ኔቶ በጦርነት ወቅት ወዳለ አስተሳሰብ ሊመጣ እንደሚገባ ዋና ጸሐፊው አስጠነቀቁ

ማርክ ሩት

የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ራሱን በጦርነት ወቅት ወዳለ አስተሳሰብ ማሸጋገር እንደሚገባው ዋና ጸሐፊው አስጠነቀቁ።

የወታደራዊ ኅብረት አባላቱ አገራት ከሩሲያ ጋር ለወደፊቱ ሊፈጠር ለሚችለው ጦርነት በበቂው እየተዘጋጁ አይደለም ሲሉ ነው ዋና ጸሐፊው ማርክ ሩት የተቹት።

ማርክ ሩት ሩሲያ "ከዪክሬን እንዲሁም ከኛ ጋር ለረጅም ጊዜ ጦርነት እየተዘጋጀች ነው" ሲሉ የወቅቱን የጸጥታ ሁኔታ በህይወት ዘመናቸው እጅግ የከፋ ነው ብለውታል።

"በመጪው አራት፣ አምስት ዓመት ለሚመጣብን ነገር ዝግጁ አይደለንም" በማለት በጥቅምት ወር የዋና ጸሐፊነትን ኃላፊነት የተረከቡት ማርክ ሩት አጽንኦት ሰጥተዋል።

አባል አገራት የመከላከያ ወጪያቸውን ሊያሳድጉ እና ሊያጠናክሩ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።

ዋና ጸሐፊው ይህንን የተናገሩት ከዚህ ቀደም አሜሪካ ለመከላከያ በቂ ወጪ ላላወጡ የኔቶ አባላት አገራቸው ከለላ እንደማትሰጥ የተናገሩት ዶናልድ ትራምፕ ዋይት ሃውስን ለመረከብ ሳምንታት በቀራቸው ወቅት ነው።

የኔቶ አባል አገራት ሊጠናቀቅ ቀናት በቀሩት የአውሮፓውያኑ 2024 ቢያንስ 2 በመቶ የሚሆነውን ብሄራዊ ያልተጣራ ገቢያቸውን (ጂዲፒ) በየዓመቱ ለመከላከያ ወጪ ለማዋል ቃል ገብተው ነበር።

ነገር ግን በብራሰልስ በተካሄደ ዝግጅት ላይ የቀድሞው የኔዘርላንድስ ጠቅላይ ሚኒስትር ይህ በቂ እንዳልሆነ እና "አደጋ በከፍተኛ ፍጥነት እየገሰገሰ እየቀረበን ስለሆነ የበለጠ ያስፈልጋል" ብለዋል።

በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት የአውሮፓ አባል አገራት ከብሔራዊ ያልተጣራ ገቢያቸው (ጂዲፒ) ውስጥ ከ3 በመቶ በላይ ወጪ ያደርጉ እንደነበር አስታውሰዋል።

"ጦርነትን ለመከላከል አሁን ብዙ ወጪ ማውጣት ካልቻልን ጦርነቱን ለመዋጋት ከፍተኛ ዋጋ እንከፍላለን" ሲሉ ነው ያስጠነቀቁት።

ሩሲያ ምጣኔ ኃብቷን በጦርነት ላይ ያለ በማድረግ፣ በመጪው የአውሮፓውያኑ ዓመት የመከላከያ ወጪዋን ከበጀቷ ውስጥ አንድ ሶስተኛ እንዳደረገች ገልጸው ይህም ከቀዝቃዛው ጦርነት በኋላ ከፍተኛው ነው ብለዋል።

ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ ከፈጸመች ጀምሮ ለመከላከያ የምታወጣውን ወጪ በከፍተኛ ደረጃ የጨመረች ሲሆን በቀጣዩም ዓመት ያጸደቀችው በጀት ክብረ ወሰን የሚባል ነው።

ሩሲያ በምስራቃዊ ዩክሬን እያደረገችው ያለው ግስጋሴ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ነው። ሩሲያ በአውሮፓውያኑ 2024 የተቆጣጠረቻቸው የዩክሬን ግዛቶች ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ስድስት እጥፍ ይበልጣል ተብሏል።

የኔቶ አባል አገራቱ 2 በመቶ የሚሆነውን ጂዲፒያቸውን ወጪ ማድረግ ቢጠበቅባቸውም ሁሉም ይህንን አያሟሉም።

ትራምፕ የምዕራቡ ዓለም ወታደራዊ ጥምረት አባል ሆኖ ክፍያቸውን ያልከፈሉ ማንኛውም የኔቶ አባል ሩሲያ እንድታጠቃ እንደሚያበረታቱ ተናግረው ነበር።

በአውሮፓ እና በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ 32ቱ የኔቶ አባላት አንደኛው ጥቃት ከተፈጸመባት ሌሎቹ እንዲከላከሉ ስምምነት ላይ ደርሰዋል።