ከጋዳፊ ገንዘብ በመቀበል የተከሰሱት የቀድሞው የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ዘብጥያ ወረዱ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ለምርጫ ቅስቀሳ ከቀድሞው የሊቢያ አምባገነኑ መሪ ሙአመር ጋዳፊ ገንዘብ ተቀብለዋል በሚል የአምስት ዓመት እስር የተፈረደባቸው የቀድሞው የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ሳርኮዚ ዘብጥያ ወረዱ።
ሳርኮዚ እስር ቤት የገቡ የመጀመሪያው የቀድሞ የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ሆነዋል።
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የናዚ ተባባሪ መሪ የነበሩት ፒሊፕ ፒቴን በአገር ክህደት ወንጀል በ1945 ታስረው የነበረ ሲሆን፣ ከዚያን ጊዜ በኋላ ግን እስር ቤት የገባ የፈረንሳይ የቀድሞ መሪ የለም።
ሳርኮዚ በአውሮፓውያኑ በ2007 ለፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ዘመቻ ከጋዳፊ ገንዘብ ተቀብለዋል በሚል የቀረበባቸውን ክስ "ፖለቲካዊ ነው" በማለት ተከራክረዋል።
ሆኖም የአገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሳርኮዚ የቅርብ ረዳቶች የሆኑት ብሪስ ሆርቴፉክስ እና ክላውድ ጉዌንት የሊቢያ ባለሥልጣናትን በማነጋገር ለምርጫ ዘመቻቸው የገንዘብ ድጋፍ እንዲጠይቁ ፈቅደዋል በሚል እስር ቤት እንዲገቡ ብይን ሰጥቷል።
ሁለቱ ግለሰቦች በ2005 የፈረንሳይ እና ሊቢያ ዜግነት ባለው ዚያድ ቲያክዲን በተባለ ግለሰብ አማካኝነት በተዘጋጀ ስብሰባ ላይ ከጋዳፊ የደኅንነት ኃላፊ እና አማች ጋር ንግግር ነበራቸው ተብሏል።
ቲያክዲን፣ ሳርኮዚ ላይ ፍርዱ ከመተላለፉ አስቀድሞ ሕይታቸው አልፏል።
ፈረንሳይን ከአውሮፓውያኑ 2007 እስከ 2012 ድረስ የመሩት ሳርኮዚ፣ በላ ሳንቴ እስር ቤት ለአምስት ዓመታት እንዲያሳልፉ የተፈረደባቸው ሲሆን ይግባኝ ጠይቀዋል።
ሳርኮዚ ከወንጀሉ ንጹህ እንደሆኑ ቢያስቡም "ባሉት ማስረጃዎች አሳሳቢነት" ምክንያት ወደ ዘብጥያ እንዲወርዱ ተፈርዶባቸዋል።
ሳርኮዚ ፓሪስ 16ኛ ዲስትሪክት ከሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ከባለቤታቸውን ካርላ ብሩኒ ሳርኮዚ ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘው ሲወጡ ከ100 በላይ የሚቆጠሩ ሰዎች ስማቸውን ሲጠሯቸው ተሰምቷል።
የ28 ዓመቱ ልጃቸው ሉዊም ደጋፊዎቻቸው ድጋፋቸውን እንዲያሳዩዋቸው የጠየቀ ሲሆን፣ ሌላኛው ልጃቸው ፔሪ በበኩሉ የፍቅር መልዕክት እንዲያስተላልፉላቸው ጠይቋል።
የ70 ዓመቱ ኒኮላስ ሳርኮዚ፣ በሴን ወንዝ ደቡባዊ አቅጣጫ ሞንትፓርነስ ዲስትሪክት ወደሚገኘው እስር ቤት ሲወሰዱ መንገዶች በበርካታ ፖሊሶች ተከበው ነበር።
ሳርኮዚ ወደ እስር ቤት እየተወሰዱ በነበረበት ወቅት በኤክስ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ የሊቢያውያንን ገንዘብ ተጠቅመዋል በሚል በቀረበባቸው ክስ ጥፋተኛ አለመሆናቸውን ገልጸዋል።
