ሚሼል ፕላቲኒ እና ሴፕ ብላተር ከማጭበርበር ወንጀል ነፃ ናቸው ተባሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቀድሞው የፊፋ ፕሬዝዳንት ሴፕ ብላተር እና ምክትላቸው የነበሩት ሚሼል ፕላቲኒ ከማጭበርበር ወንጀል ነፃ ናቸው ተብለዋል።
ሁለቱ የእግር ኳሱ ዓለም ዘዋሪ የነበሩት ግለሰቦች በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ችሎት ፊት ቀርበው ነበር።
ብላተር ለፕላቲኒ ባልተገባ መንገድ 2 ሚሊዮን የስዊዝ ፍራንክ ሰጥተዋቸዋል በሚል ነው የተከሰሱት።
ግለሰቦቹ ገንዘቡን ተረካክበዋል የተባለው በፈረንጆቹ 2011 ነበር።
ሁለቱም የተጠረጠርንበት ወንጀል አግባብ አይደለም ሲሉ ሞግተዋል። ብላተርገ ንዘቡን የከፈልኩት ፕላቲኒ ለፊፋ ላበረከቱት የምክር አገልግሎት ነው ብለዋል።
ባለፈው ዓርብ ፍርድ ቤት የቀረቡት ብላተር “እርግጥ ነው ጥፋት አጥፍቼ አውቃለሁ፤ ይህ ክስ ግን ውሃ አያነሳም” ሲሉ ተደምጠዋል።
የስዊትዘርላንድ ፌዴራል ፍርድ ቤት የሁለቱን ሰዎችጉዳይ ለ11 ቀናት ሲከታተል ቆይቷል።
ፍርድ ቤቱ የሁለቱን ግለሰቦች ጉዳይ ከግራና ቀኝ ካደመጠ በኋላ ነፃ ናቸው ሲል አሰናብቷቸዋል።
ሚሼል ፕላቲኒ
የ66 ዓመቱ ፈረንሳዊ ፕላቲኒ ሦስት ጊዜ የባሎን ደኦር ሽልማትን ማንሳት የቻለ ድንቅ ተጫዋች ነበር።
ከፈረንሳይ ጋር የ1984ቱን የአውሮፓ ቻምፒዮንሺፕን ከጁቬንቱስ ጋር ደግሞ በ1985 የአውሮፓ ዋንጫን አንስቷል።
ፕላቲኒ ለተወሰነ ጊዜ የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድንን ካሠለጠነ በኋላ በሌሎች የእግር ኳስ አስተዳደር ቦታዎች ሠርቷል።
ሚሼል ፕላቲኒ የአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበር ኃላፊ ሆኖ የተመረጠው በ2007 ነበር።
በፈረንጆቹ 2015 ብላተር በሙስና ተጠርጥረው የሥራ መልቀቂያ ሲያስገቡ ፕላቲኒ ሊተካቸው እንደሚችል ተገምቶ ነበር።
ነገር ግን የፕላቲኒን መዝገብ የመረመረው የፊፋ የሥነ ምግባር ኮሚቴ ፕላቲኒም እጁ አለበት ሲል ከሰሰ።
በዚህ ምክንያት ለስምንት ዓመት ከእግር ኳስ እንዲርቅ ታገደ። የኋላኋላ እገዳው ወደ አራት ዓመት እንዲወርድ ተወሰነ።
ፕላቲኒ ጉዳዩን ለእግር ኳስ የግልግል ዳኞች [ካስ] ቢያቀርብም ውድቅ ሆኖበታል።
ሴፕ ብላተር
የ86 ዓመቱ ስዊዝ የቢዝነስ ሰው ጆሴፍ ብላተር ፊፋን የተቀላቀሉት በፈረንጆቹ 1975 ነው።
የፊፋ ፕሬዝደንት ሆነው የተሾሙት ደግሞ በ1998።
ብላተር በተለያየ ጊዜ ብዙ ተቃውሞ ቢገጥማቸውም ፊፋን ለ17 ዓመታት አስተዳድረዋል።
በሙስና፣ በገንዘብ አያያዝ፣ ጉቦ በመቀበልና የምርጫ ድምፅ በማዛባት ወንጀል ለበርካታ ዓመታት ሲከሰሱ ቆይተዋል።
ብላተር በ2015 ለ8 ዓመታት ከእግር ኳስ እንዲታገዱ ተወስኖባቸዋል። ዘለግ ብሎ ግን እገዳው ወደ 6 ዓመት ወርዶላቸዋል።
በ2021 ደግሞ ሌላ የ6 ዓመት እግድ ተጥሎባቸዋል።
ክሳቸው ምንድነው?
የስዊዝ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ለስድስት ዓመታት ምርመራ ካደረገ በኋላ ብላተርን በማጭበርበርና በሌሎች ተያያዥ ወንጀሎች ከሷቸዋል።
ፕላቲኒም እንዲሁም በማጭበርበርና “ፎርጅድ” በማሠራት እንዲሁም በሌሎች ተያያዥ መዝገቦች ተከሷል።
ፕላቲኒ በ2011 ከሴፕ ብላተር 2 ሚሊዮን የስዊዝ ፍራንክ አሊያም 1.5 ሚሊዮን ዩሮ ተቀብሏል ተብሎ ክስ ቀርቦበታል።
ዐቃቤ ሕግ እንደሚለው ፕላቲኒ ለማማከር ሥራው በዓመት 300 ሺህ የስዊዝ ፍራንክ እንዲከፈለው ስምምነት ቢኖርም ተጨማሪ 2 ሚሊዮን ተቀብሏል።
ሁለቱ ግለሰቦች ገንዘቡ ለማማከር ሥራ እንዲከፈል የቃል ስምምነት በመድረሳቸው የተከፈለ ነው።
ብላተር ክፍያው ሕጋዊ ነው ሲሉ ይሞግታሉ።
የሁለቱ ሰዎች ክስ ስዊዝ ውስጥ በፈረንጆቹ ሰኔ 22 ጀምሮ ሐምሌ 8 ውሳኔ ይሰጥበታል ተብሎ ይጠበቃል።
ተከሳሾቹ ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ እስከ አምስት ዓመት እስር አሊያም የገንዘብ ቅጣት ይጠብቃቸዋል።












