የጦርነት ዳፋ የመጨረሻው ውጤት የሚታየው ጦር ሜዳ ላይ ሳይሆን ቤተሰብ ውስጥ ነው - ይፍቱሥራ ምትኩ

ይፍቱስራ ምትኩ

የፎቶው ባለመብት, Yiftusira

ይፍቱሥራ ምትኩ ‘በተለይ አሥራ አንደኛው’ የተሰኘው መጽሐፏ ቀዳሚ ሥራዋ ነው። አሁን ደግሞ ‘ወድቆ የተገኘ ሐገር’ የሚል መጽሐፍ ለአንባቢዎች አቅርባለች።

የደራሲ ይፍቱሥራ ምትኩ ሁለተኛ የልቦለድ ሥራ የሆነው ‘ወድቆ የተገኘ ሐገር’ ባለ 110 ገፆች ያሉት ወጥ ልቦለድ ነው።

“ወድቆ የተገኘ ሐገር” መቼቱን በ1990ዎቹ መጀመሪያ በተካሄደው የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ላይ በማድረግ የተጻፈ ልቦለድ መሆኑን ደራሲዋ ከቢቢሲ ጋር ቆይታ ባደረገችበት ወቅት ተናግራለች።

አክላም ታሪኩ ከአስከፊ ጦርነት የተመለሰ ታዳጊን ሕይወት እና አጠቃላይ የቤተሰቡን ኑሮ የሚያስቃኝ መሆኑን እና በአንድ ቤተሰብ አገርን አሻግሮ ማየት እንደሚያስችል ገልጻለች።

ቢቢሲ- መጽሐፍሽን ሳነበው እናት እና ልጅ በተደራራቢ መከራ ሲያልፉ አባት እና ወንድም ደግሞ አንደኛው በሞት ሌላኛው በሽሽት መከራ የማይጋፈጡ ሆነው እናያቸዋለን። ለምንድን ነው ሴት ገጸባህሪያቶችሽ ተደራራቢ መከራን እንዲጋፈጡ ያደረግሽው?

ይፍቱሥራ- አጠቃላይ የመጽሐፉ ታሪክ ሴት ገጸባህሪያቶችን መከራ የማጋፈጥ አይደለም። ዓላማዬ በጦርነት ምክንያት ወታደሩ ወደ ጦር ሜዳ ይዘምታል፣ የሚሞተው ይሞታል፤ የሚተርፈው ይተርፋል። ከዚያ በኋላ ግን የጦርነቱ ዳፋ መጨረሻ ላይ የሚታየው ቤት ውስጥ ነው። በአንድ ግለሰብ ቤት እና ሕይወት ውስጥ ነው።

በዚያ ምክንያት የሚፈራርስ ሕይወት፣ የሚበላሽ የአንድ ቤተሰብ ታሪክ ይኖራል። እኔም ማሳየት የፈለግኩት ያንን ነው። መታከም ወይንም መነገር ያለበት ከጦርነት በኋላ ቤተሰብ ውስጥ የሚመጣ ሰቆቃ [ትራውማ] አለ። ያንን ችግር ነው ማሳየት የፈለግኩት።

ቢቢሲ - አንድ ቤተሰብ ስንት ነው የሚለው የደራሲ አለማየሁ ገላጋይ ከመጽሐፉ ጀርባ የጻፈው ሀሳብ መጽሐፉን ስጨርስ እኔንም ተሰምቶኛል። እንደው ለአንቺ ከዚህ መጽሐፍ ተነስተሽ አንድ ቤተብ ስንት ነው?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ይፍቱሥራ - ለእኔ አንድ ሰው አገር ነው ብዬ ነው የማስበው። ለምሳሌ አገርሽ የት ነው? ብባል አገሬ ልጄ ናት እላለሁ። ጋራ ሸንተረሩ ወይንም ደግሞ መቶ ሚሊዮን ባልነው ቁጥር አይደለም አገር የሚሆነው። የእያንዳንዳችን አገር ቤታችን ውስጥ ወይንም ደግሞ ጎናችን ያለ፣ የበለጠ ዋጋ የምንሰጠው፣ የምንሞትለት ወይንም ደግሞ የምንኖርለት ዓለማችን ነው አገራችን ባይ ነኝ።

