ኢሰመኮ በኢትዮጵያ የመኖር መብት እጅግ የከፋ አደጋ ውስጥ ገብቷል አለ

በአማራ ክልል በግጭት ምክንያት የተፈናቀሉ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በመጀመሪያው ዓመታዊ ሪፖርቱ በኢትዮጵያ የመኖር መብት እጅግ የከፋ አደጋ ውስጥ ገብቷል አለ።

ኮሚሽኑ ባለፉት 12 ወራት በመንግሥት የፀጥታ አካላትና በታጣቂ ቡድኖች ኃይሎች በርካታ ጥሰቶች ተፈጽመዋል ብሏል።

በሰሜኑ የኢትዮጵያ የእርስ በእርስ ጦርነት፣ የጦርነቱ ተሳታፊዎች ተገቢውን ጥንቃቄ ባለማድረጋቸው እና ሆነ ተብሎ በተወሰዱ እርምጃዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከፍርድ ውጭ ተገድለዋል ብሏል።

ከዚህ በተጨማሪ መንግሥት ኦነግ-ሸኔ ብሎ የሚጠራው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት፤ በብዙ መቶዎች በሚቆጠሩ ሲቪል ሰዎች ላይ ግድያ መፈጸሙን፤ እንዲሁም የመከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይል እና የፋኖ ታጣቂዎች ከትግራይ ኃይሎች ወይም ከኦነግ ሸኔ ጋር አብረዋል ያሏቸው ሰዎች ላይ ከፍርድ ውጪ ግድያ መፈፀማቸውን ጠቅሷል።

 ኮሚሽኑ በዓመታዊ ሪፖርቱ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ጉባ ወረዳ አይሲድ ቀበሌ 20 የመከለከያ ሠራዊት አባላት በታጣቂዎች መገደላቸውን ተከትሎ፣ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎችና ሌሎች የሲቪል ልብስ የለበሱ ሰዎች ከፍርድ ውጪ ግድያ መፈጸማቸውን እና አንድ በሕይወት የነበረን ሰው እና አስከሬኖችን በእሳት ማቃጠላቸውን አስታውሷል።

ኢሰብዓዊ እና አዋራጅ አያያዝ

ኢሰመኮ በዓመታዊ ሪፖርቱ ሲቪሎች በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና በታጣቂ ቡድኖች ከፍርድ ውጪ በሆነ መልኩ ከመገደላቸው በተጨማሪ የሰዎች ኢሰብአዊና አዋራጅ አያያዝና ቅጣት ነፃ የመሆን መብቶቻቸው ተጥሷል ብሏል።

በሰሜን ኢትዮጵያው የእርስ በእስር ጦርነት ተሳታፊ የሆኑ ኃይሎች ይዘዋቸው የነበሩትን ሲቪል ሰዎችን በጭካኔ የመደብደብ፣ የማዋረድ እና የማሰቃየት ተግባር ፈጽመዋል።

በተማረኩ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ የኤርትራ ሠራዊትና፣ የትግራይ ኃይሎች ላይ ማሰቃየትና ኢ-ሰብአዊ አያያዝ ተፈጽሟል።

የዘፈቀደ እስር እና አፈና

ኢሰመኮ በኢትዮጵያ ባለፉት 12 ወራት ሰዎች በዘፈቀደ መታሰራቸውን እና ተገድደው እንዲሰወሩ መደረጋቸውን አትቷል።

 “በተለይ በሥራ ላይ ከነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር ተያይዞ በበርካታ የሀገሪቱ አካባቢዎች የዘፈቀደ እስራት፣ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ማሰር፣ አስገድዶ መሰወር፣ የቤተሰብ እና የሕግ ባለሙያ ጉብኝትን መከልከል እንዲሁም ምርመራ ሳይጀመር በተራዘመ የቅድመ ክስ እስራት ማቆየት በሰፊው ተስተውሏል” ብሏል ኮሚሽኑ።

ኢሰመኮ ህወሓት የትግራይ ክልልን ለማስተዳደር ተግባራዊ ያደረገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሰዎችን መብቶች በከፍተኛ ሁኔታ የገደበ እና ከኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት እና የወንጀል ሕግ ጋር የሚጣረስ ነው ብሏል።

