ሩሲያዊው ፖለቲከኛ ጦርነቱን በማውገዛቸው የሰባት ዓመት እስር ተፈረደባቸው

የፎቶው ባለመብት, KIRILL KUDRYAVTSEV/AFP
በሞስኮ ምክር ቤት አባል የሆኑት አሌክሲ ጎሪኖቭ ሩሲያ በዩክሬን ላይ የከፈተችውን ጦርነት ተቃውመው በመናገራቸው የሰባት ዓመት እስር ተፈረደባቸው።
ግለሰቡ በተቃዋሚዎች ላይ ያነጣጠረ ነው በተባለለት አዲስ ሕግም የመጀመሪያ እስር የተፈረደባቸው ፖለቲከኛ ሆነዋል።
የ60 ዓመቱ ፖለቲከኛ በከተማዋ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ወረራውን ሲነቅፉ በተንቀሳቃሽ ምስል ከተቀረጹ በኋላ ሚያዝያ ላይ ነበር በቁጥጥር ስር የዋሉት።
ከወረራው በኋላ በወጣው ሕግ መሠረት ስለ ወታደራዊ ኃይሉ "ሐሰተኛ ዜና" የሚያሰራጭ ማንኛው ግለሰብ እስከ 15 ዓመት የሚደርስ የእስር ቅጣት ይጠብቀዋል።
ሩሲያ ዩክሬን ላይ ወረራ ከከፈተች በኋላ የአገሪቱ ዜጎች ወረራውን "ጦርነት" ብለው እንዳይገልጹ ክልከላ ተጥሎባቸዋል።
ከዚህ ይልቅ ግን ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጦርነቱን ለመግለጽ "ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ" የሚል አገላለጽን አስተዋውቀዋል።
የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች የሆኑት ፓቬል ቺኮቭ በምክር ቤት አባሉ ጎሪኖቭ ላይ የተላለፈውን ብይን በተመለከተ እንደታናገሩት፣ በአዲሱ የሩሲያ ሕግ መሠረት የተወሰነ የመጀመሪያው የእስር ቅጣት ነው ብለዋል።
እስከ አሁኑ ውሳኔ ድረስ በተመሳሳይ ጉዳይ ተከሰው ፍርድ ቤት የቀረቡ ሰዎች የገንዘብ ቅጣት ወይም በገደብ የእስር ብይን እየተወሰነባቸው ነበር።
የእስር ውሳኔውን ያስተላለፉት ዳኛ ኦሌሲያ ሜንዴሌዬቫ፣ ግለሰቡ ወንጀሉን የፈጸሙት "ፖለቲካዊ ጥላቻን መሠረት አድርገው" የአገሪቱ ዜጎች በማሳሳት "ስጋትና ጭንቀት እንዲሰማቸው" ለማድረግ በማሰብ ነው ብለዋል።
በሰሜናዊ ሞስኮ ውስጥ በሚገኝ ፍርድ ቤት የቀረቡት ጎሪኖቭ በእጅ የተጻፈ "አሁንም ጦርነቱን ትፈልጉታላችሁ?" የሚል ጥያቄ የያዘ ወረቀትን ይዘው ለማሳየት ሲሞክሩና የፀጥታ ጠባቂዎች መልዕክታቸው እንዳይታይ ሲከላከሉ ተስተውለዋል።
ተቃዋሚው የምክር ቤት አባል በአንድ የአካባቢ ስብሰባ ላይ የተከሰሱበትን ንግግር ካደረጉ ከአንድ ወር በኋላ ነበር ባለፈው ሚያዚያ ወር ለእስር የተዳረጉት።
በስብሰባው ላይ ጎሪኖቭ በአካባቢው የሚካሄደውን የልጆች የስዕል ውድድርን በተመለከተ ቀረበውን ሐሳብ ተቃውመው፣ ዩክሬን ውስጥ ልጆች እየሞቱ ውድድሩ መካሄድ የለበትም ብለው ነበር።
በተጨማሪም ስብሰባው በጦርነቱ ለሞቱ ሰዎች የአንድ ደቂቃ ፀሎት በማድረግ እንዲጀመር ለማድረግ ሞክረው ነበር።
ይህንን ሐሳብ የደገፉ ሌላ የምክር ቤት አባል ደግሞ ከሩሲያ ወጥተው ተሰደዋል።
ዐቃቤ ሕግ ባቀረበው ክስ ላይ ሁለቱ ግለሰቦች ሆን ብለው የሩሲያን ሠራዊት ስም ለማጥፋት አሲረዋል ብሏል።
አርብ ዕለት ፍርድ ተገኝተው የነበሩ የመብት ተሟጋቾችና ጋዜጠኞች እንደተናገሩት፣ ሩሲያ ያላትን የጦርነት አቅም በ20ኛው ክፍለ ዘመን ጦርነቶች አሟጣላች ሲሉ ጎሪኖቭ ለዳኞቹ ሲናገሩ ተደምጠዋል።
የምክር ቤት አባሉ የሩሲያ ሠራዊት ዩክሬን ውስጥ የጦር ንጀል ፈጽመውባቸዋል የተባሉ ቦታዎችን ስም በመጥቀስ ለጦርነቱ ያላቸውን ተቃውሞ ተናግረዋል።
የግለሰቡ ወዳጆችና ደጋፊዎች በፍርድ ቤቱ የተላለፈባቸውን የሰባት ዓመት የእስር ውሳኔ ተቃውመውታል።
የሩሲያ ፖለቲካ ተንታኝ ታቲያና ስታኖቫያ እንዳለችው በዚህ የፍርድ ውሳኔ ባለሥልጣናት "ለተቃዋሚዎች" ግልጽ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በባለሥልጣናት ዐይን "ጦርነት" የሚለውን ቃል መጠቀም በአገር ላይ አሻጥር መፈጸም ነው በማለት፣ ይህም ጎሪኖቭ እንዳደረጉት ፖለቲካዊ እርምጃዎች ከታከሉበት ደግሞ እንደ ሽብር ድርጊት ተቆጥሮ ረጅም የእስር ቅጣትን ያስከትላል ብላለች።
በተመሳሳይ ባለፈው ግንቦት ወር ከሴንት ፒተርስበርግ ከተማ ሊነሳ ከነበረ አውሮፕላን እንዲወርድ የተደረገው ታዋቂው የዴሞክራሲያዊ መብት ተከራካሪ በሆነው አንድሬይ ፒቮቫሮቭ ላይ የረጅም ጊዜ አስር እንዲበየተን የሩሲያ ዐቃቤ ሕግ እየጠየቀ ነው።
ጠበቃው እንዳሉት ፒቮቫሮቭ የተከሰሰው በአገሪቱ ውስጥ የማይፈለግ ነው የተባለውን 'ኦፕን ሩሲያ' የተሰኘውን ድርጅት በመምራቱ ነው።












