ፑቲንን በመተቸት የሚታወቁት ፖለቲከኛ በቀጣዩ ምርጫ ለፕሬዝዳንትነት መወዳደር እፈልጋለሁ አሉ

የፎቶው ባለመብት, REUTERS
ሩስያ ከዩክሬን ጋር በምታደርገው ጦርነት የምትከተለውን ወታደራዊ ስልት አጥብቀው በመተቸት የሚታወቁት ፖለቲከኛ በቀጣዩ የካቲት ወር በሚደረገው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ፑቲንን መፎካከር እንደሚፈልጉ ገለጹ።
የጦርነቱ ቀንደኛ ደጋፊ የሆኑት ጦማሪ እና ፖለቲከኛው ኢጎር ጊርኪን የ52 ዓመት ሰው ናቸው። ሰውዬው በአውሮፓውያኑ 2014 ሞስኮ የደቡብ ክሪሚያ ባህረገብ መሬትን በጠቀለለችበት ጊዜ የሩስያ ደጋፊ የሆኑ ተዋጊዎችን መርተዋል።
ጊርኪን በጸንፈኝነት ተከሰው እስር ላይ የሚገኙ ሲሆን ፍርዳቸውን እየተጠባበቁ ይገኛሉ። የቀረበባቸውን ክስ ግን አይቀበሉትም።
አሸናፊው አስቀድሞ የሚታወቅበትን “የይስሙላ” ምርጫ ማደናቀፍ እፈልጋለሁ ሲሉም ተሰምተዋል።
በርካቶች ይህ አስተያየት በቀጥታ ፕሬዝዳንት ፑቲን ያነጣጠረ እንደሆነ ብዙዎች ያምናሉ። ሆኖም እስካሁን ፑቲን ለፕሬዝዳንትነት ዳግም እንደሚወዳደሩ በይፋ ያሉት ነገረ የለም።
ጊርኪን በጻፉት እና ትናንት ዕሁድ በአንድ የቴሌግራም ቻናል ላይ በተሰራጨ ደብዳቤ በዚህ ጊዜ በሩስያ ለፕሬዝዳንትነት መወዳደር በስለት መጫወት እንደሆነ በሚገባ እረዳለሁ ብለዋል።
ሆኖም በውድድሩ መሳተፋቸውና ሀገር ወዳድ ሰዎችን ማሰባሰብ መቻላቸው “ብቸኛው አሸናፊ ቀድሞ የሚታወቅበትም” ምርጫ ለማስተጓጎል እንደሚረዳ አምናለሁ ሲሉ ጽፈዋል።
ጨምረውም “ውጫዊና ውስጣዊ ስጋቶችን ለመጋፈጥ አንድ የምንሆንበት ዕድል ነው” ብለዋል።
ደጋፊዎቻቸው ለምርጫ ዘመቻው የሚሆን ዋና ጸህፈት ቤት እንዲያቋቁሙ እና ለዕጩነት የሚያበቃ ፊርማ እንዲያሰባስቡ ጠይቀዋል። በምርጫው ለመሳተፍ እንደማይፈቀድ ባውቅም ደጋፊዎቼ በዚህ ተግባር ቀጥሉ ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, IGOR STRELKOV TELEGRAM PAGE
የጊርኪን የወንጀል ምርመራ ለሳምንታት የተራዘመ ሲሆን ጥፋተኛ የሚል ብይን ስላልተላለፈባቸው በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ በምርጫ የመሳተፍ መብት እንዳላቸው ደጋፊያቸው ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።
ጊርኪን የደህንነት መኮንን ሆነው ሰርተዋል። ሰውዬው እንደ አውሮፓውያኑ በ2014፣ 298 ሰዎች የሞቱበት የማሌዥያ የመንገደኞች አውሮፕላን ተመትቶ ሲወድቅ ተሳትፎ ነበራቸው በሚል በሌሉበት የኔዘርላንድ ፍርድቤት ጥፋተኛ ሲል ከበየነባው ሶስት ሰዎች አንዱ ናቸው።
ሩስያ ዩክሬንን ላይ ጦርነት ስትከፍት የሀገራቸው ጦር የሚከተለውን የጦርነት ስልት በጠንካራ ቃላት በመተቸት ይበልጥ ታዋቂ ሆነዋል። በዚህ ጦርነት ሩስያ ውጤታማ የማትሆን ከሆነ አገራቸው አቢዮት ወይም የእርስበእርስ ጦርነት ሊያጋጥማት እንደሚችል ሲናገሩ ተደምጠዋል።
ፖለተከኛው ባለፈው ሃምሌ ወር ላይ ታስረዋል። ፍርድ ቤት ጥፋተኛ ብሎ የሚወስን ከሆነ እስከ አምሰት ዓመት ሊታሰሩ ይችላሉ።
የሩስያ ባለስልጣናት ባለፈው ሰኔ ወር የቀድሞ የቫግነር መሪ ዮቭጊን ፕሪዢጎቭ የከሸፈ አመጽ ከቀሰቀሱ በኋላ ሩስያ ዩክሬን ላይ በምታደርገው ጦርነት የምትከተለውን ስልት አጥብቀው በሚተቹ ሰዎች ላይ እርምጃ እየወሰዱ ይገኛሉ።
ፕሪዢጎቭ በነሃሴ ወር በአውሮፕላን አደጋ የሞቱ ሲሆን የአደጋው መንስሄ እስካሁን አልታወቀም።
የፕሬዝዳንት ፑቲን ቀል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስቮክ ባለፈው አርብ በታተመ ቃለ ምልልስ አለቃዬ በቀጣዩ ምርጫ ይሳተፋሉ ብዬ ታስፋ አደርጋለሁ ብለዋል።
ፑቲን ከአውሮፓውያኑ 2000 እስከ 2008 ፕሬዝዳንት ሆነው አገልግለዋል። ከዚያም በ2012 ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ተመልሰዋል።
በሩስያ በቅርቡ የተደረገ የህገ መንግስት ማሸሻያ ቀጣዩን መርጫ የሚያሸንፉ ከሆነ ፑቲን እስከ 2036 የሩስያ ፕሬዝዳንት እንዲሆኑ ያስችላቸዋል።












