ኢትዮጵያ፡ በዩቲዩብ እንዴት ‘በቀላሉ’ ገንዘብ ማግኘት ይችላል?

ሽመልስ፣ እዩኤል እና ፍራኦል

የፎቶው ባለመብት, Eyuel

የምስሉ መግለጫ, ሽመልስ፣ እዩኤል እና ፍራኦል

እዩኤል፣ ፍራኦል እና ሽመልስ ከ20 ዓመታት በላይ የቆየ ወዳጅነት አላቸው። ከልጅነት የተጀመረው ጓደኝነታቸው እስከ አሁን ዘልቋል።

የኮሮና ቫይረስ ወርሽኝ ተከስቶ እንቅስቃሴዎች ሲገደቡ ጓደኛሞቹ አንድ ነገር ለመስራት አቀዱ።

የተለያዩ ቪዲዮዎችን እየቀረጹ በዩቲየብ መልቀቅ። ሀሳባቸውንም ወደ ተግባር ቀየሩት።

ጥቂት ሳይቆዩ ገንዘብ ማግኘት ጀመሩ። ዩቲየብን ከተቀላቀሉ ከሁለት ወር በኋላም የመጀመሪያ ክፍያቸውን አገኙ። ክፍያው 5 ዶላር ወይም በያኔው ምንዛሬ ከ300 ብር ያልበለጠ ነበር።

አሁን ከ84 ሺህ በላይ ተከታዮች እና በአጠቃላይ ከ41 ሚሊዮን ጊዜ በላይ የታዩ 638 ቪዲዮችን ጭነዋል።

ከፍ ዝቅ የሚል ቢሆንም፣ ክፍያቸው በወር በሺዎች ወደሚቆጠሩ ዶላሮች ወይም ወደ መቶ ሺህ ብሮች ተመንድጓል።

ስራቸውን ሲጀምሩ፣ የሚቀርጹበት ስፍራ “ለማጸዳዳት” ካዋጡት ጥቂት ገንዘብ በስተቀር ‘ድንቡሎ’ አላወጡም።

በዩትዩብ ምን እንስራ ብለው ብዙ አልተጨነቁም። ቀላሉን መንገድ መረጡ - አጫጭር ቪዲዮችን በጋራ በማየት መሳቅ፣ መከራከር አሊያም ሀሳብ መለዋወጥ።

አንዳንዴ ካሜራ ፊት እስከማይመስል ድረስ እውነተኛ ስሜቶቻቸውን ያንጸባርቃሉ።

በልጅነታቸው ወይም ወደ ቀረጻ ከመምጣታቸው በፊት የገጠማቸውን ያወራሉ፣ ይስቃሉ። ይህ ነው ወደ ይዘት ተቀይሮ ገንዘብ የሚያመጣው።

ሶስቱም ሌላ መደበኛ ስራ ያላቸው ሲሆን ይህንን እንደ ትርፍ ጊዜ ስራ የሚያከናውኑት ነው።

ስራው ራሳቸው ከልብ የሚዝናኑበት፣ እውነተኛ ጓደኝነት እና ስሜታቸው የሚንጸባረቅበት ብቻ ሳይሆን የተለየ አቅም የማይጠይቅ እነሱ እንደሚሉት “ለእኛ እጅግ በጣም ቀላሉ ስራ ነው” ።

ስራው እጅግ ቀላል ይሁን እንጂ ከፍያው “ከባድ” ነው። “ህይወታችንን የሚቀይር ገንዘብ” ከዩቲዩብ እያገኙ እንደሆነ ይናገራሉ።

ልምዳቸውን ጠይቀናቸዋል።

ዩቲዩብ ለመጀመር ምን ያስፈልጋል?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ዩቲዩብ ለመጀመር ምን ያስፈልግ ይሆን? የሚለው ጥያቄ ምን አልባት ዩቲዩብ መጀመር በሚፈልጉ ሰዎች ጭንቅላት ውስጥ ሊመላለስ ይችላል።

ውድ ካሜራ፣ ቅንጡ ኮምፒውር አሊያም ያሸበረቀ ስቱዲዩ የግድ አይደለም።

ለዚህ ‘አውራ’ የተሰኘው የሦስቱ ወጣቶች ዩቲዩብ ቻናል ምስክር ነው።

እዩኤል ካሳ ይህንን ዩቲዩብ ጀምሮ ይህንን ያህል ገንዘብ ለማገኘት የወጣው ወጪ “እዚህ ግባ” የሚባል አይደለም ይላል።

“በአሁኑ ጊዜ የፕሮዳክሽን ዕቃ እና ባለሙያ በጣም በጣም ውድ ነው” የሚለው እዩኤል የእነሱ ሥራ በሞባይል በመቅረጽ የተጀመረ እንደሆነ ያወሳል።

ፍራኦል በዳዳ ደግሞ በዚህ የዩቲዩብ ቻናል ጅማሮ ትልቁ ወጪ የሚባለው የሚቀርጹበትን አካባቢ ለማስተካል የወጣ እንደሆነ በማንሳት ያም ገንዘብ “እጅግ ዝቅተኛ” የሚባል ነው ይላል።

