በዩክሬን በሩሲያ ጦር የተያዙ ሁለት እንግሊዛውያን በቅጥረኝነት ተከሰሱ

በዩክሬን በሩሲያ ጦር የተያዙ ሁለት ተጨማሪ የእንግሊዝ ዜጎች ቅጥረኛ ናቸው በሚል ክስ እንደተመሰረተባቸው የሩሲያ መንግስት ሚዲያ ዘግቧል።
በእርዳታ ስራ ላይ በበጎ ፈቃደኝነት ሲያገለግል የነበረው ሼፍ ዲላን ሄሊ በቁጥጥር ስር የዋለው በሚያዝያ ወር በፍተሻ ጣቢያ ላይ ነው።
ዲላን በቁጥጥር ስር በዋለበት ዕለት ሌላኛው ግለሰብ አንድሪው ሂል ወታደራዊ መለዮ ለብሶ እጅ ሲሰጥ የሚያሳይ ቪዲዮ በሩሲያ ተለቋል።
ከዚህ ቀደም በዩክሬን በሩሲያ ጦር የተያዙት ሌሎች ሁለት የእንግሊዝ ዜጎች ሻውን ፒነር እና አይደን አስሊን ቅጥረኛ ናቸው በሚል ባለፈው ወር የሞት ፍርድ እንደተፈረደባቸው ይታወሳል።
በአለም አቀፍ ደረጃ እውቅና በሌለው በምስራቅ ዩክሬን በሚገኘው የሩሲያ የውክልና ፍርድ ቤት በዋለው ችሎት ዲላን ሄሊና እና አንድሪው ሂል ተመሳሳይ ክስ ቀርቦባቸዋል።
የአውሮፓ የሰብአዊ መብቶች ፍርድ ቤት ውሳኔው እንዳይፈፀም በመጠየቅ ጣልቃ ገብቷል።
ነገር ግን ሩሲያ የስትራስቡርግ ፍርድ ቤት ትዕዛዝን እንደማትቀበል በመግለጽ ጥሪውን ውድቅ ያደረገች ሲሆን የግለሰቦቹም እጣ ፈንታ የሩስያ ደጋፊ የሆነው የዶኔትስክ ህዝብ ሪፐብሊክ ጉዳይ ነው ብላለች።
የሩስያ ታስ የዜና ወኪል ባወጣው ዘገባ መሰረት፣ ራሱን የዶኔትስክ ህዝብ ሪፐብሊክ ብሎ የሚጠራው ግዛት ስማቸው ያልተጠቀሰ ባለስልጣን ዲላን ሄሊና እና አንድሪው ሂል “ቅጥረኛ ተግባራት በመፈጸም” ክስ እንደሚቀርብባቸው ተናግረዋል።
ሁለቱም ግለሰቦች ከመርማሪዎች ጋር ለመተባበር ፈቃደኛ እንዳልሆኑ ተዘግቧል። ስለ ክሱ በገለልተኛ ወገን የተረጋገጠ ነገር የለም።
የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የጦር ምርኮኞች እንዲሁም በሰላማዊ ዜጎችን ለፖለቲካ ፍጆታ በሚል የሚደርሰውን መበዝበዝ እንደሚያወግዝ ገልጿል።












