ከትግራይ ጦርነት ሸሽቶ በጂቡቲ ሽፍቶች ከባድ ስቃይ እና መከራ የደረሰበት ማቱሳላ በረከት

ማቱሳላ በረከት እባላለሁ። ተወልጄ ያደኩት መቀለ ውስጥ በቀበሌ 03 አይደር ክፍለ ከተማ ነው።
ወላጆቼ የመንግሥት ሠራተኞች ናቸው። የትግራይ ጦርነት ሲጀመር የ11ኛ ክፍል ተማሪ ነበርኩ።
በእርግጥ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ትምህርቴን አቋርጬ ብቆይም ከትምህርት ገበታ ሙሉ በሙሉ የተለየሁት በትግራይ ጦርነት ሲጀመር ነው።
በአሁኑ ጊዜ ጂቡቲ ውስጥ በሆል ሆል የስደተኞች መጠለያ እገኛለሁ።. . .
ከጦርነቱ . . . ወደ ስደት
ጦርነቱ ሲጀመር መቀለ ከተማ ውስጥ ነበርኩ። ያኔ በጣም የሚያስፈራ ከባድ ሁኔታ ነበር። ከጦርነቱ በፊት ከተወለድኩባት ከተማ ወጥቼ አላውቅም። ከአገር መውጣት ይቅርና ወደ ሌሎች የትግራይ አካባቢዎች ሄጄ አላውቅም።
ለመጀመሪያ ጊዜ እግሬን ለስደት ያነሳሁት ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ ነው።
ጦርነቱ እንደተቀሰቀሰ ከጥቂት ቀናት በኋላ ኅዳር 12/2013 ዓ.ም. ከትግራይ ወጥቼ ወደ ስደት አቀናሁ። በዚያች ቀን ለመጀመሪያ ጊዜ ከእናቴ ተለያየሁ፤ የማልረሳት ቀን ናት።
ከዚያ በፊት ስለ ስደት አስቤ አላውቅም። ከመቀለም የምወጣ አይመስለኝም ነበር።
ትኩረቴ በሙሉ ትምህርት ላይ ነበር። ምናልባት አሁን የዩኒቨርሲቲ ተማሪ እሆን ወይም እመረቅ ነበር። ወላጆቼ የመንግሥት ሠራተኞች ናቸው፤ ስለዚህ እኔ ሥራ ይዤ እነርሱን እምረዳበት ጊዜ ይሆን ነበር ብዬ አስባለሁ።
ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ በኋላ ነገሮች እየተባባሱ ሲሄዱ እና በቅርብ የማውቃቸው ሰዎች እና ጓደኞቼ ሲጎዱ ቤተሰቤን ሳላማክር ነው ወደ ስደት ያመራሁ።
ከመቀለ ተነስቼ 45 ኪሎ ሜትር ያህል በእግሬ ተጉዤ አብአላ [በትግራይ እና አፋር ድንበር ላይ የምትገኝ ትንሽ ከተማ] ደረስኩ።
ከዚያ መኪና አግኝቼ ጉዞዬን ቀጠልኩ። ግን መድረሻዬ የት እንደሚሆን አላውቅም ነበር።
ጉዞዬ ከባድ ነበር። አጠገቤ የማውቀው ሰው አልነበረም። ፈጣሪን አምኜ ነበር የወጣሁት። ከአብአላ ወጥቼ ከዚህ በፊት በስም እንጂ ረግጫት ወደ ማላውቃት አዲስ አበባ ገባሁ።
እዚያም ምንም ጥሩ ነገር አልጠበቀኝም፤ ከባድ ጊዜ ነው ያሳለፍኩት። የማውቀው ሰው ሳይኖር ብቻዬን መውጣቴ ሁኔታዬን አባብሶታል። አዲስ አበባ እንደ ደረስኩ ተይዤ ለስድስት ወራት ታሰርኩ።
