ትራምፕ በተባበሩት መንግሥታት ጉባዔ ላይ 'ደባ ተፈፅሞብኛል' በማለት ምርመራ እንዲጀመር ጠየቁ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዶናልድ ትራምፕ ረቡዕ ዕለት በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ንግግር ሊያደርጉ በሄዱበት ወቅት "ሶስት ጊዜ ደባ እንደተፈጸመባቸው" በመግለጽ ድርጅቱ ጉዳዩን እንዲመረምር ጠየቁ።
በማኅበራዊ ሚድያቸው መልዕክታቸውን ያሰሙት የአሜሪካው ፕሬዝደንት ከቀዳማዊ እመቤት ሜላኒያ ትራምፕ ጋር አሳንሰር (ኤስካሌተር) ሊጠቀሙ ሲሉ ማሽኑ መበላሸቱን አውስተዋል።
አክለው ንግግር ሊያደርጉ ሲዘጋጁ ፅሑፍ የሚያሳየው ማሽን (ቴሌፕሮምፕተር) እና የድምፅ መቆራረጥ እንደነበር ጠቅሰው "ሶስት ጊዜ ደባ ተፈፅሞብኛል" ብለዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ባለሥልጣን ድምፅ ማጉያው የቀነሰው አንዳንድ ግለሰቦች በትርጉም እንዲሰሙት ለማስቻል ነው ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ቀደም ብሎ በሰጠው ምላሽ አሳንሰሩ የተባለሸው የትራምፕ ቪድዮን የሚያነሳ ግለሰብ ወደኋላ በመውጣቱ ማሽኑ ሳይቆም እንዳልቆረ ጠቁሞ ቴሌፕሮምፕተሩ ደግሞ የአሜሪካ ልዑካን ይዘው የመጡት ነው ብሏል።
ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ገፃቸው ሁኔታውን የተቹት ሲሆን ለተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ምርመራ እንዲካሄድ የሚጠይቅ ደብዳቤ እንደሚልኩ አስታውቀዋል።
"ትናንት በተባበሩት መንግሥታት የሆነው በጣም አሳፋሪ ነው። አንድ ብቻ አሊያም ሁለት ብቻ ሳይሆን ሶስት ጊዜ ደባ ተፈፅሟል። ይህ በግጥጥሞሽ የሆነ አይደለም። ሶስት ጊዜ ነው ደባ የተፈፀመው። በራሳቸው ሊያፍሩ ይገባል።"
ፕሬዝደንቱ ኤስካሌተሩን ሲቆጣጠሩ የነበሩ ሰዎች በቁጥጥር ሥር እንዲውሉም ጠይቀዋል።
"ይህ ደባ ነው። በኤስካሌተሩ አካባቢ ያሉ የደኅንነት ካሜራዎች ሊታዩ ይገባል። ሲክሬት ሰርቪስ ሁኔታውን እየተከታተለው ነው" ብለዋል።
በተባበሩት መንግሥታት የአሜሪካ አምባሳደር የሆኑት ማይክ ዋልትዝ ሁኔታው "ተቀባይነት የለውም" በማለት ምርመራ ይካሄድ የሚለውን የትራምፕ ሐሳብ አንፀባርቀዋል።
"ዩናይትድ ስቴትስ መሰል የደኅንነት ስጋቶችን እና ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ክብር የሚነኩ ጉዳዮችን አትታገስም። ፈጣን የሆነ ምላሽ እንጠብቃለን" ሲሉ በኤክስ ገፃቸው ፅፈዋል።
ረቡዕ የዋይት ሐውስ ፕሬስ ሴክሬታሪ ካሮላይን ሌቪት አሳንሰሩ እንዲቆም የተደረገው ሆነ ተብሎ ነው ሲሉ ስጋታቸውን ገልፀዋል።
"ፕሬዝደንቱ እና ቀዳማዊ እመቤቷ ወደ አሳንሰሩ ሲወጡ ሆነ ተብሎ ከሆነ እንዲቆም የተደረገው በፍጥነት ምርመራ ሊደረግ ይገባል።"
ትራምፕ ወደ ተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዔ ዘልቀው ንግግር ሊያሰሙ ሲዘጋጁ ፅሑፍ የሚያሳየው ማሽን እንደማይሰራ ለተሰብሳቢዎች አሳውቀዋል።
"ይህን ቴሌፕሮምፕተር የሚያንቀሳቅስ ግለሰብ ትልቅ አደጋ ላይ ነው" በማለት ቀልድ ቢጤ ማስጠንቀቂያም አሰምተው ነበር።
አንድ የተባበሩት መንግሥታት ባለሥልጣን ለቢቢሲ እንደተናገሩት ቴሌምፕሮምፐተሩን ይዘው የመጡት የዋይት ሐውስ ልዑካን ናቸው።















