"የሥነ ጽሑፍ ሥራዎቼ የፈውሴ ምንጭ ናቸው" ትዕግሥት ሳሙኤል

ደራሲ ትዕግሥት ሳሙኤል

የፎቶው ባለመብት, Tigest

ትዕግሥት ሳሙኤል በ2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ለንባብ የበቃ ‘A walk to be cherished’ የተሰኘ የግጥም መድብል አላት። አሁን ደግሞ ‘The chronicles of the unseen and other stories’ የተሰኘ የአጫጭር ልብ ወለድ እና የግጥም ስብስቦችን የያዘ መጽሐፍ ለንባብ አብቅታለች።

ደራሲ ትዕግሥት ወደ ድርሰቱ ዓለም ከመግባቷ በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ ያነበበችው የአያቷን የግጥም እና የቴአትር ሥራዎችን ነው።

አያቷ ደግሞ ከ20 በላይ የሙሉ ጊዜ እና ከ15 በላይ አጫጭር ተውኔቶችን የጻፉት ሁለገብ ከያኒው አቶ ማቴዎስ በቀለ ናቸው።

ትዕግሥት ከአያቷ በመቀጠል ከባሕር ማዶም ከአገር ውስጥ የልብ ወለድ ደራሲዎች ጋር ተዋወቀች።

በቅርብ ጊዜ ለንባብ የበቃው የትዕግሥት መጽሐፍ በዋናነት 6 ልብወለድ ታሪኮችን የያዘ የአጫጭር ታሪኮች ስብስብ ሲሆን፣ የመጽሐፉ መጨረሻ ገፆች ላይ እንደ ጉርሻ የገቡ ግጥሞችን አካትቷል።

ከኢትዮጵያ ከወጣች 25 ዓመት የሆናት ትዕግሥት የምትኖረው ኔዘርላንድስ ነው። ቢቢሲ የአጭር ልብ ወለድ ታሪኮች ስለያዘው መጽሐፏ የተወሰኑ ጥያቄዎችን ጠይቋታል።

ቢቢሲ- በስድስቱ አጫጭር ታሪኮች/ልብወለዶች ውስጥ ታዳጊ ሴቶች ናቸው በዋና ገጸባህሪነት ጎልተው የወጡት፤ ይህንን ለምን አደረግሽ?

ትዕግሥት- ይህቺ በሁሉም ታሪክ ላይ ተደጋግማ የምትመጣው ሴት ታዳጊ፣ ብዙ ጓደኞቼን የምትወክል ደፋር እና ቆራጥ ናት። አስተዳደጌ ይህቺን የመሰሉ ሴት ታዳጊዎችን ወደ ብርሃን እንዳመጣቸው ገፋፍቶኛል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

እናቷ ራሷን በመግደሏ፣ የእናትነት ሚና ተክታ የአምስት ዓመት ታናሽ እህቷን ታሳድግ የነበረች የአስራ አንድ ዓመት ልጅ አውቅ ነበር። መተዳደርሪያዋም ሽንኩርት በመቸርቸር ነበር። እንደዚህች ያለች ጓደኛ ስትኖርህ የእርሷ ሕይወት ብቻ ሳይሆን የሚቀየረው፣ በእሷ ስቃይና ተግዳሮት ውስጥ ጠቅላላ አብረናት ያለነው የእኩዮቿ ሕይወትም ይቀረፃል።

ነፍስ ካወኩበት ጊዜ ጀምሮ ሰፈሬ ውስጥ በወዳጅነት የተቆራኘኋቸው የእድሜ እኩዮቼ በብዛት ይሄዱበት የነበረው የሕይወት ጉዞ በጣም ከባድ እና ለከፍተኛ የሕይወት ቀውስ የሚዳርግ ነበር።

ጓደኞቼ በብዛት የሙት ልጆች፣ ዘመድ ተጠግተው የሚኖሩ፣ ከአንድ ወላጅ ጋር ብቻ የሚኖሩ፣ እናታቸው በምሬት ራሷን ያጠፋች፣ ከሰካራም አባት ጋር የሚኖሩ፣ በሽተኛ ወላጅ የሚያስታምሙ፣ በቂ የገቢ ምንጭ ባለመኖሩ በቀን አንዴ ለመመገብ የተገደዱ እና በእንጀራ እናት እና አባት እጅ የሚጎሳቆሉ ነበሩ።

