በፓሪስ ጎብኚዎች ከሚያዘወትሩት ሙዚየም "በዋጋ የማይተመኑ" የተባሉ በእንቁዎች ያጌጡ ቅርሶች ተሰረቁ

ከተሰረቁት ጌጣ ጌጦች መካከል በኤመራልድ ያጌጠ የአንገት ሀብል እንዲሁም የናፖሊዮን ቦናፓርቴ ሁለተኛ ሚስት የንግሥት ማሬ ሉዊዝ ጆሮ ጌጦች ይገኙበታል

የፎቶው ባለመብት, Frederic SOULOY/Gamma-Rapho via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ከተሰረቁት ጌጣ ጌጦች መካከል በኤመራልድ ያጌጠ የአንገት ሀብል እንዲሁም የናፖሊዮን ቦናፓርቴ ሁለተኛ ሚስት የንግሥት ማሬ ሉዊዝ ጆሮ ጌጦች ይገኙበታል

ትናንት ማለዳ በፓሪስ ሉቨር ሙዚየም በዋጋ የማይተመኑ የተባሉ ጌጣ ጌጦች ተሰረቁ። የፓሪስ ፖሊስ የሌቦቹን ቡድን ለመያዝ አሰሳ እያደረገ መሆኑ ገልጿል።

የፈረንሳይ አገር ውስጥ ሚኒስትር ላውረንት ኑኔዝ እሁድ ዕለት ማለዳ ሙዚየሙ ለጎብኚዎች ክፍት በሆነ በደቂቃ ውስጥ ጭምብል ያጠለቁ ተጠርጣሪዎች ዘረፋውን ለመፈጸም ደቂቃዎች ብቻ እንደፈጀባቸው ተናግረዋል።

የዘራፊዎቹ ቡድን የሙዚየሙ የመጀመሪያ ፎቅ መስኮት ላይ ለመድረስ ከመኪና ላይ የተዘረጋ መሰላል መጠቀማቸው የተገለፀ ሲሆን፣ ጌጣጌጦቹን ለዕይታ ከተቀመጡበት ሰብረው በማውጣት በአነስተኛ ሞተር ሳይክል አምልጠዋል።

በዘራፊዎቹ የተወሰዱት ጌጣጌጦች የፈረንሳይ ንጉሣውያን ቤተሰቦች ይገለገሉባቸው የነበሩ ናቸው። ባለሥልጣናት ዘጠኝ ጌጣጌጦች መወሰዳቸውን ጨምረው አስታውቀዋል።

የናፖሊዮን ሦስተኛ ባለቤት ዘውድ በአካባቢው ወድቆ መገኘቱንም ጨምረው ተናግረዋል።

እሁድ ዕለት ዘረፋው ከተፈጸመ በኋላ ሉቨር ሙዚየም ለጎብኚዎች ዝግ እንዲሆን ተደርጓል።

ጌጣ ጌጦቹ የተሰረቁት ጋሌሪያ ዲ አፖሎን ከሚባለው ክፍል ማለዳ 3፡30 ላይ መሆኑን የፈረንሳይ አገር ውስጥ ሚኒስቴር አስታውቋል።

ሌቦቹ ወደ ሕንጻው ለመግባት በባትሪ የሚሰራ መቁረጫ መጠቀማቸውን የፓሪስ አቃቤ ሕግ ለቢቢሲ ተናግሯል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አራት ሰዎች በዘረፋው ላይ የተሳተፉ ሲሆን ሁለቱ ወደ ሕንጻው ከገቡ በኋላ ጠባቂዎችን እንዳስፈራርዋቸው ጨምረው ገልፀዋል።

መሰላል የጫነ መኪና ወደ ሕንጻው የመጀመሪያ ፎቅ መስኮት በመጠጋት መሰላሉን መዘርጋቱን ተገልጿል።

የፈረንሳይ የባሕል ሚኒስቴር የዘራፊ ቡድኖቾ ከመሄዳቸው በፊት መኪናውን በእሳት ለማያያዝ ሞክረው የነበረ ቢሆንም የሙዚየሙ ሠራተኞች ይህንን ማድረግ እንዳይችሉ ተከላክለዋል።