ህወሓት ተግባራዊ ያደረገው አዋጅ መሠረት ከፌዴራል መንግሥት ጋር የሚደረግ የሥራ ግንኙነትም በወንጀል የሚያስጠይቅ እና ወላጆች በግዳጅ ልጆቻቸው የሕወሓትን ሠራዊት እንዲቀላቀሉ የሚያስገድድ ነው ብሏል።

ሃሳብን በነጻ የመግለጽ መብት

ኢሰመኮ በትግራይ ክልል የተጀመረውን ጦርነት ተከትሎ የስልክ እና የኢንተርኔት ግንኙነት እንደተቋረጠ በመቀጠሉ መረጃ የመፈለግ፣ የመቀበል እና የማስተላለፍ መብት ላይ ከፍተኛ ገደብ ጥሏል ብሏል።

ከሐምሌ 2013 ዓ.ም. እስከ ግንቦት2014 ዓ.ም. ድረስ 39 የሚዲያ ሠራተኞች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ኢሰመኮ ገልጿል።

ከእነዚህ መካከል 15 የሚዲያ ሠራተኞች በትግራይ ባለሥልጣናት በክልሉ የታሰሩ መሆናቸውን በሪፖርቱ ተመላክቷል።

ስድስተኛው አገራዊ ምርጫን በተመለከተ

ኢሰመኮ 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ በአብዛኛው በሰላማዊ መልኩ ተካሂዷል ብሏል።

ምርጫውን ለማስፈጸም በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በኩል የተደረጉት ጥረቶች በጎ እርምጃዎች ነበሩ ብሏል።

 በሌላ በኩል በተቃዋሚ ፓርቲ አባላት እና ደጋፊዎቻቸው ላይ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ጫናዎችን ማሳደር እንዲሁም ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎቻቸውን የመገደብ ጥረቶች ነበሩ ብሏል።

የታሠሩ ሰዎች መብቶች

“የፌዴራልም ሆነ የክልል ማረሚያ ቤቶች እጅግ በውስን አቅም እየሰሩም ቢሆን ባደረጉት ልዩ ልዩ ማሻሻያዎች ብዙ መልካም እርምጃዎች ተወስደዋል” ይላል ዓመታዊው የኮሚሽኑ ሪፖርት።

 ይሁን እንጂ በበርካታ ማረሚያ ቤቶች ታራሚዎችን አካላዊ ቅጣት የሚቀጡ መሆኑ፣ ለታራሚዎች በቂ እና ጥራቱን የጠበቀ የምግብ እና የሕክምና አገልግሎት እንደማይሰጡ እና ፖሊስ ጊዜውን ጠብቆ ተጠርጣሪዎችን ፍ/ቤት እንደማያቀርብ ዘርዝሯል።

 ኮሚሽኑ በሪፖርቱ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ሰዎች መደበኛ ባልሆኑ ማቆያ ስፍራዎች መታሰራቸውን ገልጿል።

በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ፣ በአማራ፣ በአፋር፣ በኦሮሚያ እና በደቡብ ክልሎች በርካታ ሰዎች ታጣቂ ኃይሎችን ደግፋችኋል ወይም አባል ናችሁ በሚል መደበኛ ባልሆኑ ማቆያ ስፍራዎች ታስረዋል ብሏል።

በአማራ ክልል በግጭት ምክንያት የተፈናቀሉ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች

ኢሰመኮ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች በግጭትና በተፈጥሯዊ አደጋ ምክንያት ከቀያቸው ተፈናቅለው በተለያዩ መጠለያ ጣቢያዎች ተጠልለው በችግር ውስጥ ይገኛሉ ብሏል።

ለተፈናቃዮች ችግር መፍትሄ የሚሰጥ በሕግ የተቋቋመ መንግሥታዊ አካል አለመኖሩ ቸግሩን ውስብስብ ማድረጉ ተመልክቷል።

የሰሜኑ የኢትዮጵያ የእርስ በእርስ ጦርነት በስደተኞች ላይ ከፍተኛውን የሰብአዊ መብቶች አደጋ ውስጥ የከተተ መሆኑ ተመልክቷል።