የ18 ስደተኞች አስክሬን በእሳት ከወደመ የግሪክ መንደር ውስጥ ተገኘ

እሳት ያወደመው ቦታ

የፎቶው ባለመብት, DIMITRIS ALEXOUDIS

በሰሜናዊ ግሪክ በእሳት ከወደመ እና በደን ተሸፍኖ ከነበረ መንደር ውስጥ ስደተኞች ሳይሆኑ አይቀርም የተባለ የ18 ሰዎች አስክሬን ተገኘ።

የሰዎች አስክሬን የተገኘበት ከቱርክ የሚዋሰነው ሰሜን ምስራቅ ግሪክ በከፍተኛ የሰደድ እሳት ተመትቷል።

በአካባቢው ያለው ከ40 ዲግሪ ሴሊሺዬስ በላይ የሆነው ሙቀት ከኃይለኛ ንፋስ ጋር ተደማምሮ በርካታ የግሪክ አካባቢዎች የሰደድ እሳት እንዲነሳ ምክንያት ሆኗል።

ትናንት ማክሰኞ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች በእሳት የወደሙ ቤቶችን ሲፈልጉ ሁለት ቦታ የ18 ሰዎች አሰክሬንን አግኝተዋል።

በአካባቢው እስካሁን አድራሻው የጠፋ ነዋሪ ስለሌለ ሟቾቹ ስደተኞች የመሆን እድላቸው ሰፊ ነው የሚል ግምት ተሰጥቷል።

ሰዎቹ እንዴት ወደ ግሪክ ድንበር አቋርጠ እንደገቡ እና አሟሟታቸውን የሚመረምር ቡድን ወደ ስፍራው እየተጓዘ ነው።

የ18 ሰዎች አስክሬን የመገኘቱ ዜና ከመዘገቡ በፊት በዚህ ኢቭሮስ በተባለው ግዛት ስደተኛ የሆነ ሰው ሕይወት በሰደድ እሳቱ ምክንያት ስለማለፉ ተገልጾ ነበር።

ኢቭሮስ ግዛት ከቅርብ ግዜ ወዲህ ከሶሪያ እና ኢሲያ አገራት የሚነሱ ስደተኞች ኢቭሮስ ወንዝን በመሻገር ወደ አውሮፓ ኅብረት አገራት ለመግባት የሚመርጡት መንገድ ሆኗል። ይህ የጉዞ መስመር የመረጡ ስደተኞች የሰደድ እሳት የተነሳበትን ዳዲአ ደን ማቋረጥ የግድ ይላቸዋል።

የአካባቢው ባለስልጣናት የሰደድ እሳቱ መስፋፋትን ተከትሎ በአካባቢው ላሉ የሞባይል ስልኮች በሙሉ የማስጠንቀቂያ መልዕክት ልከናል ይላሉ።

ስደተኞችን በመደገፍ የሚታወቀው አላርም ፎን የሰደድ እሳት ባለበት አካባቢ ካሉ ስደተኞች ጋር መልዕክት ስለዋወጥ ነበር ብሏል። ድርጅቱ የግሪክ ደንበርን የተሻገሩ 9 አባላት ያሉት የሰደተኞች ስብስብ እርዳታ እንፈልጋለን ብለውት እንደነበረ ገልጿል።

ባለፉት ሦስት ቀናት በኢቭሮስ ግዛት ብቻ 380ሺህ ሄክታር መሬት በእሳት መቃጠሉን የአገሪቱ መንግሥት አስታውቋል።

ግሪክ በሰሜን ምስራቃዊ የአገሪቱ ክፍል ብቻ ሳይሆን በሌሎች አካባቢዎችም የተቀሰቀሱ የሰደድ እሳቶችን ለማጥፋት እየደከመች ነው።

የእሳት አደጋ ብርጌድ ከግሪክ መዲና አቴንስ ሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ ከምትገኘው አኖ ሊኦሲአ በ10ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ከቀያጨው በአስቸኳይ እንዲወጡ ትዕዛዝ ሰጥተዋል።