በዘረፋው ወቅት የተጎዳ አንድም ሰው የለም

ከጋለሪው ዘጠኝ ጌጣ ጌጦች የተሰረቁ ሲሆን ሁሉም በ19ኛው ክፍለ ዘመን የፈረንሳይ ንጉሣዊ ቤተሰቦች ይገለገሉባቸው የነበሩ ናቸው ተብሏል።

ጌጣጌጦቹ በሺህዎች በሚቆጠሩ እንቁዎች እና ሌላ ውድ ማዕድናት የተንቆጠቆጡ ነበሩ።

ከተዘረፉት የፀጉር እና የጆሮ ጌጦች መካከል የናፖሊዮን ሦስተኛ ባለቤት ንግሥት ዩጂን ትገለገልባቸው የነበሩ ይገኙበታል።

የንግሥት ዩጂን ዘውድን ዘራፊዎቹ በሚያመልጡበት ወቅት ጥለውት ተገኝቷል።

በተለያዩ የከበሩ ማዕድናት የተዋበው ይህ ዘውድ በ1354 እንቁዎች እና 56 ኤመራልዶች የተጌጠ መሆኑ በሎቭሬ ድረ ገጽ ላይ ሰፍሯል።

መርማሪዎች ዘውዱ ላይ የደረሰበትን ጉዳት ምርመራ እያደረጉ ነው።

ወንጀለኞቹ ጌጣ ጌጦቹን መስረቅ የመረጡት በቀላሉ በታትኖ ለመሸጥ ስለሚመች ነው ተብሏል።

ነገር ግን እንደዚህ በከበሩ ማዕድናት የተዋቡ ጌጣ ጌጦችን ሙሉ በሙሉ ለመሸጥ መሞከር በቀላሉ ስለሚታወቅ ሊያጋልጣቸው ይችላል።

ኑኔዝ የተሰረቁት ጌጣ ጌጦች በገንዘብ ከሚያወጡት ዋጋ በተጨማሪ ባሕላዊ እና ታሪካዊ ዋጋቸው "በገንዘብ የማይሰላ" እንዲሁም " የማይተመን ቅርስ" ናቸው ብለዋል።

በዓለም በከፍተኛ ሁኔታ ከሚጎበኙ ሙዚየሞች መካከል አንዱ ወደ ሆነው ወደዚህ ስፍራ እሁድ ዕለት ፖሊስ ጎብኚዎች እንዳይገቡ የከለከለ ሲሆን ለምርምራ ዝግ እንዲሆን አድርጓል።

አሜሪካዊ ጎብኚዎች ጂም እና ጆአን ካርፔንተር የሙዚየሙ ጠባቂዎች "ከጋለሪው ሲያስወጡን" የሊዮናርዶ ዳ ቪንቺን ሞና ሊሳን ልናይ ነበር ብለዋል።

ጥንዶቹ ለሮይተርስ የዜና ወኪል ዘረፋ በተፈጸመበት በጋሌሪያ ዲ አፖሎን በኩል አልፈው በድንገተኛ አደጋ መውጫ በኩል እንዲወጡ መደረጋቸውን ተናግረዋል።

ካርፔንተር በሙዚየሙ ውስጥ "ብዙ ግራ መጋባት ነበር" ያለ ሲሆን ምን አንደተፈጠረ ጥበቃዎቹን ሲጠይቁ "የቴክኒክ ችግር እንደገጠማቸው" እንደነገሯቸው አብራርቷል።

"የሆነ ነገር እንደተፈጠረ ገብቶኛል ምክንያቱም በሙዚየሙ ውስጥ የሚገኘውን ሁሉ ነበር እያስወጡ የነበረው" ሲል ካርፔንተር አክሏል።