በናይጄሪያ ታግተው የነበሩ የሰርግ ታዳሚዎች ተለቀቁ

የፎቶው ባለመብት, Jafar Kanoma
በናይጄሪያ ሰሜናዊ ምዕራብ ዛምፋራ ግዛት ከሁለት ሳምንት በፊት ታግተው የነበሩ 29 የሰርግ ታዳሚዎች ተለቀቁ።
ታዳሚዎቹ አጎራባች ከሆነችው ሶኮቶ ግዛት በነበረ የአንድ የስራ ባልደረባቸው ሰርግ ላይ ቆይተው ወደ ቤታቸው እየተጓዙ በነበረበት ወቅት ነው አድፍጠው በነበሩ ታጣቂዎች ከነ ተሽከርካሪያቸው ታፍነው የተወሰዱት።.
የታገቱት ግለሰቦች የዛምፋራ ግዛት ዋና ከተማ በሆነችው ጉሳው ውስጥ ቤቤጂ ፕላዛ ተብሎ ከሚጠራው ታዋቂ የስልክ ገበያ የሞባይል ስልክ አዘዋዋሪዎች ናቸው።
ሃሙስ አመሻሽ ላይ ታግተው የተለቀቁትን ግለሰቦች ከተቀበሉት መካከል የገበያው ኃላፊ ኢብራሂም ካዶ ይገኙበታል።
ኃላፊው ለቢቢሲ እንደተናገሩት ግለሰቦቹ ተዳክመውና በተጎሳቆለ ሁኔታ እንዳገኙዋቸው ነው።
አንደኛው ታጋችም በጠና ታሞ እንደነበርና ለህክምናም ወደ ሆስፒታል ተወስዶ ደም እንደተለገሰውና ሌሎችም ህክምና እንደተደረጉለት ተገልጿል።
ካዶ “አንድ ሰው ምንም ያህል ኢሰብአዊ ቢሆንም የተለቀቁትን ታጋቾች ሲያዩ ስሜታቸው ሊነካ ይገባል” ብለዋል።
የገበያው ኃላፊ ግለሰቦቹ በመጨረሻም በመለቀቃቸው ደስተኛ መሆናቸውን የገለጹ ሲሆን ግለሰቦቹን ለማስለቀቅ ካሳ ተከፍሏል የሚለውን በተመለከተ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።
ነገር ግን የታጋቾቹ ሌላ ባልደረባ ከአጋቾቹ ጋር ድርድር ከተደረገ በኋላ ካሳ መከፈሉን ለቢቢሲ አስረድቷል።
ባለሥልጣናቱ ስለ ታጋቾቹ መለቀቅ እስካሁን የሰጡት መግለጫ የለም።
ግለሰቦቹ ከታገቱ በኋላ ብዙም ሳይቆይ የፖሊስ ቃል አቀባይ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የአሰሳ እና የማዳን ስራ መጀመሩን ተናግረዋል።
በናይጄሪያ በተለይም በሰሜን ምዕራብ ክልል ገንዘብ ለማግኘት ሲባል በታጠቁ የወንጀለኞች ቡድን የሚደረጉ ግድያዎች እና አፈናዎች የተለመዱ ሆነዋል ። በዚህም ከጥር ወር ጀምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ታግተዋል ወይም ተገድለዋል።












