ኪሊያን ምባፔ በስዊድን ቀርቦበታል የተባለው የመድፈር ክስ ውድቅ ተደረገ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የስዊድን አቃቤ ሕግ ከፈረንሳዊው እግር ኳስ ተጫዋች ጋር የተያያዘ ነው የተባለውን የመድፈር ክስ ውድቅ ማድረጉ ተሰምቷል። የስዊድን መገናኛ ብዙኃን ናቸው ጉዳዩ ከምባፔ ጋር የተያያዘ ነው ሲሉ ሲዘግቡ የቆዩት።
የስዊድን አቃቤ ሕግ ባለሥልጣን አባል የሆኑት ማሪና ቺራኮቫ ስቶክሆልም ውስጥ ተፈፅሟል የተባለው የመድፈር ወንጀል በማስረጃ እጥረት ምክንያት መዘጋቱን አስታውቀዋል።
በዓለማችን አሉ ከሚባሉ ቁንጮ እግር ኳስ ተጫዋቾች አንዱ የሆነው የሪያል ማድሪዱ ኪሊያን ምባፔ በስዊድን አቃቤ ሕግ በይፋ ስሙ አልተጠቀሰም። የወንጀል ተጠርጣሪ ነው የሚል ክስም አልቀረበበትም።
ጉዳዩ ባለፈው ጥቅምት ሲናፈስ የምባፔ ጠበቃዎች ደንበኛቸው ስሙን ለማጥራት ዝግጁ መሆኑን ተናግረው ነበር። ምባፔ ከዚህ ቀደም ዘገባውን "ሐሰተኛ ዜና" ሲል ገልፆት ነበር።
የመጀመሪያውን ዙር ምርመራ የመሩት ነባሯ አቃቤ ሕግ ቺራኮቫ ያለው ማስረጃ "ወደፊት ለመጓዝ በቂ አይደለም፤ ስለዚህ ምርመራ ተዘግቷል" ብለዋል።
ፊጋሮ ጋዜጣ እንደዘገበው የእግር ኳስ ተጫዋቹ ጠበቃዎች በጉዳዩ ዙሪያ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።
የመድፈር ወንጀል እና ሁለት ፆታዊ ጥቃቶች በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 10 በስዊድን ዋና ከተማ መከሰታቸው ተዘግቦ ነበር።
አፍቶንብላዴት እና ኤክስፕሬሽን የተባሉ ጋዜጣዎች እንዲሁም ዋናው የሀገሪቱ ጣቢያ ኤስቪቲን ጨምሮ በርካታ የስዊድን ሚድያዎች ተጠርጣሪው ኪሊያን ምባፔ ነው ሲሉ ነበር የዘገቡት።
ምባፔ በወቅቱ በስዊድን ጉብኝት እያደረገ ነበር።
ፖሊስ ምባፔ በወቅቱ አርፎበት በነበረው ባንክ የተባለ ሆቴል ውስጥ የታየ ሲሆን የፖሊስ መኮንኖች ሻንጣዎች ይዘው ሲወጡ ታይተዋል። አንድ ዘገባ እንደጠቆመው ፖሊስ ለማስረጃ እንዲሆን ልብሶችን ነበር ከሆቴሉ ይዞ የወጣው።
ስሙ የተነሳበትን ጉዳይ በተለመከተ ለመጀመሪያ ጊዜ ክሊክ በተሰኘው የፈረንሳይ ጣቢያ ቀርቦ ሐሳቡን የሰጠው ምባፔ እሱ "እዚህ ውስጥ እንደሌለበት" ተናግሯል።
"ምንም የደረሰኝ ነገር የለም። በጉዳዩ አልተጠራሁም. . . እኔ እዚህ ውስጥ የለሁበትም።"
የተጫዋቹ ጠበቃዎች ከዚህ ቀደም የስዊድን መገናኛ ብዙኃንን በስም ማጥፋት የወቀሱ ሲሆን ስለክሱ ምንም የሚያውቁት ነገር እንደሌላ ተናግረዋል።
"[ምፓቤ] ብቻውን ሆኖ አያውቅም። እንዲህ ያለ አደጋ ውስጥ ሊያስገባው የሚችለው ነገር ውስጥ ገብቶ አያውቅም" ሲሉ ማሪ-አሊክስ ካኑ-በርናርድ ተናግረው ነበር።
የሪያል ማድሪድ የፊት መስመር ተጫዋች በዚህ ሳምንት 50ኛ የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ጎሉን አስቆጥሯል። ተጫዋቹ ባለፈው ክረምት ነው ከፈረንሳዩ ፓሪ ሳን-ዠርማ ወደ ማድሪድ የተዛወረው።
በአውሮፓውያኑ 2018 በሩሲያ የተካሄደውን የዓለም ዋንጫ ያነሳው ምባፔ በካታሩ 2022 ዓለም ዋንጫ ፍፃሜ ሶስት ጎል አስቆጥሮ ሀት-ትሪክ መሥራቱ ይታወሳል። በጨዋታው ፈረንሳይ በአርጀንቲና ተሸንፋለች።