"ምንም ጥርጥር የለኝም፣ እውነት ያሸንፋል" ብለዋል በጽሑፋቸው።
"በማይናወጥ ጥንካሬ ለፈረንሳይ ሕዝብ የምናገረው በዚህ ጠዋት እስር ቤት ውስጥ ያጎሩት የቀድሞ ፕሬዝዳንቱን አይደለም - ንጹህ ሰው እንጂ። ለእኔ አትዘኑ ምክንያቱም ባለቤቴ እና ልጆቼ ከጎኔ ናቸው። ሆኖም ዛሬ ጠዋት ለበቀል ሲባል ፈረንሳይ ስትዋረድ ሳይ መራር የሆነ ሐዘን ተሰምቶኛል" ብለዋል ሳርኮዚ።
ሳርኮዚ እስር ቤት ከገቡ በኋላ ጠበቃቸው ክሪስቶፍ ኢንግሬን የቀድሞው ፕሬዝዳንቱ እንዲለቀቁ ይግባኝ መጠየቃቸውን ገልጸዋል።
"ለእስራቸው ምክንያት የሚሆን ምንም ማስረጃ የለም" ያሉት ጠበቃቸው ኢንግሬን፣ "ሳርኮዚ ለሦስት ሳምንታት አሊያም ለወር ያህል እስር ቤት ሊቆዩ እንደሚችሉ" ተናግረዋል።
ሳርኮዚ በእስር ቤቱ ውስጥ አደገኛ እፅ አዘዋዋሪዎች አሊያም በሽብር ወንጀል የተፈረደባቸው እስረኞች ስለሚገኙ ለግል ደኅንነታቸው ሲባል የተለየ ክፍል ውስጥ እንዲገቡ ቢደረጉም፣ በእስር ቤት ቆይታቸው ምንም የተለየ እንክብካቤ እንደማይፈልጉ ተናግረዋል።
ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ሳርኮዚ በኢልይሴ ቤተ መንግሥት ከፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር ተገናኝተው ነበር።
ማክሮን ሰኞ ዕለት ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት "እንደ ሰው የቀድሞ መሪዎችን መቀበል የተለመደ ነው" ብለዋል።
የፍትሕ ሚኒስትር ጄራልድ ዳርማኒንም የሳርኮዚን ደኅንነት ለማረጋገጥ እና የእስር ቤቱን ሁኔታ የመከታተል ሚናቸውን ለመወጣት እንደሚጎበኟቸው ተናግረዋል።
ሳርኮዚ በ2012 በምርጫ ከተሸነፉ በኋላ ሳርኮዚ በተለያዩ ወንጀሎች ላይ እጃቸው አለበት በሚል ምርመራዎች ተደርጎባቸዋል።
በ2024 ለዳግም ምርጫ ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ በማውጣት እና ወንጀላቸውን ለመሸፈን የሕዝብ ግንኙነት ኩባንያ በመቅጠር ጥፋተኛ ከተባሉ በኋላ ይግባኝ ብለዋል።
በዚህ ክስ የአንድ ዓመት እስር ተፈርዶባቸው የነበረ ሲሆን በኋላ ላይ ስድስት ወር ተቀንሶላቸዋል።
በሚቀጥለው ወር መጨረሻ የፈረንሳይ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 'ቢግማሊዮን አፌርስ' በተባለ ሕገ ወጥ የገንዘብ ዘመቻ ምክንያት በተፈረደባቸው የስድስት ወር እስር ላይ ላቀረቡት ይግባኝ ብይን ይሰጣል።
ሳርኮዚ ዛሬ ጠዋት እስር ቤት ከመድረሳቸው በፊት ለበርካታ መገናኛ ብዙኃን ቃለ መጠይቅ ሰጥተዋል።
'ላ ትሪቡን' ለተባለ ጋዜጣ " እስር ቤት አልፈራም። በእስር ቤት መግቢያም ላይ ቢሆን አንገቴን ቀና አድርጌ ነው የምሄደው" ብለው ነበር።
ሳርኮዚ ወደ እስር ቤት ሁለት መጽሐፎችን ይዘው እንደሚገቡም የተናገሩ ሲሆን፣አንደኛው በጂን ክርስቲያን ፒቲትፊልስ የተፃፈው 'ኤ ላይፍ ኦፍ ጂሰስ' ሲሆን ሌላኛ በሐሰት እስር ቤት የገባ እና ከእስር ያመለጠ ግለሰብ ታሪክ ላይ የሚያጠነጥነው በአሌክስአንደር ዱማስ የተፃፈው 'ዘ ካውንት ኦፍ ሞንቴ ክሪስቶ' ነው።















