ ዋሻዎች ከመሬት በታች ከ 80 እስከ 90 ሜትር ርቀት ላይ እንደሚገኙ ይታመናል።

ስለዚህም ኤምኦፒ ውጤታማ በሆነ መልኩ ያወድመዋል ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር አይቻልም።

ነገር ግን ተቋሙን ለማውደም ሊቀርብ የሚችለው ብቸኛው ቦምብ ነው።

የአሜሪካ ባለሥልጣናት በጥቃቱ ወቅት ኤምኦፒን ጥቅም ላይ መዋሉን ለሲቢኤስ ያረጋገጡ ሲሆን፣ ለእያንዳንዱ ዒላማ ሁለት ሁለት ቦምቦች ተጠቅመዋል።

ካርታ
የምስሉ መግለጫ, ጥቃት ከተፈጸማባቸው አካባቢዎች ፎርዶ የተባለው የሚገንበት ቦታ

በኢራን ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ምንድን ነው?

የአሜሪካ ጥቃት በኒውክሌር ተቋማቱ ላይ ያደረሰው ጉዳት፣የሰው ሕይወት ስለማለፉ ወይንም ጉዳት የደረሰበት ስለመኖሩ እስካሁን ግልጽ አይደለም።

የኢራን መንግሥት መገናኛ ብዙኃን ምክትል የፖለቲካ ዳይሬክተር ሐሰን አቤዲኒ ኢራን እነዚህን ሦስት የኒውክሌር ጣቢያዎች "አስቀድማ" ለቅቃ መውጣቷን ተናግረዋል።

በብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ ቀርበው ኢራን "ቁሳቁሶቹ ቀደም ብለው ስለወጡ ትልቅ ጉዳት አልደረሰባትም" ብለዋል።

ትራምፕ በቴሌቭዢን ቀርበው ባደረጉት ንግግራቸው "የኒውክሌር ማበልፀጊያ ተቋሞቹ ሙሉ በሙሉ ተደምስሰዋል" ብለዋል።

የቀድሞ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፖለቲካ እና ወታደራዊ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ማርክ ኪምሚት ለቢቢሲ ሲናገሩ ግን የበለጠ ጥንቃቄ ማድረግ መርጠዋል።

"እስከ መጨረሻው ወድሟል ብሎ ለመገመት ምንም መረጃ የለም" ነበር ያሉት።

ኢራን ከእስራኤል ጋር እያካሄደች ባለችው ጦርነት ከ200 በላይ ሰዎች መሞታቸውን እና ከ1,200 በላይ ሰዎች መቁሰላቸውን ገልጻለች።

ይህ በእንዲህ እንዳለ እስራኤል በኢራን ቁልፍ የኒውክሌር ተቋማት ላይ የምትሰነዝረውን ጥቃት ተከትሎ እስራኤል የፀጥታ ጥበቃዋን እያጠናከረች ነው።

እስራኤል በመላ አገሪቱ የሕዝብ የደኅንነት ገደቧን አጠናክራለች ሲል የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት አስታውቋል።

አሜሪካ ኢራንን ከደበደበች በኋላ "በትምህርት እንቅስቃሴዎች፣ ስብሰባዎች እና የሥራ ቦታዎች" ላይ የጣለችውን የደኅንነት ገደብ አጥብቃለች።

በፎርዶ ይገኛሉ ከተባሉ ቦታዎች አንዱ
የምስሉ መግለጫ, በፎርዶ ይገኛሉ ከተባሉ ቦታዎች አንዱ

የኢራን አጸፋ ምላሽ ምን ሊሆን ይችላል?