ለአንዳንድ የዩቲየብ ይዘቶች ደግሞ ካሜራ ወይም ሌሎች ግብአቶች ላያስፈልጉ ይችላሉ። ድምጽ በመቅረጽ ወይም በዚያው በዩቲየብ የሚገኙ የቅጂ መብት የማይጠይቁ (copyright free) ሙዚቃዎችን በመጠቀም ከሌሎች ግብዓቶች ጋር በማዘጋጀት ማቅረብ ይቻላል።

እዩኤል በዩቲየብ የሚጫኑ ቪዲየዎች ‘ኤዲት’ ማድረግ “በጣም ቀላል” እና የተለየ እውቀት የማይፈልግ እንደሆነ ይገልጻል። ይህንንም የተማረው በዩቲየብ ከሚጫኑ ከሌሎች የማስተማሪያ ቪዲዮዎች ነው።

አሁን ላይ ኮምፒውተር ሳያስፈልግ ቪዲዮዎችን ‘ኤዲት’ ማድረግ የሚችሉ በርካታ የሞባይል መተግበሪያዎችም ይገኛሉ። መተግበሪያዎቹ ወጪን ከመቀነስ በተጨማሪ ሥራን እጅግ በማቅለል በርካቶች ያሞካሿቸዋል።

ለዚያ ነው ወጣቶቹ “እጃችን ላይ ያለው ስልክ ሕይወታችንን ለመቀየር አቅም አለው” የሚሉት።

እዚህ ጋ ግን ቁልፉ ጉዳይ የቻናሉ ይዘት ነው “አንዳንዴ ጊዜ በራስህ ተማምነህ በትንሽ ነገር የምትሠራው ቪዲዮ በቴክኒካቸው በጣም ከተሻሉ ቻናሎች የበለጠ ሊሆን ይችላል” የሚለው እዩኤል ለሥራው ከሚያስፈልገን ዕቃ ቅንጡነት በላይ “ምን አይነት ሀሳብ እናንሳ፣ ምን ይዘት ይኑረን?፣ ምን እንሥራ?” የሚለው ወሳኙ ነጥብ እንደሆነ ይናገራል።

ዩቲዩብ

የፎቶው ባለመብት, AFP

በዩቲዩብ ምን ይሠራል?

ምን ይሠራልስ? ለሚለው ጥያቄ ደግሞ የፍራኦል መልስ “ቀለል ያለ እና የምንችለው ነገር” ቢሆን ውጤታማ ሊያደርገን ይችላል የሚል ነው።

“አንዳንዴ የምናስበውን ነገር መሬት ላይ ለማውረድ ከባድ ሊሆን ይችላል [ስለዚህ] ለመተግበር ቀላል የሆነ ነገር መመረጥ ይኖርብናል” ሲል አክሏል።

በዚህ ሀሳብ የሚስማማው እዩኤል ደግሞ ቀላል ሀሳብ ማንሳት በቀላሉ የሰዎችን ቀልብ ሊገዛ ይችላል ሲል ያስረዳል።

“የምሠራው ቪዲዮ ዛሬም፣ ነገም፣ ከነገ ወዲያም ልሠራው የምችለው ነው ወይ?” የሚለው ጥያቄ ወሳኝ እንደሆነ ያነሳል።

ለአብነት እነሱን ውጤታማ ያደረጋቸውን የተሰበሰቡ ቪዲዮችን እያዩ በካሜራ ፊት ስሜትን መግለጽ (Reaction Video) አዋጪ እና ቀላል እንደሆነ ይጠቅሳሉ።

“ሪአክሽን ቨዲዮ አሠራሩ ቀላል እና የሚፈልገው አንድ ካሜራ ነው። ዩቲየብ ቀጣይነት ባለው ሁኔታ መሥራትን እንደሚጠይቅ ስለምናውቅ በሌሎች ሰዎች ይዘቶች ላይ መሥራት ብዙ ያሠራል” ይላሉ።

አክሎም “ሥራ መስሎ እንዲታየን አልፈለግንም። ስትጀምር ነገሮችን ራስህ ላይ ካከበድካቸው ዛሬም ነገም በተከታታይ መሥራት አትችልም” ብሏል።

ከሥራቸው በላይ ለጓደኝነታቸው የሚሰጡት ቦታ ሌላኛው የሥራቸው ስኬት እንደሆነም ይጠቅሳሉ።

ወጣቶቹ ይህንን አይነት ቪዲዮ ከመሥራታቸው አስቀድሞ መጣጥፎችን ማንብብ ጨምሮ ሌሎች ይዘቶችን ሞክረዋል።

ሆኖም ቀስ በቀስ ለእነሱ ባህሪይ ቅርብ ወደ ሆነው እና ወደ ቀላሉ ይዘት መቀየራቸውን ያስረዳሉ።

ለዚያ ነው እዩኤል “ዩቲየብ እራሱ እያስተማረህ ይሄዳል” የሚለው።

“የውጪ የሪአክሽን ቪዲዮዎች እመለከት ነበር። ጓደኛሞች በጋራ በእውነተኛ ስሜት ሲሠሩ አይ ነበር። ይሄንን ነገር ከሁለቱ ጓደኞቼ ጋር ብንሠራው የምር ሰው ይቀበለዋል ብዬ አሰብኩ። የመጀመሪያው ቪዲዮ [ምን ማድረግ እንዳለብን] ምንም ሳንነጋገር ነው መቅረጽ የጀመርነው። ሦስታችንም የራሳችንን ባህሪይ ይዘን ነበር የቀረብነው” ሲል የነበረውን ያስታውሳል።