ቤተሰብ ሲሆን ከፍ ይላል ብዬ ነው የማስበው። . . . ቤተሰብ ብቻ አይደለም አገር። አንድ ግለሰብ ራሱ አገር ይሆናል። እርሱ ሲደማመር ነው ሚሊዮን የሚሆነው። በቅርቤ ያሉትን ልጄን፣ እህቴን ወይንም እናቴን ሳልወድ፤ አይቼው የማላውቀው የሩቅ አገር ሰው እንዴት አገሬ ይሆናል? ለዚያ ለመኖር ወይንም ለዚያ ለመሞት ዝግጁ ሳልሆን ያኛው ሰው እንዴት አገሬ ሊሆን ይችላል። ለዚያኛው ሰው እንዴት ለመሞት ዝግጁ ልሆን እችላለሁ? ብዬ አምናለሁ። እና ለእኔ ቤተሰብ ሲሆን እንደውም ሰፋ፤ እንጂ አንድ ሰውም አገር ሊሆን ይችላል ብዬ አምናለሁ።

ቢቢሲ- ማስረሻ በልጅነቱ ዘመተ፤ ያንንም ተከትሎ የአእምሮ ሕመም ገጠመው። ከዚያ ከተመለሰ በኋ ደግሞ ለረዥም ጊዜ ጠፍቶ ከረመ። በኋላም እስር ቤት መጨረሻው ሆነ። ለምንድን ነው ማስረሻን ከንቱ ማድረግ ያስፈለገው?

ይፍቱሥራ - አላማው አንኳን ማስረሻን ከንቱ ማድረግ አልነበረም። [ሳቅ] ማሳየት የፈለግኩት ከጦርነት በኋላ የሚመጣ ጦስን ነው። በተለይ ከጦር ሜዳ በሕይወት የሚወጣ ወታደር በሰላም ተመሰለ ይባላል፤ ይወደሳል።

እውነት ያ ወታደር በሰላም ነወይ የተመለሰው? እውነት በሕይወትስ ነወይ የተመለሰው? አብሮት የነበረ ሰው፣ ጓደኛው ሲሞት አይቶ፣ ሲቆስል ተመልክቶ ሲመጣ እውነት በሰላም ነወይ የተመለሰው? ብዙ ነገሩ ሞቶ፣ ብዙ ነገሩ ጎድሎ አይደለም ወይ የሚመለሰው?

ሥነ ልቦናው ታሞ፣ ሥነ ልቦናው ተጎድቶ አይደለም ወይ የሚመለሰው? እኛ ደግሞ ያንን ባለማከማችን በጣም ብዙ የፈረሱ ሕይወቶች አሉ። እውነቱን ለመናገር ከጦር ሜዳ ከተመለሱት መካከል በጣም ጥቂቶች ናቸው ሕይወታቸውን አስተካክለው ሲመሩ የምናየው። አብዛኛው ባክኖ ነው የሚቀረው። ምክንያቱም ጦርነት ቀላል ነገር አይደለም፤ እና ያ መታከም አለበት ለማለት ነው። ያ ነገር ሳይታከም ሲቀር መዘዙ ብዙ መሆኑን ለማሳየት ነው።

ቢቢሲ- መጽሐፍሽ ውስጥ የተሳሉት ወንድ ገጸባህሪያት ጠንካራ አይደሉም። እውነቱን ለመናገር ወንድ ልጅ ባዳ ነውየሚለውን የእናትየውን ንግግር የሚወክሉ ናቸው። ለአገር ዘምተው የሚዋደቁ፣ ቤተሰባቸውን ቀጥ አድርገው የያዙ፣ ገመና ሆነው እናትየውን የሸፈኑ ሌሎች በክፉ እንዳያይዋቸው ሆነው ሳሉ ድኩም የሆኑት ለምንድን ነው?