ኢራን እስካሁን ድረስ እስራኤል በወታደራዊ ተቋማቷ ላይ በፈጸመችው ጥቃት በከፍተኛ ደረጃ ተዳክማለች ሲሉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

እንዲሁም በቀጠናው የነበሯት አጋሮች በሊባኖስ (ሔዝቦላህ)፣ በሶሪያ እና በጋዛ (ሐማስ) በመፈራረሳቸው ኢራን በከፍተኛ ሁኔታ ተዳክማለች።

ኢራን ግን አሁንም ከፍተኛ ጉዳት ማድረስ ትችላለች።

የኢራን ባለሥልጣናት አሜሪካ በሁለቱ አገራት ጦርነት ውስጥ የምትሳተፍ ከሆነ የከፋ ጉዳት እንደሚደርስባት እና ቀጠናው ወደ "ሁለገብ ጦርነት" እንደሚገባ አስጠንቅቀዋል።

በአካባቢው የሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮችንም ለማጥቃት ዝተዋል።

ዩናይትድ ስቴትስ በመካከለኛው ምሥራቅ ቢያንስ 19 ወታደራዊ ሠፈሮች አሏት።

እነዚህም በባህሬን፣ በግብፅ፣ በኢራቅ፣ በዮርዳኖስ፣ በኩዌት፣ በኳታር፣ በሳዑዲ አረቢያ እና በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች የሚገኙ ናቸው።

ለኢራን በጣም ግልፅ ከሆኑት ዒላማዎች መካከል በባህሬን ሚና ሳልማን የሚገኘው የአሜሪካ ባሕር ኃይል 5ኛ ፍሊት ዋና ማዘዣ ነው።

እንዲሁም የፋርስ ባሕረ ሰላጤ ከሕንድ ውቅያኖስ ጋር የሚያገናኘውን እና 30 በመቶ የሚሆነው የዓለም ነዳጅ ዘይት አቅርቦት የሚጓጓዝበትን የሆርሙዝ ሰርጥ በመባል የሚታወቀውን ወሳኝ የመርከብ መስመር ዒላማ ልታደርግ ትችላለች።

እንዲሁም የዓለም ገበያን አለመረጋጋት አደጋ ላይ በሚጥሉ ሌሎች የባሕር መስመሮች ላይ ጥቃት ትፈጽም ይሆናል።

ኢራን አሜሪካን እየረዱ ነው የምትላቸውን የአካባቢውን አገራት ንብረቶች ዒላማ ማድረግ ትችላለች፤ ይህም ጦርነቱ ወደ መላው ቀጣና ሊሸጋገር ይችላል።

የሳተላይት ምሥል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images / Maxar Technologies

የምስሉ መግለጫ, ሌላኛው ዒላማ የተደረገው ናታንዝ

ትራምፕ አሜሪካን ወደ ጦርነት ለማስገባት የኮንግረስ ይሁንታ ያስፈልጋቸዋል?

በአሜሪካ ሕግ ፕሬዝዳንቱ በሌላ አገር ላይ ጦርነትን በይፋ የማወጅ ብቸኛ ሥልጣን የላቸውም።

በኮንግረስ እና በሴኔት ውስጥ የተመረጡ የሕግ አውጪዎች ብቻ ናቸው የሚችሉት።

ነገር ግን ሕጉ ፕሬዝዳንቱ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ መሆናቸውንም ይገልጻል። ይህም ማለት የአሜሪካ ወታደሮችን ማሰማራት እና ያለ መደበኛ የጦርነት አዋጅ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ይችላል ማለት ነው።

ለምሳሌ ትራምፕ በአውሮፓውያኑ 2017 በሶሪያ በአሳድ መንግሥት ላይ የአየር ድብደባ ለማካሄድ ለመወሰን የኮንግረሱ ይሁንታ አላስፈለጋቸውም።

በምትኩ ትራምፕ የብሔራዊ ደኅንነት እና ሰብዓዊ ምክንያቶችን በመጥቀስ ተንቀሳቅሰዋል።

የሕግ አውጪዎች ትራምፕ ኢራን ላይ ድብደባ እንዲፈጸም ለማዘዝ ያላቸውን አቅም ለመገደብ ጉዳዩን ወደ ኮንግረስ እንዲሄድ ሲገፉ ቆይተዋል።