ከሥነ ምግባር ውጪ የሆነ ቪዲዮ አሰራጭታለች የተባለች ታዋቂ ናይጄሪያዊት ቲክቶከር ታሰረች

የፎቶው ባለመብት, Sani Maikatanga
ከሃይማኖታዊ ሥነ ምግባር ውጪ የሆነ ቪዲዮ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ አሰራጭታለች የተባለችን ታዋቂ ሴት ቲክቶከር ናይጄሪያ ውስጥ በቁጥጥር ስር መዋሏ ተዘገበ።
በሰሜናዊቷ ናይጄሪያ በምትገኘው ካኖ በተባለችው ግዛት ውስጥ የሚገኝ እስላማዊ ፖሊስ እንዳስታወቀው ታዋቂዋ ቲክቶከር “ከእስላማዊ ሥነ ምግባር ያፈነገጠ” ቪዲዮ በማጋራቷ ነው ይዞ ያሰራት።
ከሁለት ሳምንታት በፊት ሂስባህ የተባሉት እስላማዊ ፖሊሶች በግዛቲቱ ውስጥ የሚገኙ እና እስላማዊ መመሪያዎችን በተደጋጋሚ በመጣስ ቪዲዮዎችን በቲክቶክ ላይ ያጋሩ ቲክቶከሮችን ለመያዝ አደን መጀመሩን አስታውቆ ነበር።
የሃይማኖታዊው ፖሊስ ቃል አቀባይ ላዋል ፋጌ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ ታዋቂዋ ናይጄሪያዊት ቲክቶከር ሙርጃ ኢብራሂም ኩነያ ዛሬ ማክሰኞ ከወንድ ጓደኛዋ ጋር ነው በቁጥጥር ስር የዋለችው።
“የፖሊስ አባሎቻችን ተፈላጊዋን ግለሰብ ከጓደኛዋ ጋር ከቤቷ በቁጥጥር ስር አውለው፤ አሁን ሁለቱም በእኛ ጥበቃ ስር ይገኛሉ” ብለዋል።
ፖሊስ ጨምሮ እንዳለው በምታሳየው ባህሪ ምክንያት የቲክቶከሯ ጎረቤቶች ቀደም ብለው አቤቱታ አቅርበው ነበር። “ተጨማሪ እርምጃ ከመውሰዳችን በፊት በአሁኑ ጊዜ ምርመራ እያደረግን ነው” ብለዋል የፖሊስ ቃል አቀባይ።
ቲክቶከሯ በሚሊዮኖች በሚቆጠሩ ሰዎች በታዩ ቪዲዮዎቿ ላይ “ብልግና የተሞላባቸው እና አጸያፊ አገላለጾችን” ትጠቀማለች ተብላ ትከሰሳለች።
በፖሊስ ከተያዘች በኋላ ትክክለኛነቱ ባልተረጋገጠ ቪዲዮ ላይ የታየችው ቲክቶከር፣ ስለቀርቡባት ክሶች አስተያየቷን አልሰጠችም።
በቪዲዮው ላይ በፖሊስ የተያዘችው ምንም ነገር ሰርቃ እንዳልሆነ እና ለዚህም ፈጣሪዋን እንደምታመሰግን ስትናገር ተሰምታለች።
የካኖ ግዛት እስላማዊ ፖሊስ አዛዥ የሆኑት አሚኑ ዱራዋ ደንብ የተላለፉትን የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ለመያዝ አሰሳ ሲጀምሩ እንዳሉት፣ በቲክቶክ ላይ ይዘት ለሚያሰራጩ ተጠቃሚዎች መልዕክት አስተላልፈው ነበር።
በዚህም ቲክቶከሮቹ በሚያሰረጩት ቪዲዮ ላይ የሚወጡ ይዘቶች ሥርዓትን የተከተሉ እንዲሆኑ ቀደም ሲል የተላለፈላቸውን ትዕዛዝ ጥሰዋል ብለዋል።
በናይጄሪያዋ የካኖ ግዛት አብዛኛው ነዋሪ የእስልምና እምነት ተከታዮች ሲሆን፣ በግዛቲቱ ውስጥም ከዓለማዊው ሕግ ጎን ለጎን እስላማዊ ሕግ ሥራ ላይ ይውላል።












