በካናዳ ከፍተኛ የስልክ እና ኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጥ አጋጠመ

የቶሮንቶ ከተማ ነዋሪዎች የዋይፋይ አገልግሎት ፍለጋ ወደ ካፍቴሪያዎች አቅንተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የካናዳ ግዙፉ የስልክ እና የኢንተርኔት አገልግሎት አቅራቢ ኩባንያ ባጋጠመው እክል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተጠቃሚዎቹ የኢንተርኔት እና የስልክ አገልግሎት ተቋረጠባቸው።

ሮጀርስ ኮሚኒኬሽንስ ባጋጠው እክል ምክያት የባንክ ገንዘብ ማውጫ ማሸኖች (ኤቲኤም) እና የአደጋ ጊዜ አገልግሎት መስጫ የስልክ ቁጥሮች ከአገልግሎት ውጪ ሆነዋል።

ሮጀርስ ያጋጠመው እክል መንግሥታዊ አገልግሎቶች ላይም እንቅፈታት መፍጠሩ ተነግሯል።

የቴሌኮም ኩባንያው በመላው አገሪቱ ያጋጠመውን ችግር ለመቅረፍ እየሰራ መሆኑን አስታውቋል። “ደንበኞቻችን አገልግሎት ሳይቋረጥባቸው መቆየታቸው ምን ያክል አስፈላጊ እንደሆነ እንገንዘባለን” ብሏል ኩባንያው ባወጣው መግለጫ።

የስልክ እና የኢንተርኔት አገልግሎቱ እንዲቋረጥ ያደረገው ምክንያት ምን እንደሆ እስካሁን አልታወቀም። ይሁን እንጂ ኩባንያው ባለፉት 15 ወራት ውስጥ ተመሳሳይ ችግር ሲያጋጥመው ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።

የአገራትን የኢንተርኔት አገልግሎት የሚከታተለው ኔትብሎክስ፤ በአገሪቱ ሰዓት አቆጣጠር አርብ ንጋት ላይ የኢንተርኔት አገልግሎት ከ75 በመቶ በታች ሆኗል ብሏል።

ሮጀርስ ከ11 ሚሊዮን ያላነሱ ካናዳውያን የስልክ አገልግሎት ተጠቃሚዎች ያሉት ሲሆን፤ የክፍያ ቴሌቪዥንን ጨምሮ የስፖርት ክለቦች ድርሻዎች ያሉት ትልቅ ኩባንያ ነው።

የቶሮንቶ ፖሊስ እርዳታ የሚሹ ተጠቃሚዎች በስልክ ሊያገኙኝ አልቻሉም ሲል በትዊተር ገጹ ላይ ጽፏል።

የመዲናዋ ኦታዋ ፖሊስ በበኩሉ ሰዎች ወደ ፖሊስ የሚያደርጉት ጥሪ ሳይሳካ ቢቀር በተደጋጋሚ እንዲሞክሩ፣ በመደበኛ ስልክ እንዲደውሉ አልያም ሌላ የስልክ አግልግሎት አቅራቢን እንዲጠቀሙ መክሯል።

የሮጀርስ አገልግሎት መቋረጥ ፖስታ ቤቶችን፣ ፍርድ ቤቶች እና የትራንስፖርት ክፍያ መፈጸሚያ ሥርዓቶች ላይም ችግር አስከትሏል።

በአንዳንድ የካናዳ ከተሞች በርካታ ሰዎች ወደ ካፍቴሪያዎች እና የዋይፋይ አገልግሎቶች ወዳሉባቸው ቦታዎች ሲተሙ ታይተዋል።

ትናንት ዓርብ ሐምሌ 01/2014 የሮጀርስ ኮሚኒኬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ኩባንያው ያጋጠመው ‘መሠረታዊ ችግር’ ምን እንደሆነ ለመለየት እየሰራ ነው ሲሉ ለሲቢሲ ተናግረዋል።

“እስካሁን ችግሩ መቼ እንደሚቀረፈ አናውቅም። . . . ዛሬ ወይ ነገ ሰዎች አገልግሎት ማግኘት ይጀምራሉ የሚለውን በትክክል መናገር አልችልም” ሲሉ የኩባንያው ምክትል ፕሬዝዳንት ኬይ ፕሪግ ተናግረዋል።

ምክትል ፕሬዝዳንቱ ኩባንያው ችግር ውስጥ የገባው የሳይበር ጥቃት ተፈጽሞበት ይሆን ስለሚለው ጥርጣሬ ከመናገር ተቆጥበዋል።