በአሶሳ ከተማ የምሽት የሰዓት እላፊ ገደብ ተጣለ

የአሶሳ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ቡሽራ አልቀሪብ

የፎቶው ባለመብት, Benishangul Gumuz Mass Media Agency

የምስሉ መግለጫ, የአሶሳ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ቡሽራ አልቀሪብ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ዋና ከተማ በአሶሳ ላይ የሰዓት እላፊ ገደብ መጣሉን የአሶሳ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ።

በክልሉ መዲና የተጣለው የሰዓት እላፊ ገደብ ከሐምሌ 01/2014 ዓ.ም. ጀምሮ ተፈጻሚ እንደሚሆን የከተማው ፖሊስ መምሪያ አስታውቋል።

የክልሉ ፖሊስ ረዳት ኮሚሽነር ቡሽራ አልቀሪብ ለክልሉ መገናኛ ብዙኃን እንደገለጹት ሰዓት እላፊውን ተግባራዊ ለማድረግ የተለያዩ ገደቦች ተጥለዋል።

በሰዓት እላፊው ገደብ መሠረት ተሸከርካሪዎች ከምሽቱ 2 ሰዓት እስከ ንጋት 12 ሰዓት እንዲሁም እግረኞች ከምሽት 3 ሰዓት እስከ ንጋት 12 ሰዓት ድረስ በከተማዋ መንቀሳቀስ አይችሉም ተብሏል።

የክልሉ የፀጥታ ኃይል አሁን የተጣለው የሰዓት እላፊ ገደብ አስፈላጊ የሆነበትን ምክንያት እንዲሁም አስከ መቼ ድረስ ተግባራዊ እንደሚሆን የሰጠው ምክንያት የለም።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከቀናት በፊት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሰጡት ማብራሪያ ላይ፤ በቅርቡ በአሶሳ ከተማ ታቅዶ የነበረ የሽብር ጥቃት መክሸፉን መናገራቸው ይታወሳል።

የሰዓት እላፊው ገደብ የሰዎችና የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴን የሚያግድ ሲሆን፣ ለአስፈላጊ እንቅስቃሴዎች ከፀጥታ ኃይሉ ፈቃድ መግኘት እንደሚገባ አመልክቷል።

በአሶሳ ከተማ በተጣለው የሰዓት እላፊ ገደብ መሠረት፤ ከምሽቱ 2 ሰዓት እስከ ንጋት 12 ሰዓት ድረስ ከአምቡላንስ እና ከመንግሥት ፀጥታ አስከባሪዎች ውጪ ተሸከርካሪዎች መንቀሳቀስ አይችሉም ተብሏል።

ከተሸከርካሪዎች በተጨማሪ የሰዓት እላፊ ገደብ በተጣለበት ሰዓት ሆቴሎች፣ መጠጥ ቤቶች እና ማናቸውም የንግድ ተቋማት አገልግሎት መስጠት አይችሉም።

እግረኞች ደግሞ ከምሽቱ 3 ሰዓት እስከ ንጋቱ 12 ሰዓት ድረስ መንቀሳቀስ እንደማይችሉ የአሶሳ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ቡሽራ ገልጸዋል።

የእንቅስቀሴ ገደቡ ተጥሎ በሚገኝበት ወቅት ድንገተኛ የሆኑ ማኅበራዊ ችግሮች ካጋጠሙ፤ ነዋሪው በአቅራቢያው ከሚገኙ የመንግሥት ጸጥታ አካላት ፍቃድ ወስዶ መንቀሳቀስ እንደሚቻልም ምክትል ኮሚሽነሩ አስረድተዋል።

ኅብረተሰቡ አጠራጣሪ ነገሮች ሲያጋጥሙት ለፀጥታ ኃይሎች በመጠቆም ተባባሪ እንዲሆንም ጥሪ ቀርቧል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባለፉት ዓመታት ታጣቂዎች በሚያደርሱት ጥቃት እና የመንግሥት ፀጥታ ኃይሎች በሚወስዷቸው እርምጃዎች በርካታ ሰዎች ተገድለዋል፤ ከቀያቸውም ተፈናቅለዋል።

ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ እየገነባች ያለችው ግዙፉ የሕዳሴ ግድብ በሚገኝበት ክልል ለሚከሰተው ተደጋጋሚ ጥቃትና አለመረጋጋት መንግሥት የጉሙዝ ታጣቂዎችን በዋናነት ተጠያቂ ሲያደርግ ቆይቷል።

ከጥቂት ሳምንታት በፊት ደግሞ በጎረቤት ክልል ከተማ ጋምቤላ፤ መንግሥት በአሸባሪነት የፈረጀው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እና የጋምቤላ ነጻነት ግንባር በጋራ በፈጸሙት ጥቃት የጋምቤላ ከተማን በከፊል ተቆጣጥረው ነበር።