የባይቶና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር አቶ ክብሮም በርኸ መታሰራቸው ተነገረ

አቶ ክብሮም በርኸ

የፎቶው ባለመብት, kibrom/fb

የምስሉ መግለጫ, አቶ ክብሮም በርሀ

የብሔራዊ ባይቶ አባይ ትግራይ ወይም ባይቶና የሚባለው የፖለቲካ ፓርቲ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ የሆኑት አቶ ክብሮም በርኸ አዲስ አበባ ውስጥ በፀጥታ ኃይሎች መታሰራቸው ተነገረ።

በትግራይ ከሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆነው የባይቶና ከፍተኛ አመራር አንዱ የሆኑት አቶ ክብሮም በቅርቡ “ምጽአት” የሚል ርዕስ ያለው በትግራዩ ጦርነት ላይ የሚያጠነጥን መጽሐፍ ለንባብ አቅርበዋል።

አቶ ክብሮም እሑድ ምሽት አዲስ አበባ ውስጥ በፀጥታ ኃይሎች መያዛቸውን ለቢቢሲ የተናገሩት የፓርቲው የቁጥጥር ኮሚሽን ኃላፊ የሆኑት አቶ ዮሴፍ ኃይለሥላሴ ናቸው።

ምሽት ከአንድ ሰዓት እስከ ሁለት ሰዓት ባለው ጊዜ ሲቪል የለበሱ ሰዎች በቅድሚያ የአቶ ክብሮም ባለቤትን መያዛቸውን የተናገሩት አቶ ዮሴፍ “ባለቤትሽን አምጪ ብለው ጠይቀዋት፣ ከዚያ በኋላ እርሱ ሲሄድ በቁጥጥር ስር አዋሉት” ብለዋል።

ጦርነቱ በተስፋፋበትና የትግራይ ኃይሎች ወደ አፋርና አማራ ክልሎች በገቡበት ወቅት የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎ፣ የባይቶና ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ ክብሮም ተይዘው በአፋር ክልል ውስጥ ለወራት በእስር ላይ ቆይተው እንደነበር ተነግሯል።

አቶ ክብሮም በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከመዋላቸው በፊት ስልክ በመወደል ባለቤታቸው መያዛቸውንና እሳቸውም በፖሊስ እንደሚፈለጉ እንደተነገሯቸው የጠቀሱት አቶ ዮሴፍ፣ አቶ ክብሮም በአሁኑ ጊዜ በቃሊቲ ክፍለ ከተማ በሚገኝ እስር ቤት እንዳሉም ጨምረው ገልጸዋል።

የአቶ ክብሮም ባለቤት እሳቸው በቁጥጥር ሥር ሲውሉ መለቀቃቸውን የተናገሩት አቶ ዮሴፍ፣ የባይቶና የውጭ ጉዳይ ኃላፊው አቶ ክብሮም በርኸ ለምን እንደታሰሩ የሚያውቁት ነገር እንደሌለና ፍርድ ቤትም አለመቅረባቸውን አመልክተዋል።

የአቶ ክብሮም እስርን በተመለከተ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ቢቢሲ ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ስልክ በመደወል ያደረገው ተደጋጋሚ ሙከራ ለጊዜው አልተሳካለትም።

ከቅርብ ወራት ወዲህ መንግሥት ሕግ ማስከበር ባለው ዘመቻ በአዲስ አበባ፣ በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች ውስጥ ጋዜጠኞችን ጨምሮ በርካታ ሰዎች በፀጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወሳል።