ናይጄሪያ በታጣቂዎች እገዛ ከእስር ያመለጡትን ለመያዝ የአፋልጉኝ ማስታወቂያ አወጣች

የናይጄሪያ መንግሥት በታጣቂዎች እገዛ ከእስር ቤት ያመለጡ እስረኞች መልሶ ለመያዝ የአፋልጉኝ ማስታወቂያ አወጣ።
የናይጄሪያ መንግሥት በመዲናዋ አቡጃ ከሚገኘው እስር ቤት ያመለጡ የ69 እስረኞችን ምስል እና ስም አትሞ ለሕዝብ ይፋ አድርጓል።
ባለፈው ማክሰኞ ሰኔ 28/2014 ዓ.ም. ታጣቂዎች ከጄ የተባለን እስር ቤትን ሰብረው በመግባት ከ800 በላይ እስርኞችን አስመልጠው ነበር።
የአገሪቱ መንግሥት ከ800ዎቹ መካከል ግማሽ ያህሉን መልሶ መያዙያን ያስታወቀ ሲሆን፣ እስካሁን ካልተያዙት መካከል የ69ኙ እስረኞች ጉዳይ አሳስቦኛል ብሏል።
የናይጄሪያ ማረሚያ ቤት አስተዳደር እነዚህ 69 ግለሰቦች ከጂሃዲስት ቡድኑ ቦኮ ሃራም እና ከሌሎች በሽብር ተግባር ከሚሳተፉ ቡድኖች ጋር ግንኙነት ያላቸው ግለሰቦች ናቸው ብሏል።
ሕዝቡ እነዚህን ሰዎች መልሶ ለመያዘ የሚረዳ መረጃ ካላው ለፀጥታ አካላት እንዲያስታውቅ አሳስቧል።
ኢስላሚክ ስቴት ማክሰኞች ዕለት በአቡጃ በሚገኘው ማረሚያ ቤት ላይ ለተፈጸመው ጥቃት ኃላፊነቱን ወስዷል።
ታጣቂ ቡድኖች በማረሚያ ቤቱ ላይ ጥቃት ሲፈጽሙ የቡድን አጋሮቻቸው የሚገኙበትን የእስር ቤት ክፍሎች እንዴት በትክክል መለየት ቻሉ የሚለው ጥያቄ በርካቶች እንዲያነሱ አድርጓል።
በዚህ ጥቃት በማረሚያ ቤቱ ላይ ከፍተኛ ውድመት ያጋጠመ ሲሆን ቢያንስ 4 እስረኞች፣ አንድ የእስር ቤት ጠባቂ እና በርካታ የታጣቂ ቡድኑ አባላት ተገድለዋል።
ባለፉት ዓመታት በናይጄሪያ በእስር ቤቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃት ተበራክቶ ቀጥሏል።
እስካሁን በማረሚያ ቤቶች ላይ በሚፈጸሙ ጥቃቶች ከ5ሺህ የማያንሱ እስረኞች ማምለጥ እንደቻሉ ይነገራል።
ጥቃቱ በተፈጸመበት ወቅት በርካታ ቁጥር ያላቸው ተጠርጣሪ ታጣቂዎች እና ፖለቲከኞችን ጨምሮ ከፍተኛ ወንጀል ፈጽመዋል የሚባሉ ግለሰቦች በእስር ቤቱ ውስጥ ነበሩ።
ጥቃቱ ሲፈጸም በእስር ቤቱ ውስጥ 1 ሺህ የሚሆኑ እስረኞች እንደነበሩ ባለሥልጣናት አመልክተዋል። ጥቃቱን ተከትሎ ሁሉም በሚባል ደረጃ ከአስር ቤቱ አምልጠው የነበረ ቢሆንም 443ቱ መልሰው ተይዘዋል።
የናይጄሪያ የመከላከያ ሚኒስትር ባሺር ማጋሺ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፣ በአስር ላይ የነበሩ 64 የቦኮ ሃራም ቡድን ታጣቂዎች ማምለጣቸውን “አንዳቸውም በእስር ቤቱ ውስጥ የሉም፣ አምልጠዋል” ብለው ነበር።
የናይጄሪያው ፕሬዝዳንት ሙሐማዱ ቡሃሪ የአገሪቱ የደኅንነት ተቋማት የመረጃ ሥርዓት ደካማነትን በማንሳት ለጥቃቱ መከሰት ምክንያት ነው ሲሉ ወቅሰዋል።
ፐሬዝዳንቱ ጨምረውም ለእስር ቤቱ ይደረግ በነበረው ጥበቃ ላይ ጥያቄ አንስተው፣ ስለተፈጸመው ጥቃት “አጠቃላይ ሪፖርት” እንዲቀርብላቸው አዘዋል።
በአገሪቱ በትጥቅ የተደገፉ ጠላፊ ወንጀለኞችና ታታቂ ቡድኖች በሚፈጽሟቸው ጥቃቶች ሳቢያ የፕሬዝዳንት ቡሃሪ መንግሥት እየተስፋፋ ያለውን የደኅንነት ስጋት ሊቆጣጠር አልቻልም በሚል እየተጠናከረ የመጣ ትችት ይቀርብበታል።












