የቀድሞው የጃፓን ጠቅላይ ሚንስትር ሺንዞ አቤ በጥይት ከተመቱ በኋላ አረፉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በፖለቲካዊ ቅስቀሳ ላይ ሳሉ በጥይት ተመትተው የነበሩት የቀድሞው የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ አረፉ።
ዛሬ ጠዋት ሺንዞ አቤ ላይ ጥቃቱን ያደረሰው ግለሰብ ከኋላቸው መጥቶ ሁለት ጊዜ እንደተኮሰባቸው ተዘግቦ ነበር።
የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ፉሚዮ ኪሺዳ በከፍተኛ ሃዘን ውስጥ ሆነው እምባቸውን ለመቆጣጠር እየታገሉ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ አቤ “በአስጊ ሁኔታ ላይ” መሆናቸውን ተናግረው ነበር።
ጨምረውም “በአሁኑ ወቅት ዶክተሮች የቻሉትን ሁሉ እያደረጉ” መሆናቸውን በመጥቀስ፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቤ ሕይወት እንዲተርፍ ከልባቸው እየጸለዩ መሆኑን ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኪሺዳ ጥቃቱን “ክፋት እና ጭካኔ የተሞላበት የማይታገሱት” ድርጊት እንደሆነ ገልጸዋል።
የቀድሞ የቶኪዮ ገዢ ዮኢቺ ማሱዞ በትዊተር ገጻቸው ላይ የሺንዞ አቤ ‘የልብ ምታቸው መቀነሱን’ ጠዋት ላይ ጽፈዋል።
አብዛኛውን ጊዜ ይህ አገላለጽ በጃፓን አንድ ግለሰብ መሞቱ በይፋ ከመነገሩ በፊት ጥቅም ላይ የሚውል ነው።
በቀድሞው የጃፓን ጠቅላይ ሚንስትር ላይ ተኩስ የከፈተው የ41 ዓመቱ ግለሰብ በፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር መዋሉም ተዘግቧል።
በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በስፋት የተጋሩት እና እስካሁን ትክክለኛነታቸው ያልተረጋገጡ ተንቀሳቃሽ ምስሎች፣ የሕክምና ባለሙያዎች መሃል መንገድ ላይ የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትርን ከበው የሕክምና እርዳታ ሲያደርጉ ታይተዋል።


የፎቶው ባለመብት, NHK
ጃፓንን ለረጅም ጊዜ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ያገለገሉት ሺንዞ አቤ ግድያ ከአገሪቱ አልፎ መላውን ዓለም አስደንግጧል።
ግድያውን በተመለከተ አስካሁን የሚታወቁ ዋና ጉዳዮች፡
- ከዋና ከተማዋ ቶኪዮ በስተደቡብ በ480 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ናራ ከተማ ውስጥ በሚካሄድ የምክር ቤት ምርጫ ቅስቀሳ ላይ ንግግር ሲያደርጉ ነበር።
- በአሁኑ ወቅት የአገሪቱ የላይኛው ምክር ቤት አባል የሆኑት ኬይ ሳቶ ለድጋሚ ምርጫ ለሚያደርጉት ቅስቀሳ ድጋፍ በመስጠት ነበር የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ንግግር እያደረጉ የነበረው።
- ንግግር በሚያደርጉበት ጊዜ የሁለት ጥይት ተኩስ የተሰማ ሲሆን፣ አቤም አንገታቸው ላይ ሳይመቱ እንዳልቀረ ይነገራል።
- አቤ በጥይት ከተመቱ በኋላ ወዲያውኑ መሬት ላይ የወደቁ ሲሆን፣ በፍጥነት በአቅራቢያ ወደሚገን ሆስፒታል ተወስደዋል።
- በስፍራው የነበሩ የደኅንነት ሰዎች ጥቃት ፈጻሚውን የተቆጣጠሩት ሲሆን አሁን በእስር ላይ ይገኛል።
- ጥቃቱ ተፈጽሞበታል የተባለና ምንነቱ ያልታወቀ መሳሪያ መሬት ላይ ወድቆ የታየ ሲሆን፣ ጥቃት ፈጻሚው ቤት ውስጥ የተሰራ ሽጉጥ ሳይጠቀም እንዳልቀረ ይታመናል። ፖሊስ ግን አስካሁን አላረጋገጠም።

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የጃፓን የአደጋ ጊዜ ባለሥልጣን እንዳለው ጥቃቱን ተከትሎ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር በአንገታቸው የቀኝ ክፍል በጥይት መመታታቸውንና በግራ ደረታቸው በኩልም ከፍተኛ የደም መፍሰስ አጋጥሟቸው ነበር።
ብሔራዊው የቴሌቪዥን ጣቢያ ኤንኤችኬ የፖሊስ ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው ከጥቃቱ በኋላ አቤ “እራሳቸውን አለመሳታቸውንና ንቁ” እንደነበሩ ገልጿል።
ነገር ግን አቤ አባል የሆኑበት ፓርቲ እንዳለው የ67 ዓመቱ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ተጨማሪ ደም እየተሰጣቸው እንደሆነና ያሉበት ሁኔታን “አሳሳቢ” ሲል ገልጾታል።
ሺንዞ አቤ ጥቃቱ የተፈጸመባቸው ከመዲናዋ ቶኪዮ በስተደቡብ አቅጣጫ በምትገኘው ናራ በተባለችው ከተማ በአንድ ዕጩ ፖለቲከኛ የቅስቀሳ መድረክ ላይ ተገኝተው ንግግር ሲያደርጉ ነው።
የዐይን እማኞች እንዳሉት ከሆነ ሺንዞ አቤ ንግግር እያደረጉ ሳለ አንድ የጦር መሳሪያ የያዘ ሰው ከጀርባቸው መጥቶ ሁለት ጊዜ ተኩሶባቸዋል።
የመጀመሪያው ጥይት ሺንዞ አቤን ከሳታቸው በኋላ ሁለተኛው ግን ጀርባቸውን እንደመታቸው ተነግሯል።
ሺንዞ አቤ እንደተመቱ ወድቀው ደም ይፈሳቸው እንደነበረ በስፍራው የነበሩ የዐይን እማኞች ተናግረዋል።
ጥቃቱን ያደረሰው ግለሰብ ለመሸሽ ምንም አይነት ሙከራ ያላደረገ ሲሆን፤ በፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር ውሏል።
የጃፓን መገናኛ ብዙኃን የጥቃት ፈጻሚውን ግለሰብ ማንነት መለየቱንና በግድያ ሙከራ ክስ እንደተመሰረተበት ዘግበዋል።
ጃፓንን በጠቅላይ ሚንስትርነት ለረዥም ጊዜ በመምራት የሚታወቁት ሺንዞ አቤ፤ በጤና እክል ምክንያት ሥልጣናቸውን የለቀቁት ከሁለት ዓመት በፊት ነበር።
በጃፓን ጦር መሳሪያዎችን በመጠቀም የሚፈጸሙ ወንጀሎች አነስተኛ ናቸው።
በፖለቲካዊ ሁነቶች ላይም ግጭቶች ተሰምተው አያውቁም ማለት ይቻላል።
ሰዎች በጃፓን አንስተኛ የጦር መሳሪያዎችን ገዝቶ ለመታጠቅ ጥብቅ ፈተና እንዲሁም የአእምሮ ጤና ምርመራ ማለፍ ይጠበቃል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images