ይፍቱሥራ - እርግጥ ነው አገርን ያቆሙት ወታደሮች ናቸው። አገርን ያቆሙ የሞቱላት ሰዎች ናቸው። ይኼ ብዙዎችን የሚያስማማ ሃሳብ ነው። . . . ከዚያ በሻገር ግን አገርን የሚያቆመው ሴቶች ባሉበት ቦታ ጸንተው መቆማቸው ነው ብዬ አምናለሁ። ምን ማለቴ ነው። አገር ማለት እንግዲህ . . . በሰሜን በደቡብ፣ በምዕራብ በምሥራቅ የተከበበው ድንበር ብቻ አገር ነው ብዬ አላምንም።

አገር ማለት የእኔ ቤት ነው ብዬ አምናለሁ። እና አንድ ሰው ከእኔ ቤት ወጥቶ ሲሄድ ቤቴ እንዲፈርስ አድርጎ ከሆነ አገር አፍርሷል ብዬ አምናለሁ። . . . አገር ማለት ሴቶች ቤት ውስጥ ይዘውት በመቆየታቸው፣ ጠብቀው በመቆየታቸው የምትገነባዋ ናት። እርግጥ ነው አገር በዳር ድንበር፣ በጦር ግንባር ትጠበቃለች። ትገነባለች አይደለም፤ ትጠበቃለች። ለመገንባቷ ግን በሴቶች በኩል የሚሠራ ሥራ አለ።

የጦረኛው አቅም ወይንም የጦረኛው ጉልበት ብዙ ጊዜ፣ ቤት ውስጥ መጠበቅ ያለበትን የእናትን የሴትን ሥነ ልቦና ይዘነጋል። ለማን ጥያት ነው የምሄደው? ለምን ጉዳይ ነው ጥያት የምሄደው? ምን ላይ ነው ጥያት የምሄደው? መሬቱን ማን ያርስላታል? ከብቶቹን ማን ይጠብቅላታል አይልም። ከዚያ ትንሽ አይል ትልቅ፣ አባት አይል ልጅ ሁሉም ተሰብስቦ ጉሮ ወሸባዬ እየዘፈነ ወደ ጦር ሜዳ ይሄዳል። በዚህ መካከል ነው እኔ የምጠይቀው ምንን ለመጠበቅ ነው ምን አፍርሰን የምንሄደው። አገርን? እዚህ ላይ እውን ጉብዝና ጥንካሬ አለ ወይ? ስንፍና አይደለም ወይ?

ምክንያቱም እዚህ ጋር መጠበቅ ያለበት ትልቅ ሥነ ልቦና እያለ፣ እናት እያለች፣ ለዚህ ነው እናቶች ባሎቻቸው ጥለዋቸው ሲሄዱ እኔ አገር አይደለሁም፣ እኔ ሆድ ውስጥ ያለው አገር አይደለም ብለው ሲጠይቁ የምንሰማው።

አገር በአካል ቆሞ እያለ አንዳንዴ ሁሉንም ረግጠህ የምትሄደው መንገድ በራሱ አገር መሥራት አይደለም። አገር በየቦታው፣ በየአካባቢያችን ያለ ሰው ነው ብዬ አስባለሁ። ለዚያ የጀግንነትንም ሐሳብ መቀየር ነው የእኔ ሐሳብ። የጀግንነት ሐሳቡንም በሌላ ዓይነት መነጽር እንድናየው በመፈለግ ነው ወንዶቹን በዚያ መልክ የሳልኳቸው።

የይፍቱስራ ሁለተኛ ስራ የሆነው ወድቆ የተገኘ ሐገር መጽሐፍ

የፎቶው ባለመብት, Yiftusira

ቢቢሲ - መጽሐፍሽ ውስጥ እናትየው ባለ ብዙ ገበር ናቸው። እናትየው ከባላቸው ሞት በኋላ፣ ከልጃቸው ዘመቻ መሄድ በኋላ፣ ከዘመቻ ከተመለሰ በኋላ፣ እንደገና ደግሞ በስተርጅናቸው ድርብ ድርብርብ ማንነት እናይባቸዋለን። በዚያ ውስጥ ማሳየት የፈለግሽው ነገር ምንድን ነው?