በብዛት በእንደዚህ አይነት ቤተሰብ ውስጥ የሴቷ ትከሻ ላይ ብዙ ሸክም አለ። በእድሜ ትንሽ ብትሆንም ወላጅ የወላጅነቱን ሚና እና ግዴታ መወጣት ባልቻለ ቁጥር ታዳጊዋ ሴት ላይ ብዙ ጫና ይበረታባታል። ይህም ለብዙ አደጋ ተጋላጭ ያደርጋታል። የሚንከባከባት፤ ለእሷ የሚቆም ጠበቃ ባለመኖሩ በአፍላ ልጅነቷ ያለ አቅሟ ቆራጥ እንድትሆን ትገደዳለች።

ለዚህም ይመስለኛል ይህቺ ተደጋግማ የምትመጣው ታዳጊ ገፀ ባህሪ የተረሳች፣ የተጣለች እና የተተወች ብትሆንም፣ ያ ደግሞ ጊዜዋን ሕብረተሰቡን በጥሞና እንድታጤነው ዕድል ሰጥቷታል። ስለዚህ እነዚህ ታሪኮች ላይ የልጅቷ ብሩህና አስተዋይ መሆን እንዲሁም በሁሉም ጽሑፎቼ ውስጥ ጎልታ መታየቷ የረሳትን ማኅበረሰብ ለመገሰጽ ዕድሉን እንድታገኝ ብዬ ነው።

ቢቢሲ- ሁሉም ታዳጊዎች የሚኖሩበትን ማኅበረሰብ፣ ቤተሰብ የሚያስተውሉ፣ የሚታዘቡ፣ የሚተቹ ናቸው። ከእድሜያቸው በላይ የበሰሉ ሆነው ያገኘኋቸው አሉ። አንቺ በልጅነትሽ እንደዚያ ዓይነት ልጅ ነበርሽ? ወይስ ምናብሽ ውስጥ ያለችው ሴት ማኅበረሰቡን የምታየው በዚያ መነጽር ነው?

ትዕግሥት- እነዚህ ታሪኮች ላይ ጎላ ብለው ከሚታዩት ታዳጊ ሴቶች መካከል በዋነኛነት እኔነቴ ይታይበታል። እንደ ጓደኞቼ የኢኮኖሚ ችግር፣ ረሃብ ወይም የከፋ የሕይወት ጫና ገጥሞኝ ባያውቅም፣ በጣም ቀረብ ብዬ ማኅበረሰባችንን እንዳስተዉል እና እንድታዘብ ያስገደደኝ መረሳቴ ነበር።

መረሳት ወይም ከሰው አለመቆጠር ራሱን የቻለ የሥነ ልቦና ችግር አለው። የመጨረሻ ልጅ ስለነበርኩ ከመረሳት በላይ ደግሞ እናቅ ነበር። ተንቀህ የማውራት ዕድልህን ሲነፍጉህ ሳትወድ በግድህ አዳማጭ ትሆናለህ። በዚህ ምክንያት በልጅነቴ ከእድሜዬ በላይ በጣም ብስል ነበርኩ።

የሰፈሬም ልጆች አኗኗር በእርግጠኛነት ቀርጾኛል። አእምሮዬ ላይ አሻራ ጥሎ ያለፈው ተሞክሯቸው እድሜዬ ከሚችለዉ በላይ ሸክም ጥሎብኝ ነበር። ይህንን ሸክም የሚያቀል የቤተሰብ እርዳታ ስላልነበረ የገጠመኝን የህሊና ቀውስ በመፈላሰፍ በውስጤ አብላላው ነበር።

ሰካራም አባቱ በድንጋይ ፈንክቶት አንድ አይኑ የታወረዉ ጓደኛህ፣ አባቱ ዲያቆን እንደሆነ ሲነግርህ በግዴታ ስለ ፍቅር፣ ስለ አመጽ እና ስለ እግዚአብሄር ትፈላሰፋለህ።

ቤታችን ደጋግሞ እንግድነት የሚመጣ አንድ ቄንጠኛ ጴንጤ ነበር። ምን ይሸጥ እንደነበር ትዝ ባይለኝም ነጋዴ ነበር። እንደእነዚህ አይነት ደጋግመው የሚመጡ እንግዶች ቤተሰብህ እንደ ሰው እንደማይቆጥርህ ካወቁ፣ እነሱም ኢየሱስን ተመርኩዘው ጭንህን በመነካካት ለሰብእናህ ያላቸውን ንቀት ያሳዩሃል።

