በኮንጎ ተሰማርተው የነበሩ የዩክሬን ሰላም አስከባሪዎች ወደ አገራቸው ተመለሱ

የፎቶው ባለመብት, MONUSCO
በተባበሩት መንግሥታት ሥር በሰላም አስከባሪነት ዲሞክራቲክ ኮንጎ ውስጥ ተሰማርተው የነበሩ የዩክሬን ወታደሮች በጦርነት ውስጥ ወዳለችው አገራቸው ተመለሱ።
በመንግሥታቱ ድርጅት የሰላም አስከባሪ ኃይል ውስጥ የነበሩት 250 ዩክሬናውያን ወታደሮች የሩሲያ ወረራን ተከትሎ ለወራት በቆየ ጦርነት ውስጥ ወደምትገኘው አገራቸው ዩክሬን ተመልሰዋል።
ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ላይ የሰላም አስከባሪው ኃይል የአየር ትራንስፖርት ክፍል አካል የነበረው የዩክሬን ቡድን ወደ አገሩ ተመልሶ ነበር።
ይህም በዲሞክራቲክ ኮንጎ ውስጥ የተሰማራው የመንግሥታቱ ድርጅት ተልዕኮ ላይ ከፍተኛ የሄሊኮፕተሮች እጥረት በማስከተል ሰላም አስከባሪው በአስፈላጊው ሁኔታ እንዳይንቀሳቀስ ሊያደርገው ይችላል ሲሉ ዲፕሎማቶች አስጠንቅቀው ነበር።
በጥቅጥቅ ደኖች በተሸፈኑት የዲሞክራቲክ ኮንጎ አካባቢውዎች ውስጥ የሚንቀሳቀሱትን የተለያዩ አማጺ ቡድኖችን ለመቆጣጠር ለሚደረገው ጥረት የአየር ትራንስፖርት አገልግሎቱ ለሰላም አስከባሪው ኃይል እጅግ ወሳኝ መሆኑ ይነገራል።
ከወራት በፊት ከሰላም አስከባሪው ቡድን የወጡት ስምንት የዩክሬን ሄሊኮፕተሮች የተባበሩት መንግሥታት በዲሞክራቲክ ኮንጎ ውስጥ ካሉት ሄሊኮፕተሮች ውስጥ አንድ ሦስተኛውን ይይዙ ነበር።
ባለፈው ዓመት የካቲት ወር ላይ ሩሲያ ወረራ የከፈተችባት ዩክሬን ከዲሞክራቲክ ኮንጎ በተጨማሪ በተባበሩት መንግሥታት ሥር በሌሎች ስፍራዎች በሰላም አስከባሪነት አሰማርታቸው የነበሩ ወታደሮቿን አስወጥታለች።
የዩክሬን ወታደሮች ከዲሞክራቲክ ኮንጎ በለቀቁበት ጊዜ በአገሪቱ የመንግሥታቱ ድርጅት ኃይል አዛዥ የሆኑት ብራዚላዊው ጄኔራል ማርኮስ ዳ ኮስታ እንደተናገሩት፣ የዩክሬናውያኑ ወታደሮች “ለአስር ዓመታት የዘለቀው ታላቅ አስተዋጽኦን” አድንቀዋል።
ሞኑስኮ በመባል የሚጠራው በዲሞክራቲክ ኮንጎ ለዓመታት ተሰማርቶ የቆየው የተባበሩት መንግሥታት ተልዕኮ በአገሪቱ ውስጥ በከፍተኛ ጫና ውስጥ ይገኛል።
ለሰላሳ ዓመታት ያህል በርካታ ታጣቂ ቡድኖች ግድያ፣ መድፈር እና ወርቅና አልማዝ የመሳሰሉ ማዕድናት ዘረፋን ሲፈጽሙ በቆዩበት በዲሞክራቲክ ኮንጎ ምሥራቃዊ ክፍል ሰላም ለማስፈን ባለመቻላቸው የመንግሥታቱ ድርጅት ወታደሮች በስፋት ይተቻሉ።
ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ላይ በምሥራቃዊ ኮንጎ ውስጥ በሚገኙ ከተሞች በሰላም አስከባሪው ላይ ተቃውሞ ያሰሙ ነዋሪዎች በመንግሥታቱ ድርጅት ህንጻዎች ላይ ጥቃት ሰንዝረው የሰላም አስከባሪው ኃይል አባላትን ጨምሮ 36 ሰዎች ተገድለዋል።
የመንግሥታቱ ድርጅት ሰላም አስከባሪ ተልዕኮ በዲሞክራቲክ ኮንጎ ውስጥ ለ22 ዓመታት የቆ ሲሆን፣ ቀስ በቀስ እየለቀቀ ይወጣል ቢባልም የተቀመጠለት ቀነ ገደብ ግን የለም።
በማዕድንና ሀብቷ በበለጸገችው በዲሞክራቲክ ኮንጎ ውስጥ ተሰማርቶ የሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰላም አስከባሪ ኃይል በአገሪቱ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ቆይቷል።
ይህ ተልዕኮ የመንግሥታቱ ድርጅት በዓለም ዙሪያ ካሉት 12 የሰላም ማስከበር ስምሪቶች መካከል ትልቁ እና ከፍተኛ ወጪን የሚያስወጣ ነው።