ይፍቱሥራ - በዚህ ውስጥ ማሳየት የፈለግኩት ነገር ሁለት ነገር ነው። አንደኛው ሰው መሸሸግያ ሲፈልግ፣ መጠጊያ ሲያጣ መጀመሪያ ቀድሞ ያምንበት የነበረው ነገር እንደሸሸገው ሳያምንበት ሲቀር ወደ ሌላ መሸሸጊያ ይሄዳል።

ለምሳሌ እኚህ እናት በታሪኩ መጀመሪያ ላይ ቆራቢ ሆነው፣ ከባላቸው ጋር ልጆቻቸውን ጠበል እያስጠመቁ እያስቆረቡ ያሳደጉ እናት ናቸው። እና እርሳቸው እግዚአብሔር ቤተሰቤን ልጆቼን ከምንም ዓይነት መከራ ይሸሽግልኛል፣ ያድንልኛል እና ያኖረኛል ብለው ያመኑ እናት ነበሩ።

ከዚያ በኋላ ግን መሸሸጊያ ይሆነኛል ብለው የሚያሰቡት ‘የአባቴ አምላክ’ የሚሉት የሆነ ሰዓት ላይ ከዳኝ ብለው ያስባሉ። የአባቴ አምላክ የሚሉትን ደግሞ በባሕላዊ አምልኮ መንገድ መለማመን ነው። ሰው መሸሸጊያ ሲያጣ መጠጊያ የማጣት ስሜት ወደ እንደዚህ ዓይነት ስሜት ይወስደዋል የሚለውን ነው መንገር የፈለግኩት። መሸሸጊያ ፍለጋ መባዘን. . .

ሁለተኛ ደግሞ ወደ ሥነ ልቦና ከወሰድነው፤ ሰው በተለያየ መከራ ውስጥ ሲያልፍ የተለያዩ ዓይነት ሥነ ልቦናዎችን ያዳብራል። አንደኛው ያለን የምንኖርበት በተለያየ ዓይነት መንገድ የምናሳድገው የራሳችን ማንነት ነው። ከዚያ በኋላ ግን ይህ በተለያየ ዓይነት መንገድ ሲናወጥ ሰውነታችን ምላሽ የሚሰጥበት ኢ-ንቁ የሆነ ማንነት አለ። እና በዚያ ምክንያት በሁለት የስሜት ጽንፍ ውስጥ መዋለል ይኖራል።

አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ሰዎች ላይ ዘርፈ ብዙ ሰብዕና ያጋጥማል። በዚህ ዓይነት መንገድ አንድ ሰው ውስጥ ብትን ያለ ሁለት ዓይነት ሦስት ዓይነት ሰብዕናዎችን እናገኛለን። እናትየውም ላይ የምናስተውለው ያንን ነው። . . .የማኅበራዊ ቀውስ ሲፈጠር፣ ሰዎች መጠጊያ ሲያጡ የሚያበጁት ራሱን የቻለ፣ አንዳንዱ ወደ ሰው፤ አንዳንዱ ደግሞ ወደ እግዚአብሔር፣ አንዳንዱ ደግሞ የራሱን እግዜር ይሰራል። ወይንም ደግሞ በአባቱ በእናቱ በኩል የሚያውቀው አምላክ ከነበረው ወደ እዚያ ይሸሸጋል። እና እኔም ለእናትየው የሰጠኋቸው የዚያ ዓይነት መወክል ነው።

ቢቢሲ- እናትየው ከፈጣሪ ጋር መጣላታቸውን በግልጽ መጽሐፉ ላይ ይነበባል። የእናትየው ብቻ ሳይሆን ልጅየውም በኋላ ላይ እንዲሁ ከፈጣሪዋ ጋር ስትጋጭ እናስተውላለን። ለምንድን ነው በተደጋጋሚ አለ ከሚሉት፣ ምርኩዛችን ነው ከሚሉት ጋር የሚጣሉት?