'ሰላማችሁ ይብዛ' እያለ ሰላሜን ሊሰርቅ የነበረውን ይህን ቄንጠኛ የኢየሱስ ልጅ ነኝ ባዩን በብልሃት አመለጥኩት። ነገር ግን 'እወዳለሁ ንፃ' ብሎ ለምፃም የፈወሰው ኢየሱስ ከዚህ ተልካሻ ጋር እንዴት ተቆራኘ የሚለዉ ጥያቄ ማኅበረሰቡ ሊመልስለኝ አልቻለም ነበር።

ስለዚህ እንደዚህ የመሳሰሉ ጽድቅን እና ሳጥናኤልን እያደበላለቁ ግራ ያጋቡኝን ግለሰቦች፣ ለፍልስፍና እጠቀምባቸው ነበር። ታድያ ይህ ባህሪዬ በስሎ ለመጽሐፍ የሚበቁ ትዝብቶችን ይዞ መጣ።

የደራሲ ትዕግሥት ሁለት መጽሐፍት

የፎቶው ባለመብት, Tigest

ቢቢሲ- በገጸባህሪነት የመጡት ሴቶች በአጠቃላይ ማለት ይቻላል ከዝቅተኛው እና ከመካከለኛ ገቢ ካላቸው ቤተሰቦች ናቸው። አብረው ማኅበራዊ ሕይወትን የሚጋሩ፣ ከሳይንስ ይልቅ ልማድ እና ባሕል ያሰራቸው፣ ለመፍትሔ የማኅበረሰቡን የኖረ ልማድ የሚማጸኑ ናቸው። ይህንን ያደረግሽው ለምንድን ነው?

ትዕግሥት- ይህን ያደረኩበት ምክንያት ፈልጌ ሳይሆን፣ ያስገደደኝ የልጅነት እውነተኛው ትውስታዬ ነዉ። መጽሐፉ ላይ ያነብካቸው ታሪኮች ሙሉ በሙሉ የፈጠራ ሥራ ናቸዉ። ገጸ ባህሪያቶቹም የተገነቡት በፈጠራ ነው።

ነገር ግን ሁሉንም ታሪኮች የጻፍኩት አስተዳደጌ ላይ የገጠሙኝን እውነታዎች ተመርኩዤ ነው። ማኅበረሰባችን ብዙ የሚወደዱ ነገሮች አሉት። አብሮ መብላት መጠጣቱ፣ አብሮ ማዘን መደሰቱ፣ እርስ በእርስ መደጋገፉ፣ በተለይ ችግሮችን አብሮ የመፍታት መንፈሱ በጣም የሚደነቅ ነው።

. . . በተለይ እንደእኔ መርካቶ እምብርት ውስጥ ስታድግ የምትታዘበው ነገር ሰዎች ለችግሮቻቸው መፍትሄ የሚፈልጉበት መንገድ ባላቸው የኢኮኖሚ ይዘት መጠን ነው።

ሌላው ነገር ያደኩበት ማኅበረሰብ እጅግ በጣም ሃይማኖተኛ የበዛበት ነበር። በተለይ እዚያ መርካቶ ውስጥ በጣም በብዛት ጎልቶ የሚታየዉ ተከባብሮ የሚኖረዉ የእስልምና እና የኦርቶዶክስ እምነት ነበር።

የብዙ ችግር ምንጭ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው ተብሎ ስለሚታመን መፍትሄውም ከሳይንስ ይልቅ በእግዚአብሔር ትከሻ ላይ የተጣለ ነበር።

. . . እንዲህ አይነት ክስተቶች ማኅበረሰቡ በዚያን ወቅት ለሳይንሳዊ ትንተና ጊዜም አቅምም እንዳልነበረዉ ያሳያል። . . .

ቢቢሲ- (The patriot) ኩሩው ባላገር (በእኔ ትርጉም) ላይ የምናየው ክርክር፣ ኩሩ ኢትዮጵያዊ ሆኖ የሚሞግተው እና በኋላ በዝሙት ሲወድቅ የምናየው ገጸባህሪ ላይ የሚነሱ ክርክሮች ኢትዮጵያዊነታችንን ቅኝ ባለመገዛት ብቻ እንዳንለካው፣ እርስ በእርስ ጦርነቱን እንዲሁም ለሌሎች ያለንን አመለካከት፣ ‘ባርያው’ በሚለው ጥሪ ውስጥ መፈተሽ እንደሚገባን ገጸባህሪይዋ ስትናገር እናስተውላለን። እዚህ ውስጥ አንቺ እንደ ደራሲ ዋና ማለት የፈለግሽው ነገር ምንድን ነው?