ከእስር ቤት እንደወጣሁ የስደት ጉዞዬን ቀጥዬ ሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ደረስኩ። እዚያም ተይዤ ለአራት ወር ታሰርኩ።

‘ፍላጎቴ ከኢትዮጵያ መውጣት ነበር’
በአዲስ አበባ ውስጥም ሆነ ጅግጅጋ ውስጥ ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ በማንነቴ ነው የታሰርኩት ብዬ አምናለሁ።
በሁለቱም እስራት ፍርድ ቤት ሳልቀርብ ለወራት ቆይቻለሁ። በማይታወቁ እስር ቤቶች 10 ወራት ያህል አሳልፌያለሁ።
የኢትዮጵያን ድንበር ተሻግሬ ለመውጣት ጉዞዬን ስጀምር ሌሎች የማላውቃቸው ሰዎች ከሩቅ እያየሁ ነበር።
ቢሆንም ግን ብቻዬን ነበር ጉዞዬን የቀጠልኩት። ወዴት እንደምሄድ አላውቅም። ያኔ ፍላጎቴ ከኢትዮጵያ መውጣት እና ወደ የትኛውም አገር መግባት ነበር።
ያን ሁሉ መንገድ ተሻግሬ ጂቡቲ ብገባም የት እንዳለሁ ግን አላወቅኩም።
የስደተኞች መጠለያ መኖሩን ወይንም የት ሄጄ ማረፍ እንዳለብኝ አላውቅም ነበር። ብቻዬን በረሃዎቹን እየሰነጠቅኩ ስጓዝ ፍርሃትም፣ ስጋትም አልተሰማኝም። ምክንያቱም ከኢትዮጵያ እየራቅኩ በሄድኩ ቁጥር ነፃነት ይሰማኝ ነበር።
እንደ አጋጣሚ ወደዚህ አካባቢ [ጂቡቲ-ሆል ሆል የስደተኞች ካምፕ] ስደርስ ትግርኛ የሚናገሩ ሰዎች ወንዝ ውስጥ ገላቸውን ሲታጠቡ አገኘሁ።
ከኢትዮጵያ መሆኔን አውቀው በአማርኛ አናገሩኝ፤ እኔ ግን ከትግራይ መምጣቴን ነገርኳቸው። እነዚያ ያገኙኝ የትግራይ ተወላጆች ተባበሩኝና በስደተኛነት ተመዝገብኩ።
ነሐሴ 11/2013 ወደዚህ ካምፕ ገባሁ። ካገኘሁ እየበላሁ፣ ካጣሁ እየተራብኩ ለአንድ ዓመት ያህል እዚህ ቆየሁ።


ተስፋዬን ያጨለመ ውሳኔ
ከእኔ በፊት ወደዚህ አገር የመጡ ሰዎች በቀጥታ የስደተኛ ወረቀት ይሰጣቸው እንደነበር ነገሩኝ።
እኔ ከመጣሁ በኋላ ግን መጀመሪያ የጥገኝነት ጠያቂ ወረቀት ነው የሚሰጠው። ቀጥሎ ማጣራት ይደረግና ጥያቄው ተቀባይነት ያገኛል ወይም ውድቅ ይደረጋል። ከመጣሁ ከአንድ ወር በኋላ ይመስለኛል የጥገኝነት ጠያቂ ጊዜያዊ ወረቀት ተሰጠኝ።
ጊዜያዊ ወረቀቱን ካገኘሁ ከወራት በኋላ የስደተኞች ኮሚሽን መርማሪዎች ፊት ቀርቤ ጥያቄያቸውን ከመለስኩ በኋላ ጥያቄዬ ተቀባይነት እንዳላገኘ ተነገረኝ።
ውሳኔው ተስፋዬን ያጨለመ ነበር። ያኔ የእኔ ብቻ ሳይሆን የብዙ ሰዎች የጥገኝነት ጥያቄ ተቀባይነት አላገኘም።
የተለያዩ የአካል ክፍሎቻቸውን በጥይት የተመቱ ራሱ ጥያቄያቸው ውድቅ ተደርጎባቸዋል።