ይፍቱሥራ - እንግዲህ ደራሲዋ አማኝ አንደመሆኗ [ሳቅ]. . . እንደ አንድ አማኝ ከማን ጋር እጋጫለሁ ነው። እዚህ ላይ አንደዚያ ብዬ ብመልስ ይሻላል ብዬ ነው። ከማን አገር እጋጫለሁ። ከሰው ጋርማ መኮራረፍ፣ መጣላት፣ መታረቅ፣ ከባሰ ደግሞ ፈጽሞ መራራቅ ይኖራል። ነገር ግን ዞሮ የሚመለሱበር ያስፈልጋል።

እና ለአማኝ ዞረን የምንመለስበት ይመስለኛል እምነትም የሚባለው። እንጣላለን እኮ ከእግዜሩም ጋር። . . . እምነታችንን ይዞ ከቆመልን አምላክ ጋር አንጋጫለን። ከዚያ ግን አማኝ ነኝ እና ጥዬ እንዳልጥል የማውቃው እና እኔን ይዘው የሚያቆሙኝ አምዶች አሉ። ስለዚህ ተመልሰን ወደ እዚያው እንሄዳለን፤ እንጂ እየተጋጨን እዚያው አንቀርም ብዬ አምናለሁ።

ሌላው ደግሞ ሰው የመሆን አቅመ ቢስነትም ነው በነገራችን ላይ። አንዳንዴ በአቅማችን ልትፈታ የምንሞክረው ነገር አለ፤ እንሮጣለን። . . .ከአቅማችን በላይ ሲሆን ደግሞ ከፈጣሪ ጋር እንጣላለን።

ይፍቱስራ ምትኩ

የፎቶው ባለመብት, Yiftusira

ቢቢሲ- መጽሐፍሽ ገጽ 60 ላይ ገጸባህሪዋ ከራሷ ጋር ግጭት ላይ ባለችበት ወቅት ተማሪዎቿ ፊት ቆማ ‘ባዳ ነው አገር፤ ባዳ ነው እግዜር ልላቸው ይዳዳኛል’ ስትል እናነባለን። አገርን፣ እግዜርን ያህል ነገር ባዳ ነው ስትል ጠንካራ ደጋፊ ምክንያትሽ ምንድን ነው?

ይፍቱሥራ- ታስታውስ እንደሆነ 10ኛ ክፍል ማትሪክ መውሰድ የተጀመረው በ1994 ዓ.ም ነበር። ከዚያ በኋላ ለሁለት ዓመት ያክል በድጋሚ መፈተን አይቻልም ነበር። የወደቀ ወደቀ፤ ያለፈ ወደ 11ኛ ክፍል ገብቶ የመሰናዶ ትምህርቱን ይቀጥል ነበር። የዚህ መጽሐፍ መቼት ያ ጊዜ ነው። በትምህርቷ ጎበዝ የነበረችው ገጸባህሪዋ ቤተሰቧ በገጠመው ምስቅልቅል የተነሳ በሥነ ልቦናዋ ተጎድታ አስረኛ ክፍል ወድቀች። ከዚያ በኋለም ምርጫ አልተሰጣትም።

በወቅቱ የነበረው እውነታ ደግሞ አስረኛ ክፍል የወደቁ ተማሪዎች ወደ ቴክኒክ እና ሙያ ገብተው መምህር እና ነርስ ይሆኑ ነበር። ገጸባህሪዋም. . .ወሳኝ ሆነው፣ መንግሥት ሆነው የተቀመጡት ናቸው ለዚህ የዳረጉኝ ትላለች። ስለዚህ እነዚህ ሰዎች አላሰቡልኝም ባዳዎቼ ናቸው ነው ቅሬታዋ። ወንድሟ መጥፋቱ አባቷ መሞታቸው እና የእናቷ የጤና ሁኔታ በዚያ ደረጃ መጎዳቱ ደግሞ ከእግዚአብሄር ጋር እንድትጣላ ያደርጋታል። መሸሸጊያ ይሆኑኛል ያለቻቸው በሙሉ በአጠቃላይ በዙሪያዋ አለመኖራቸው ነው እግዜአብሔርም አገርም ባዳ ናቸው ብላ አንድታስብ ያደረጋት።

ቢቢሲ- ከዚሁ ገጽ ብዙም ሳንርቅ 'ሕልማችሁን ከፈተና አርቃችሁ ስቀሉ እሺ ልጆች፤ ከመውደቅ እና አለመውደቅ፣ ከመጎበዝ እና ከመስነፍ አርቁት ህልማችሁን። ፊደል ለመለየት ከረዳችሁ በቂ ነው ይኼ ሲስተም' ትላለች። የዚህችን ገጸባህሪ ሃሳብ አንቺ እንዳልሽው በ1994 ብቻ ሳይሆን ባለፈው ዓመት በዚህም ዓመት የማትሪክ ተፈታኞች ላይ አይተነዋል።

