40ሺህ የተሰረቁ ስልኮችን ወደ ቻይና በማዘዋወር የተጠረጠረው የወንጀል ቡድን እንዴት ተደረሰበት?

ከዩናይትድ ኪንግደም ወደ ቻይና የተሰረቁ ስልኮችን የሚያዘዋውር ዓለም አቀፍ የወንጀል ቡድን እንደተደረሰበት ፖሊስ አስታውቋል።
ወደ 40,000 የተሰረቁ ስልኮችን በማዘዋወር ቡድኑ ይጠረጠራል። በዩኬ ከስልክ ስርቆት ጋር በተያያዘ ትልቁ ኦፕሬሽን ነው ተብሏል።
18 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ሲውሉ 2,000 የተሰረቁ ስልኮችም ተይዘዋል።
ከተሰረቁት ስልኮች ግማሹ የተዘረፉት ከለንደን ነው ተብሏል።
ፖሊስ ኦፕሬሽኑን ያካሄደው በለንደን እና ኸርትፎርሼር ከተሞች ነው።
አንድ ስልካቸው የተሰረቀባቸው ግለሰብ ስልካቸው የት እንደደረሰ ተከታትለው ከደረሱበት በኋላ ነበር ምርመራው የተጀመረው።
"በገና በዓል ዋዜማ ስልካቸውን በኤሌክትሮኒክ መሣሪያ ታግዘው ተከታትለው ሂትሮው አውሮፕላን ማረፊያ መድረሱን አወቁ። ስልካቸው ከሌሎች 894 ስልኮች ጋር ታሽጎ ተገኘ" ሲሉ መርማሪ ማርክ ጋቪን ገልጸዋል።
የተሰረቁት ስልኮች ወደ ሆንግ ኮንግ እየተወሰዱ ነበር። ስልኮቹ ከተቀመጡባቸው ካርቶኖች አሻራ በመውሰድ ምርመራ ከተደረገ በኋላ ሁለት ግለሰቦች ተለይተዋል።
ፖሊስ ባደረገው ክትትል ከሁለቱ ግለሰቦች የአንዱ መኪና ውስጥ በፎይል የተጠቀለሉ ስልኮች ተይዘዋል።
የተሰረቁ ስልኮችን ለማሳለፍ በፎይል መጠቅለል የተለመደ ነው።
በ30ዎቹ ዕድሜ ክልል የሚገኙት የአፍጋኒስታን ዜጎች የተሰረቀ ስልክ ለመቀበል በመመሳጠርና የተሰረቀ ንብረትን በመደበቅ ተከሰዋል።
መኪናቸው በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ሲውል በርካታ የተሰረቁ ስልኮች ተገኝተዋል።
ሌላ የ29 ዓመት ሕንዳዊም በተመሳሳይ ወንጀል ተከሷል።
መርማሪው "ስልኮቹ ወዴት እንደሚወሰዱ ስናውቅ ዓለም አቀፍ የወንጀል ቡድን መሆኑ ታወቀ። በለንደን ከሚሰረቁ ስልኮች 40% የሚዘዋወረው በእነሱ በኩል ነው" ብለዋል።
ከዝርፊያ፣ የተሰረቀ ንብረትን ከመያዝና ከመስረቅ ከመመሳጠር ጋር በተያያዘ ተጨማሪ 15 ሰዎች ታስረዋል።
ከተጠርጣሪዎቹ አንዷ የቡልጋርያ ዜጋ የሆነች ሴት ናት።
ኦፕሬሽኑ ሲጀመር 30 ስልኮች ብቻ ነበሩ የተያዙት።
ባለፉት አራት ዓመታት በለንደን የተሰረቁ ስልኮች በአራት እጥፍ ጨምረዋል። በ2020 ቁጥሩ 28,609 ሲደርስ በ2024 ደግሞ 80,588 ደርሷል።
በየዓመቱ 20 ሚሊዮን ሰዎች ለንደንን ይጎበኛሉ። ዌስት ኢንድ እና ዌስትሚኒስተር ስልክ በብዛት የሚመነተፍባቸው ቦታዎች ናቸው።
በዩኬ እና በሌሎችም አገራት ያገለገሉ ስልኮች ተፈላጊነታቸው መጨመሩ ዝርፊያው እንዲባባስ አድርጓል።
የፖሊስ ኃላፊው ሳራ ጆንስ "አደገኛ ዕፅ አዘዋዋሪዎች ወደ ስልክ ስርቆት ፊታቸውን አዙረዋል። የተሻለ አዋጭ ሆኖ አግኝተውታል። አንድ ስልክ መቶ ፓውንድ ገደማ ያስገኛል" ብለዋል።
የአፕል ስልኮች የበለጠ ትርፋማ ስለሚያደርጉ ዘራፊዎቹ አይፎን ላይ ያተኩራሉ።
ሌቦች በእያንዳንዱ ስልክ እስከ 300 ፓውንድ እንደሚከፈላቸው የፖሊስ መረጃ ያሳያል። ስልኮቹ በቻይና እስከ 4,000 ፓውንድ ይሸጣሉ።
የስልክ ምዝበራን ለመከላከል የተቋቋመው የፖሊስ ክፍል ኃላፊ ኮማንደር አንድሪው ፊትርስቶን "በዩኬ ታሪክ ትልቁ ፀረ የስልክ ምዝበራ ኦፕሬሽን ተከናውኗል። ጎዳና ላይ ካሉት ዘራፊዎች አንስቶ የስልክ ስርቆት ሰንሰለቱን ሰብረናል" ብለዋል።
በየዓመቱ የወንጀል ቡድኑ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ የተሰረቁ ስልኮችን ያዘዋውራል።
ስልካቸው የተሰረቀባቸው ሰዎች ፖሊስ እምብዛም እንዳልረዳቸው በመግለጽ ያማርራሉ።
አፕል ስልኮችን የሚከታተል 'ፋይንድ ማይ ፎን' የተባለ መተግበሪያ ስላለቸው ስልካቸው የተሰረቀባቸው ሰዎች ስልካቸው ወዴት እንደተወሰደ ይከታተላሉ።
ይህንን መረጃ ለፖሊስ ቢሰጡም ክትትል ተደርጎ ስልካቸው አለመገኘቱን ሲገልጹም ይደመጣል።