በጣም መጥፎው የስደት ጉዞዬ የሚጀምረው እዚህ ላይ ነው። ማመልከቻዬ ውድቅ ሲደረግ ተስፋ ቆርጬ ባሕር ለመሻገር ወሰንኩ። ከዚያም ብቻዬን ነው የተነሳሁት።
የመን ውስጥ የተሻለ ነገር ሊኖር ይችላል ብዬ ተስፋ አድርጌ መንገድ ጀመርኩ። በጉዞዬ ላይ ግን ያልጠበቅኳቸው እና አሰቃቂ ነገሮች አጋጠሙኝ።
ከጂቡቲ በባሕር ተሻግሮ ነው የመን የሚደረሰው። እናም የመን ለመድረስ በማሰብ ከካምፑ ወጥቼ ጉዞዬን ወደፊት ቀጠልኩ።
ብዙ ሳልሄድ ወደ የመን የሚያደርሰኝን ጉዞ ሳልጀምር ከባሕሩ ዳርቻ ላይ በሽፍቶች ተያዝኩኝ። መንገድ ላይ ጠብቀው አስቆሙኝ፤ በኦሮምኛ ያነጋግሩኝ ጀመር። አፋርኛ የሚናገሩ የአካባቢው [የጂቡቲ ዜጎችም] አብረዋቸው ነበሩ።
ኦሮምኛ እንደማልችል ሲረዱ በአማርኛ አዋሩኝ። በአማርኛ ስመልስላቸው “እንድንለቅህ 3,000 ብር ክፈል” አሉኝ። ምንም ገንዘብ እንደሌለኝ እና ተቸግሬ እየተሰደድኩ መሆኔን ነገርኳቸው።
የያዝኩት አንዳችም ነገር እንደሌለ ላሳያቸው እና ላስረዳቸው ሞከርኩ። ነገር ግን ሊረዱኝ አልቻሉም፤ ያዙኝ።
በእጃቸው ስገባ ቀጥሎ ምን ማድረግ እንዳለብኝ የማውቀው ነገር አልነበረም።
ምንም ውሃ እና ምግብ ሳልቀምስ እየገረፉ እና እያስፈራሩ ገንዘብ እንድሰጣቸው ይጠይቁኝ ነበር። ሕይወቴን ለማዳን የሰጡኝ ብቸኛ አማራጭ ወደ ቤተሰቤ ስልክ መደወል ነበር።
የወላጅ ዕዳ!
ያኔ ጥሙና ረሃቡ ላይ ድብደባው ሲጨመርበት ሞቴን የተመኘሁበት ቅጽበት ነበር።
የያዙኝ ሽፍቶች ደውለው ከቤተሰቦቼ ጋር አገናኙኝ። ወላጆቼን በትግርኛ ነበር ያነጋገርኳቸው። ይህም በጣም የከፋ አደጋ ውስጥ አስገባኝ።
በትግርኛ ስናገር ሲሰሙ መጀመሪያ የጠየቁኝን 3,000 ብር ወደ 25,000 ብር ከፍ አደረጉት።
በጦርነት የተከበቡት ወላጆቼ ለራሳቸው ከባድ ችግር ውስጥ በነበሩበት ወቅት ይህን ያህል ገንዘብ እንዲልኩ ተጠየቁ።
ወላጆቼ የመንግሥት ሠራተኞች በመሆናቸው፣ በጦርነቱ ምክንያት ሥራቸውን እና ደሞዛቸው ከተቋረጠባቸው ረዥም ጊዜ ሆኗል።
ወላጆቼ ግን እኔን ለማዳን የትም ገብተው የተጠየቅኩትን ገንዘብ ከፈሉልኝ። ግን በዚህ አላበቃም። እኔን ሳይለቁ እንደገና ተጨማሪ ገንዘብ መጠየቅ ቀጠሉ።
ገንዘብ እንዲከፈላቸው ሲጠይቁ ወደ ወላጆቼ ቪዲዮዎችን ይልኩ ነበር።
ቪድዮዎቹ እኔን ሲደበድቡ እና አንገቴ ላይ ቢላ በማድረግ “እንገድለዋለን” እያሉ ሲያስፈራሩ የሚያሳዩ ናቸው።
በያዙኝ ሽፍቶች እጅ ለሦስት ቀናት ያህል ክፉኛ ተሠቃየሁ። ድብደባ፣ ጥማት እና ረሃብ ሞቴን እንድመኝ አደረገኝ።