ይፍቱሥራ- በገጸባህሪዋ በኩል የትምህርት ሥርዓቱን መሄስ ፈልጌ ነው ይህንን ያስገባሁት። እንግዲህ የ10ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነትን ተከትሎ የመጣ ነገር ነው። አሁን ያለንበት ድረስ የተከተለን ደግሞ የዚሁ ትምህርት ሥርዓት ውጤት ነው። እና ሙሉ በሙሉ የትምህርት ሥርዓቱን፣ አሁን ያለንብትን ሁኔታ ለመሄስ ፈልጌ ነው ይንን ያስገባሁት።

ቢቢሲ- መጽሐፉ በአጠቃላይ የተጻፈው በጎጃም አማርኛ ነው። ተራኪዋ እና ገጸባህሪያቱ በቋንቋቸው አይለያዩም። ይህንን ሆን ብለሽ ነው ያደረግሽው?

ይፍቱሥራ- ገጸባህሪያቱ እና ተራኪዋ አንድ ዓይነት አውርተው ከሆነ ስህተት ነው። ጎጃምኛው ግን የአንድ ቤተሰብ፣ የአንድ አካባቢ፣ የአንድ ማኅበረሰብ ሰዎች እንደመሆናቸው አንድ ዓይነት ነው ሊያወሩ የሚችሉት። አንድ አይነት ቋንቋ፣ አንድ ዓይነት አገላለጽ፣ አንድ ዓይነት ተረት ተረት ነው ሊጠቀሙ የሚችሉት። ነገር ግን አንዱ ገጸባህሪ ከሌላኛው ገጸባህሪ መለየት እስከማይቻል ድረስ ደርሶ ከሆነ አንደ ጉድለት ነው የምወስደው። እርሱን ከሆነ እያልከኝ ያለኽው።

. . . .የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ እንደ ሥነ ጽሑፍ ቋንቋ የሚቀበለው የሸዋውን አማርኛ ነው። አሁን እኔ እና አንተ የምናወራበት አብዛኞቹ የአማርኛ ልቦለዶች የተጻፉበት ማለት ነው። በዚያ ምክንያት አካባቢያዊ ቋንቋን ተጠቅሞ የሚጻፍ መጽሐፍ ሲኖር ለምሳሌ የመጀመሪያው መጽሐፌ ላይ የገጠመኝ አስተያየት ምንድን ነው፤ ሥነ ጽሑፋዊ ቋንቋ አልተጠቀምሽም የሚል ነበር። . . . አንድ ቋንቋ ሐሳቡን መሸከም ከቻለ ቋንቋው ሥነ ጽሑፋዊ ቋንቋ ሆኗል ማለት እንችላለን። ነገር ግን ሳይሸከም ቢቀር፣ ግንጥል ጌጥ ሆኖ ቢቀር እንደዚያ ከሆነ እንደ ሂስ እወስዳለሁ። ማሻሻል ያለብኝን እወስዳለሁ። አለበለዚያ ግን ሥነ ጽሑፋዊ ቋንቋ አልተጠቀምሽም የሚለውን ሂስ በደረቁ አልቀበልም ብዬ ነበር የመለስኩት።

እዚህኛው መጽሐፍ ላይ ስንመጣ እንደውም ከመጀመርያ መጽሐፌ አንጻር ለዘብ ያለ የቋንቋ አጠቃቀም ነው ያለው። ገጸባህሪዋ የተማረች በመሆኗ በጣም ቀበልኛ ከሆነው ቋንቋ ወጣ ያለ ነው የቋንቋ አጠቃቀሟ። ከዚያ ባሻገር ግን ሥነ ጽሑፋችን የሚገለጥበት የግድ አሁን እኔ እና አንተ የምናወራበት፣ ከተማ ላይ ከምንሰማው ባሻገር የሆነ ብዙ የቋንቋ አጠቃቀሞች አሉን። ያ ደግሞ መነገር አለበት። ቋንቋው ሃሳቡን እስከ ተሸከመ ድረስ ራሱ ሥነ ጽሑፍ ነው ብዬ አስባለሁ።