ትዕግሥት- The patriot የሚለው ቃል በቃል ሲተረጎም አንተ ያልከው ትርጉም በደንብ ያስኬዳል። እኔ ግን The Patriot የሚለዉን ርዕስ ምን ለማለት ፈልገሽ ነዉ ብባል 'አጉል አገር ወዳድ' ወይም 'አገር ወዳድ ነኝ ባይ' ብዬ ነዉ የምተረጉመው። . . . ኢትዮጵያ ጣልያንን አሸንፋ በቅኝ አለመገዛቷ በጣም የሚያስደንቅ ድል ነው። በዚህ ጉዳይ የኢትዮጵያ ሕዝብ መኩራቱ በጣም ምክንያታዊ ነው ብዬ አምናለሁ።

ነገር ግን በአስተዳደጌ ላይ የገጠሙኝ እንዲሁም አሁን ባለሁበት እድሜም ላይ የታዘብኳቸው አጉል አገር ወዳድ ነን ባዮች ኢትዮጵያዊነትን የሚያዩበት መነጽር በጣም የተጋነነ ነው። በመጀመሪያ ደረጃ አገር ወዳድ ነኝ የሚል ሰው ስለ ኢትዮጵያ ሉዓላዊነት፣ ስለ ኢትዮጵያ ውበት፣ ስለ ኢትዮጵያ የባህል እና ስለሌሎችም ነገሮች አዎንታዊ ስሜት በተሞላበት ሚዛናዊ በሆነ ሁኔታ መወያየቱ መጪውን ትዉልድ ስለ ሀገሩ ያለውን ግንዛቤ እንዲያዳብር ይረዳዋል።

ይህንን ግን ሌላውን አገር በማደብዘዝ፣ የሌላ በማናናቅ እና በማሳነስ እናም ከእኔ አገር በላይ ፃድቅ አገር የለም በማለት ኢትዮጵያዊነትን ለአዲሱ ትውልድ ማስተዋወቅ በጣም ያሳፍራል።

. . . አንዳንድ አገር ወዳድ ነን ባዮች ስለኢትዮጵያ የተፈጥሮ ውበት ከልክ ባለፈ መጠን ሲያጋንኑ ሌላ አገር እንኳን ተራራ ሊኖር ሳርም የሚበቅል አይመስልህም። ነገር ግን ከሁሉም አገር ወዳድ ነኝ ባይ በጣም የሚያበሳጨኝ እንደ ክፍሌ አይነቱ ገፀባሀሪ አስመሳይ ነው። የገዛ ያገሩን ልጅ ጥቁር በመሆኑ 'ባርያ' ብሎ እየጠራ ስለኢትዮጵያ ቅኝ አለመገዛት ልብን መንፋት አስቂኝ ነው።

ደራሲ ትዕግሥት ከሳለቻቸው ስዕሎች መካከል አንዱ

የፎቶው ባለመብት, Tigest

ቢቢሲ- የኖረውን ባሕል ለማስታወስ ደጋግመሽ በየልቦለዶቹ የምታመጪያቸው ነገሮች እንዳሉ ሆነው፣ አስለቃሿ የሚለው ልብ ወለድ ሙሉ በሙሉ ያንን የቀደመ እና አሁን የቀረ ባህል ለማስታወስ የተጻፈ ይመስላል። ልክ ነኝ?

ትዕግሥት- በጣም ልክ ነህ። ከስድስቱ ታሪኮች 'አስለቃሿ' የሚለው ልብ ወለድ ከሌሎቹ ለየት ባለ መልኩ ከእውነተኛ ታሪኬ ጋር በጣም የተቀራረበ ነው። ስለዚህ እዚህ ታሪክ ላይ ያለችው ተራኪ እኔው ነኝ። ገፀባህሪያቶቹ ስማቸው ተቀያይሮ እና ብዙ ቅመማ ቅመሞች ገብቶበተ የተሸከፈ ልብ ወለድ ቢሆንም እውነታው ግን የወንድሜ ሞት ሐዘን ጥልቅ እንደነበረ ማሳያ ነው። አስለቃሿ ጥላብኝ ያለፈችው ነገር ለትውስታ በጽሁፍ እንዲቀመጥ ብዬ በማሰብ እዚህ አጫጭር የልብወለድ ሥራዎቼ ውስጥ አካትቼዋለሁ።