ሽፍቶቹ ገንዘቡ ተልኮ ሲደርሳቸውም በሕይወት ልተርፍ እንደማልችል አስብ ነበር።
ቤተሰቦቼን ደጋግመው ገንዘብ ሲጠይቁ በስተመጨረሻ አደጋ ውስጥ እንደምገባ አመንኩኝ። ገድለው በረሃ ላይ ወይም ወደ ባሕር እንደሚጥሉኝ አልተጠራጠርኩም፤ ጨካኞች ናቸው።
እነዚያ ይህን ተግባር የፈጸሙት ሽፍቶች ብቻ ሳይሆኑ ሕገወጥ አሸጋጋሪዎችም ናቸው። ከእኔ ሌላ ብዙ ስደተኞችንም አስረው ገንዘብ ይጠይቁ ነበር።
ነገር ግን እራሳቸው ሊያሻግሯቸው ያመጧቸውን ሰዎች በተሻለ ሁኔታ ይይዟቸው ነበር። ውሃ እና ምግብ ያቀርቡላቸዋል። እንዲንቀሳቀሱም ይፈቅዱላቸው ነበር። እኔ ግን ጨለማ ሁኔታ ውስጥ ነበር ያሳለፍኩ።
ውሃ እና እህል ከመከልከላቸውም በተጨማሪ በአጠገቤ ሲያልፉ ይደበድቡኛል፤ ያሰቃዩኛል። አካላዊ ጥቃት ያደርሱብኝ እና በማንነቴ ይሳለቁብኝ ነበር። ክፉኛ ጎዱኝ። ጫማ ስላላደረግኩ እግሬ ቆሰለ፤ ወባም ታመምኩ . . . የሞትኩ ያህል ሆንኩ።
“መሞቴ ካልቀረ . . .”
ገንዘብ ቢከፈላቸውም አጋቾቼ ሊለቁኝ እንደማይፈልጉ ተረዳሁ።
እኔን ይዘው ወላጆቼን ገንዘብ ላኩ እያሉ የገቢ ምንጭ አድርገው እንደሚጠቀሙብኝ ሳውቅ በሕይወት የመትረፍ ተስፋዬ እየደበዘዘ ሄደ።
በመጨረሻ “ብሞትም ማምለጥ አለብኝ” ብዬ ወሰንኩ።
በተደጋጋሚ እየጠየቁ የተላከላቸው ገንዘብ ስላልበቃቸው እንደ መጠቀሚያ ከሚይዙኝ በደመ ነፍስ ለማምለጥ ወሰንኩ። እንደ ገንዘብ ማግኛ ተጠቅመው መጨረሻ ላይ እንደሚገድሉኝ አልተጠራጠርኩም።
“መሞቴ ካልቀረ እየሮጥኩም ቢሆን ልሙት” በሚል በጭፍን ሸሸሁ። በባዶ እግሬ ሮጥኩ። እግሬ በደም ታጥቦ መሮጤን ቀጠልኩ።
ከእነርሱ ሸሽቼ የተወሰነ ርቀት ከተጓዝኩ በኋላ በድካም እና በሕመም ራሴን ስቼ ወደቅኩ። ብዙ የማውቀው ነገር አልነበረም፤ ግን አንድ የአፋር ተወላጅ አግኝቶ አነሳኝ።
በመጨረሻም ወደዚህ ወዳለሁበት የስደተኞች ካምፕ ተመልሼ መጣሁ።
እዚህ ካምፕ ስደርስ እግሬ፣ አካሌ እና ዐይኔ ቆስሎ በሕመም ተዳክሜ ስለነበር ሁሉም ስደተኞች ተረባርበው የቻሉትን ያህል ረዱኝ።
ለጥረታቸው ምስጋና ይግባውና ከደረሰብኝ አካላዊ ጉዳት እና ከወባ በሽታ አገግሜ ይችን ቀን ለማየት በቃሁ።
ከጠላፊዎቼ አምልጬ እዚህ ከመጣሁ ወራቶች ተቆጥረዋል። እዚህ በሆልሆል የስደተኞች መጠለያ ውስጥ አስቸጋሪ ሁኔታን እያሳለፍኩ እገኛለሁ።
*
ወጣቱ ማቱሳላ በሕጋዊ መንገድ ወደ ሦስተኛ አገር ሄዶ በጦርነቱ ምክንያት ከፍተኛ ችግር ውስጥ የሚገኙትን ወላጆቹን ለመደገፍ ተስፋን ሰንቋል።












