ስለልጆች አስተዳደግ በዩቲዩብ በመምከር ታዋቂ የሆነችው አሜሪካዊት ልጇቿን በማሰቃየት ተፈረደባት

የፎቶው ባለመብት, @MOMS_OF_TRUTH
ወላጆች ልጆቻቸው ሥርዓት ለማስተማር አስከፊ አያያዝን እንዲከተሉ በዩቲዩብ በመምከር ታዋቂ ለመሆን የበቃችው አሜሪካዊቷ የዩታህ ግዛት እናት ልጆቿን በማሰቃየት ተከሳ የዓመታት እስር ተፈረደባት።
ልጆቿን በማስራብ እና በማሰቃየት ጥፋት መፈጸሟን ለፍርድ ቤቱ ያመነችው እናት ሩቢ ፍራንክ፣ የእስር ቅጣት ሲበይንባት እያለቀሰች ችሎቱ ይቅርታ እንዲያደርግላት ጠይቃለች።
እናትየው ክስ ተመስርቶባት እስር የተፈረደባት ከቀድሞ የሥራ ሸሪኳ ጋር ነው። በዚህም ሁለቱም ተመሳሳይ የእስር ቅጣት ተላልፎባቸዋል።
በዚህም በቀረበባቸው የተለያዩ ክሶች በተናጠል ከአንድ አስከ 15 ዓመታት የሚደርስ እስር በእያንዳንዳቸው ላይ ተፈርዷል። የእስር ቅጣቶቹንም በተከታታይ የሚፈጽሙ ሲሆን፣ የግዛቲቱ የይቅርታ ቦርድ የመጨረሻውን ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ በእስር ላይ ይቆያሉ።
የዩታህ ግዛት ዐቃቤ ሕግ ለችሎቱ እንደተናገረው ፍራንክ የ9 እና የ11 ዓመት ልጇቿን “የማጎሪያ ስፍራ በሚመስል ሁኔታ ውስጥ ነበር የያዘቻቸው” በማለት ተከሳሿን ለማኅበረሰቡ ስጋት ናት ሲል ገልጿታል።
“ልጆቿ በመደበኛ ሁኔታ ምግብ፣ ውሃ፣ የሚተኙበት የመኝታ ቦታ እና የመዝናኛም ሆነ የመጫወቻ ዕድል ተነፍገው ቆይተዋል” በማለት እናት በልጇቿ ላይ የፈጸመችውን በደል አመልክቷል።
ፍርድ ቤት ውስጥ ብይን ከተሰጠ በኋላ አምርራ ያለቀሰቸው ፍራንክ “ፈጽሞ አቅጣጫዬን ስቼ ነበር፤ ጨለማውን ብርሃን፣ ብርሃኑን ጨለማ አድርጌ ነበር የማምነው” በማለት ይቅርታ እንዲደረግላት ጠይቃለች።
ሁለቱ ሴቶች የተያዙት ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ በምግብ እጥረት የተጎዳው ትልቁ የፍራንክ ልጅ ከቤቱ በመስኮት በኩል ሾልኮ ከወጣ በኋላ ነበር። ፖሊስ እንዳለው ልጁ ወደ ጎረቤት በመሄድ ምግብ እና ውሃ ጠይቋል። በገመድ ታስሮ ስለነበረም በቆዳው ላይ ሰንበር እና ቁስለት ነበረው።

የፎቶው ባለመብት, CONNEXIONS YOUTUBE CHANNEL
ፍራንክ በቁጥጥር ስር ስትውል አወዛጋቢ የነበረው የዩቲዩብ ታዋቂነቷም አብሮ አክትሟል። ከስምንት ዓመታት በፊት የከፈተችው የዩቲዩብ ቻናሏ ከሁለት ሚሊዮን በላይ አባላት ነበሩት።
ከልጇቿ ጋር በቤቷ ውስጥ እና በጊቢዋ የተለያዩ የቤት ውስጥ ተግባራትን ስታከናውን እና ምክር ስትሰጥ በቪዲዮዎቿ ላይ የምትታየው ፍራንክ ታዋቂነትን አትርፋ ነበር።
ነገር ግን ከሦስት ዓመት በፊት ከልጆቿ አንዱ ጆንያ ውስጥ ለሰባት ወራት እንዲተኛ መደረጉን ከተናገረ በኋላ በአድናቂዎቿ ዘንድ ጥርጣሬ ተፈጥሮ ነበር።
ከዚህ በኋላም የዩቲዩብ ተመልካቾቿ ቀደም ሲል የሠራቻቸውን ቪዲዮዎች ወደ ኋላ ተመልሰው በሚመረምሩበት ጊዜ ሌሎችም የሚረብሹ ሁኔታዎችን ለመመልከት ችለዋል።
ልጆቿን ምግብ መከልከል፣ የአሻንጉሊቶቻቸውን ጭንቅላት እንደምትቆርጥ ማስፈራራት እና እንደቅጣት የገና በዓልን እንዳያከብሩ መከልከልን የመሳሰሉት ድርጊቶቿ ተከታዮቿን አስደንግጧል።
የዩታህ ግዛት የልጆች ጥበቃ ተቋም በፍራንክ ላይ ምርመራ እንዲያካሂድ በሺዎች የሚቆጠሩ ፊርማቸውን ሰብስበው ቢያቀርቡም በጊዜው ምንም ሕጋዊ እርምጃ ሳይወሰድ ቀርቷል። ፍራንክ እና ባለቤቷም ሰዎች የቪዲዮዎቹን ይዘት ከአውድ ውጪ ተወስደዋል በሚል የቀረበውን ክስ አጣጥለውታል።
ነገር ግን ፍራንክ ከባሏ ጋር በተፋታችበት በአውሮፓውያኑ 2022 የዩቲዩብ ቻናሏ ተከታዮች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ማሽቆልቆል ጀምሮ ነበር። ከዚያም አሁን አብራት ከተከሰሰችው ጓደኛዋ ጋር በመሆን ቪዲዮዎችን ስታቀርብ ነበር።
በዚህ ወቅት ከካሜራ የራቁት የፍራንክ ልጆች በቤታቸው ውስጥ በእናታቸው አማካይነት መታሰር፣ መደንደብ፣ ምግብ መከልከል፣ በግድ ሥራ እንዲሰሩ ማድረግ እና ሌሎችም ከባድ በደሎች ሲፈጸምባቸው እንደቆየ የፖሊስ መዝገብ አመልክቷል።
እናት በልጆቿ ላይ ያደረገቻቸውን በደሎች በሙሉ መፈጸሟን ለፍርድ ቤቱ ያመለች ሲሆን፣ የልጆቿ አባትም በህጻናቱ ላይ ለፈጸመችው “ኢሰብአዊ ዘግናኝ” ድርጊት ከፍተኛው ቅጣት እንዲፈረድባት በጠበቃው አማካይነት ጠይቆ ነበር።












