“ሙዚቃዎቼን የምሰራው የትውልዴን መንፈስ ለማነቃቃት ነው” ሮፍናን

ሮፍናን

የኢትዮጵያን ኤሌክትሮኒክ ሙዚቃ በግንባር ቀደምነት የሚመራው ዲጄ ሮፍናን፣ ከቢቢሲው ዲጄ ኤዱ ጋር ባደረገው ቆይታ ሙዚቃ የሚሠራው “የአድማጮችን መንፈስ ለማነቃቃት” እንደሆነ ገልጿል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ቀውስ የዜጎች ደኅንነት ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ በመሆኑ ሙዚቃ የሚሠራው የሰዎችን መንፈስ ለማነቃቃትና ከፍ ለማድረግ መሆኑን ከቢቢሲ አፍሪካ ጋር ባደረገው ቆይታ ተናግሯል።

“የእኔ ትውልድ የሥነ ልቦና ማገገሚያ ሕክምና (ቴራፒ) እንደሚያስፈልገው በጽኑ አምናለሁ” ብሏል ድምጻዊ፣ ሙዚቃ ፀሐፊና የድምጽ ኢንጂነሩ ሮፍናን።

ኢትዮጵያ ሁለት ዓመት ሊሞላው በተቃረበው በፌደራል መንግሥትና በትግራይ ኃይሎች መካከል በተነሳው የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ትገኛለች።

“እዚያ ካሉ ጓደኞቼና ቤተሰቦቼ ጋር ማውራት አለመቻል ከባድ ድብታ ውስጥ ይከታል” ብሏል።

ሮፍናን ከዓለም አቀፉ ዩኒቨርሳል ሚውዚክ ጋር በመፈረም የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ነው።

ከሰሞኑ ስድስት የተሰኘውን ሁለተኛ አልበሙን ለቋል።

ሮፍናን አዲስ አበባ በሚገኙ ክለቦች ገናና ስም ማትረፍ የጀመረው በ16 ዓመቱ ነው።

ኤሌክትሮ ሙዚቃን ከባህላዊ መሣሪያና ዜማ ጋር በማጣመር ይታወቃል።

ስድስት ባገኘው ተቀባይነት ደስተኛ እንደሆነ ለቢቢሲ ተናግሯል።

“በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች አለ። በጣም ዕድለኛ ነኝ። በዚህ አልበም እጅግ በጣም ነው የደከምኩት። እያገኘን ያለነው ምላሽ አስገራሚ ነው” ብሏል።

የመጀመሪያ ሚክስ ቴፑን ያወጣው በ16 ዓመቱ ነው። በአዲስ አበባ ክለቦች ዕውቅና ያገኘውም በዚህ አልበም ነበር።

“ጊታር መጫወት የጀመርኩት በ17 ዓመቴ ገደማ ነው። ግን የምሠራው ሙዚቃ ላይቭ [በቀጥታ አድማጮች በተሰበሰቡበት] መጫወት የምችለው እንዳልሆነ ተረዳሁ። ያኔ ሰዎች ዲጄዎችን እንደ ሙዚቀኛ አያይዋቸውም ነበር።”

ጊዜው እየገፋ ሲሄድ ግን ዲጄዎች የራሳቸው መሰናዶ ሲያዘጋጁና ሙዚቃ ሲሠሩ ተመለከተ።

ዲጄዎች አዲሶቹ ሙዚቀኞች እንደሆኑም ተገነዘበ።

“አሁን በአንድ ሙዚቃ ፒያኖ ወይም ጊታር በመጫወት እንሳተፋለን” ብሏል።

ሮፍናን ሙዚቃውን በክለብ እያጫወተና በራድዮ እየሠራ ለሦስት ዓመታት ቆየ።

“በአገሪቱ ካሉ መሰናዶዎች ትልቁ የእኔ ነበር። ከዚያ ነው [ሙያዬን] ያሳደግኩት።”

ሙዚቃ የመሥራት ፍላጎት ያደረበት ገና ልጅ ሳለ ነበር።

“በ10 ዓመቴ አካባቢ እናቴን ድምጿን እቀዳ ነበር። ለእናቴ ካለኝ ፍቅርና ሁሌ አብሬያት ለመሆን ከመፈለጌ የተነሳ ነው።”

ያ የቤተሰብ ፍቅር በአዲሱ አልበሙም ተንጸባርቋል። በተለይም “ወገሕታ” በተባለውና ለእናቱ በጻፈው ሙዚቃ ላይ።

“እናቴ ባትኖር ኖሮ ሙዚቃ ውስጥ ከነጭራሹ አልኖርም ነበር” ብሏል ሮፍናን ለቢቢሲ አፍሪካ።