በፓኪስታን አንድ ተማሪ በዋትስአፕ ባጋራቸው መልዕክቶች ምክንያት ሞት ተፈረደበት

የፎቶው ባለመብት, PA Media
ፓኪስታን ውስጥ አንድ የ22 ዓመት ተማሪ የእስልምና እምነትን የሚያንቋሸሹ መልዕክቶችን በዋትስአፕ አማካይነት በማስተላለፍ ተከሶ የሞት ቅጣት ተፈረደበት።
በፓኪስታኗ ግዛት ፑንጃብ ውስጥ ጉዳዩን የተመለከተው ፍርድ ቤት ወጣቱ የእስልምና እምነት ተከታዮችን ስሜት ለማስቆጣት አስቦ ሃይማኖትን የሚያራክሱ ምስሎችን እና ቪዲዮዎችን አጋርቷል ብሏል።
ከዚሁ ክስ ጋር በተያያዘ የተከሰሰ ሌላ የ17 ዓመት ተማሪ የእድሜ ልክ እስራት ተፈርዶበታል። ነገር ግን ሁለቱም ፍርደኞች ምንም ዓይነት ጥፋት አልፈጸምንም ብለው አስተባብለዋል።
በፓኪስታን ሃይማኖትን የማንቋሸሽ ድርጊት በሞት የሚያስቀጣ ተግባር ነው። አንዳንዶችም ለፍርድ እንኳን ሳይቀርቡ ተወግረው ይገደላሉ።
የፑንጃብ ግዛት ዋና ከተማ በሆነችው ላሆር ውስጥ ሞት እና የዕድሜ ልክ እስር በተፈረደባቸው በሁለቱ ተማሪዎች ላይ ክስ የቀረበባቸው ከሁለት ዓመት በፊት በፓኪስታን የፌደራል የምርመራ ተቋም የመረጃ መረብ ደኅንነት ክፍል ነው።
በዚህ ሳምንት የፍርድ ውሳኔያቸውን ያስተላለፉት ዳኞች የ22 ዓመቱ ወጣት ነቢዩ ሙሐመድን እና ሚስቶቻቸውን የሚያንቋሽሹ ቃላትን የያዙ ፎቶዎችን እና ቪዲዮዎችን በማዘጋጀቱ ሞት ፈርደውበታል።
የ17 ዓመቱ ተከሳሽ ደግሞ ምስሎቹን በማጋራት ክስ የእድሜ ልክ እስራት ተወስኖበታል።
ተከሳሹ ፎቶዎቹን እና ቪዲዮዎቹን ከሦስት የተለያዩ የሞባይል ቁጥሮች መቀበሉን የተናገረ ሲሆን፣ የፌደራል የምርመራ ተቋሙ የተከሳሹን ስልክ በመመርመር መልዕክቶቹ ተልከውለት የደረሱት እንደሆነ አረጋግጧል።
የተከሳሾቹ ተከላካይ ጠበቆች ሁለቱ ተማሪዎች “በሐሰተኛ ክስ ወጥመድ ውስጥ እንዲገቡ ተደርገዋል” ሲሉ ተከራክረውላቸዋል።
ማንነታቸው ያልተገለጸው ሞት የተፈረደበት ወጣት አባት ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ በልጃቸው ላይ የተጣለውን የሞት ፍርድ በተመለከተ ለከተማዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ እንደሚያርቡ ተናግረዋል።
ፍርድ ቤቱ በሌላኛው ተከሳሽ ተማሪ ላይ የዕድሜ ልክ እስራት የፈረደው የዕድሜውን ሁኔታ ከግምት በማስገባት ታዳጊ በመሆኑ ነው ብሏል።
በፓኪስታን ውስጥ ሃይማኖትን የማንቋሸሽ ድርጊቶችን የሚመለከቱ ሕግጋት በሕግ ውስጥ የተካተቱት የሕንድ አስተዳዳሪዎች በነበሩት የብሪታኒያ ቅኝ ገዢዎች ነበረ። ከዚያም በኋላ በአውሮፓውያኑ በ1980ዎቹ በፓኪስታን ወታደራዊ መንግሥት እንዲቀጥል ተደርጓል።
ባለፈው ዓመት ነሐሴ በአገሪቱ ምሥራቃዊ ከተማ ጃራንዋል ውስጥ ሁለት ክርስቲያኖች ቁርዓን ቀደዋል ተብሎ በርካታ አብያተ ክርስቲያናት እና ቤቶች መቃጠላቸው ይታወሳል።