ቪዲዮዎቹን ቀደም ብሎ በቴሌግራም አማካኝነት ከተከታዮቻቸው እንደሚያገኙትም አስረድተዋል

“ከሪአክሽን ቨዲዩ” በተጨማሪ ያለንን ዕውቀት ማጋራት፣ አንድ ነገሮች ከጅምሩ ጀምሮ እንዴት እንደሚሠሩ ማሳየት፣ የምንጠቀማቸው ምርቶች ላይ ምልከታ (review) መሥራት፣ የምግብ ዝግጅት፣ ጨዋታዎች፣ ጉዞ፣ የልጆች አስተዳደግ፣ የዕለት ውሎ እና መሰል ይዘቶች በቀላሉ ለዩቲብ የሚሠሩ ቪዲዮዎች ሊሆኑ ይችላሉ።

ዋናው ጉዳይ ግን ውጤታማ መሆን የሚቻለው “ሳናቋርጥ ልንሠራው እንደምንችል በራሳችን እምነት ሊኖረን ይገባል” ብለዋል።

እዩኤል፣ ፍራኦል እና ሽመልስ

የፎቶው ባለመብት, Eyuel

የምስሉ መግለጫ, እዩኤል፣ ፍራኦል እና ሽመልስ

ዩቲዩብ መቼ መክፈል ይጀምራል?

“የዩቲየብ ዕይታ አዲስ ቻናል ላይ በጣም ቀስ ብሎ ነው የሚመጣው። እንደ ቲክቶክ በአንድ ጊዜ የሚነሳ አይደለም” የሚለው እዩኤል የሰዎች አስተያየት ዕይታ እና ገንዘብ የሚመጣው ምን አልባት ከበርካታ ቪዲዮዎች በኋላ እንደሆነ ይናገራል።

የአውራ ቻናል ባለቤቶች ሥራውን ሲጀምሩ እምነት ነበራቸው። ለዚያ ነው እዩኤል የቀደመ ሥራውን ትቶ ቢያንስ በስምንት ወራት ውስጥ ዩቲዩብ ገንዘብ እንዲሚያመጣ አቅዶ ከጓደኞቹ ጋር መሥራት የጀመረው።

ሆኖም ካቀደው ጊዜ ስድስት ወራት ቀድሞ ሥራውን በጀመረ በሁለተኛው ወር ገንዘብ ማግኘት ጀመረ።

“ዩቲዩብ ቪዲዮ ይፈልጋል። ጥሩ ብር ሠርተህ በተከታታይ ቪዲዮ ካልጫንክ [በቀጣዩ ጊዜ] በጣም ነው የሚወርደው። ብዙ ገንዘብ መሥራት ከፈለክ ቶሎ ቶሎ መልቀቅ ይገባል። ድንገት ብትቀንስ ደግሞ ዜሮ ይገባል። ይሄ ሁኔታ ብዙ ሰውን ተስፋ ሊያስቆርጥ ይችላል። በተከታታይ ከሠራህ ግን ዩቲዩብ በጣም አሪፍ [የገንዘብ] ምንጭ ነው” ብሏል።

ዩቲዩብ ቀደም ብሎ ክፍያ ለማግኘት ቢያንስ አንድ ሺህ ተከታዮች (ሰብስክራይበሮች) እና የ4 ሺህ ሰዓት ዕይታን (watch hour) በመስፈርትነት አስቀምጦ ነበር።

አሁን ይህንን ዝቅ አድርጎ ተከፋይ ለመሆን 500 ተከታዮች እና የ3 ሺህ ሰዓታት ዕይታን ወይም በአጫጭር ቪዲዮ (ዩቲዩብ ሾርት) 3 ሚሊዮን ዕይታ ማግኘት ይበቃል።

ከዚያም በኋላ ቪዲዮዎቹ እንደታዩበት አገር፣ እንደተላለፈባቸው ማስታወቂያ እና እንደ ቪዲዮው ርዝመት እና ሰዎች እንዳሳለፉት ጊዜ ደንብ እና መመሪያዎች ከግምት ውስጥ ገብተው ገንዘብ ይከፍላል።

ይህ ለሁሉም ክፍት የሆነ አሠራር ነው። በትጋት ያለማቆራረጥ ለሚሠሩ ደግሞ ክፍያው ሕይወትን የሚቀይር ነው።