ትራምፕ ባለፈው ዓመት ጥፋተኛ የተባሉበትን ወንጀል ለመቀልበስ አቤቱታ አቀረቡ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በ2024 የአፍ ማዘጊያ ገንዘብ በመክፈል በወንጀል ጥፋተኛ የተባሉበትን ወንጀል ፕሬዝዳንታዊ ያለመከሰስ መብታቸውን በማንሳት ይግባኝ ብለዋል።
ትራምፕ በኒው ዮርክ ፍርድ ቤት በቀርበ በንግድ መዝገቦች ማጭበርበር በ34 የተለያዩ ወንጀሎች ጥፋተኛ ተብለዋል።
ባለፈው ታኅሳስ ትራምፕ ወደ ዋይት ሐውስ የማይቀረው ጉዞ ጫፍ ላይ ሲደርሱ የኒው ዮርክ ፍርድ ቤት ዳኛ እስር ወይም የገንዘብ ቅጣት ያልጣለ የጥፋተኝነት ብይን በይነዋል።
የትራምፕ ጠበቆች አቤቱታውን ሲያቀርቡ "መዝገቡ እንኳንስ ለብይን የሚደርስ የችሎቱን ክፍል መርገጥ የነበረበት አይደለም" ብለዋል።
ጠበቆቹ መዝገቡን "በአገራችን ታሪክ በፖለቲካ የተገፋፋ ትልቁ ክስ" ሲሉም ገልፀውታል።
ትራምፕን የከሰሰው የማንሀተን ፍርድ ቤት አስተያየት እንዲሰጥ ለቀረበለት ጥያቄ ወዲያው ምላሽ አልሰጠም።
ዓቃቢያነ ሕግ ከ2016ቱ ምርጫ ጥቂት ቀናት አስቀድሞ ትራምፕ ማይክል ኮኸን የተባሉትን የግል ጠበቃቸውን የወሲብ ፊልም ሰሪ ለሆነችው ስቶርሚ ዳንኤልስ ከፕሬዝዳንቱ ጋር ስለነበራት ወሲባዊ ግንኙነት እንዳታወራ 130 ሺህ ዶላር እንዲከፍሏቸው ማዘዛቸውን ተናግረዋል።
ክፍያው ወንጀል አለመሆኑን የገለፁት ዓቃቢያን ሕግ ትራምፕ ኮኸን የከፈሉት ገንዘብ ሲመልሱ እውነተኛ ዓላማውን በመሸፈን የሕግ አገልግሎት ክፍያ አድርገው መክፈላቸውን ገልፀዋል።
የ2024ቱ ክስ በትራምፕ የምረጡኝ ዘመቻ ላይ ጥላ እንዲያጠላ ያደረገ ነበር።
በችሎቱ ወቅት ዓቃቢያነ ሕግ ክፍያውን ሐሰተኛ ስም በመስጠት መሸፈኑ መራጮች የስቶርሚ ዳንኤልስን አቤቱታ እንዳይሰሙ በማድረጉ እንደ ምርጫ ጣልቃ ገብነት ይቆጠራል ብለዋል።
ትራምፕ የቀረበባቸውን ክስ ምንም ጥፋት አልሰራሁም በሚል ውድቅ አድርገውታል።
ሆኖም ትራምፕ በ34 የንግድ መዝገብ በማጭበርበር ክሶች ጥፋተኛ የተባሉ ሲሆን፤ ይህም በአገሪቱ ታሪክ የቀድሞ ወይም በሥልጣን ላይ ያሉ ወንጀለኛ የተባሉ ፕሬዝዳንት አድርጓቸዋል።
ብይኑ ከተሰጠ ከአንድ ወር በኋላ የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች በሥልጣን ዘመናቸው ለሚወስኗቸው ውሳኔዎች በወንጀል እንዳይከሰሱ የሚያደርግ ሰፊ ያለመከሰስ ሽፋን እንዳላቸው ወስኗል።
የትራምፕ ጠበቆች ይህን ብይን መሠረት አድርገው እና ከትራምፕ ፕሬዝዳንትነት ዘመን የመነጩ ማስረጃዎች እንዳይቀርቡ ቢጠይቁም ፍርድ ቤቱ መከራከሪያውን ውድቅ አድርጎታል።
ጠበቆቹ ባቀረቡት አቤቱታ ትራምፕ ሕግን የጣሱ ባለመሆናቸው ብይኑ ውድቅ እንዲደረግ እንደሚሹ አስረድተዋል።
ባለፈው ሐምሌ አቤቱታ የቀረበለት ፍርድ ቤት በፍትሐ ብሔር ትራምፕ ላይ የተመሰረተባቸው የ500 ሚሊዮን ዶላር ክስ ውድቅ አድርጓል።