እዚህ ታሪክ ላይ የአስለቃሽ ሙያ ተመልሶ ይምጣ እያልኩ ሳይሆን አስለቃሽዋን ከባህሉ ነጥለን በቃላት አገላለጽ የተካነች አርቲስት ሆና እንድናያት ፈልጌ ነው። ሰውን ለማሳመን የምትጠቀምበት ጥበብዋ በጣም ረቂቅ ከመሆኑ የተነሳ ሀዘንን ከማቀጣጠል በላይ ሕይወት ላይ ያላትን ፍልስፍናም ያሳያል።

ለምሳሌ፣

ክምር ከማሪና እግዜር አንድ ናቸው፣

መልሰው ሊያፈርሱት ምነው መድከማቸው

ብላ ስታስለቅስ የእግዚአብሔር እና የአንድ የተራ ክምር ከማሪ ኃይል እንዴት አንድ ዓይነት ሊሆን ቻለ ብላ እየጠየቀች ነው። ይህ ደግሞ መልስ የሚያስፈልገዉ ጥልቅ ጥያቄ ነው። እግዚአብሔር ሕይወትን ከፈጠረ ለምን ሞትን አብሮ ፈጠረ እያለች ነው። በጥሞና ለሚያዳምጣት የሕይወትን ከንቱነት ፍልስፍና እያስተማረች ይመስለኛል።

ብቻ በጣም ስለሳበችኝ መጽሐፌ ውስጥ ለትውስታ አስገብቻታለሁ።

ቢቢሲ- ከአጫጭር ልብ ወለዶች ውጪ ግጥሞችም በዚህ መፍሐፍ ውስጥ ተካተዋል። አንድ ቦታ It was my way of conveying that what is absent in reality can often be found in pictures and poetry. ገጸባህሪዋ ትላለች። ላንቺ ግጥም ምንድን ነው? ልክ ገጸባህሪዋ እንደምትለው በእውነታው ዓለም የሌለ በግጥም እና ሥዕል ውስጥ ይገኛል ብለሽ ነው የምታምኚው?

ትዕግሥት- አዎ በጣም አምናለሁ። . . . ለእኔም ግጥም የነፍስ ማደሻ ሙዚቃ ነው። መደበቂያ እና መሸሺያም ነው። የገሃዱ ዓለም ፍቅር ቢከለክልህ በስንኞችህ የምናብ ዓለም ፈጥረህ በፍቅር የሞላ ውቅያኖስ ውስጥ ራስህን ማጥመቅ ትችላለህ።

ሠዓሊነቴን እንደ ፀሐፊነቴ ባልተማመንበትም ብዙ ጊዜ አብስትራክት ሥዕሎችን ለመሳል እሞክራለሁ። በዚህ ግራጫ ዓለም ውስጥ እየኖርኩ ሥዕሎቼ ግን ብዙ ጊዜ በጣም በቀለማት ያሸበረቁ፣ ተስፋ የሞላባቸው፣ ይህንን ዓለም የማይወክሉ ቦታዎች ናቸው። በይበልጥ ግን ስለ ሥነ ጽሑፍ ስለሆነ የምናወራው ግጥሞቼ ለአንባቢዎች ምን እንደሚያበረክቱ ደፍሬ መናገር ባልችልም ለእኔ ግን የፈውስ ምንጭ ናቸው።

ደራሲ ትዕግሥት ሳሙኤል

የፎቶው ባለመብት, Tigest

ቢቢሲ- መጽሐፉ በእንግሊዝኛ ነው ለአንባቢ የቀረበው። ለዚህ የተለየ ምክንያት አለሽ?

ትዕግሥት -አሁን ከአገሬ ከወጣሁ 25 ዓመት ሞልቶኛል። ኔዘርላንድስ ውስጥ የደች እና የእንግሊዘኛ ቋንቋ እየተናገርኩ ነው የምኖረው። አማርኛ በደንብ እናገራለሁ። አንድ አንድ ግጥሞች እና አጫጭር ልብወለዶችም በአማርኛ ሞክሬአለሁ።

ነገር ግን አማርኛ ከሚናገር ሕብረተሰብ ለ25 ዓመት ተነጥዬ ስኖር ወድጄ ሳይሆን በግድ አማርኛዬ ለዛውን እያጣ ይሄድና አንዳንዴ እንዲያውም ቀና ብሎ መራመድ ስለሚያቅተው እንግሊዝኛን እንደምርኩዝ ካልተደገፍኩ እያለ ያስቸግራል።

ሥነ ጽሑፍ ደሞ ጠለቅ ያለ የቋንቋ ክኅሎትን ይጠይቃል። ስለዚህ መጽሐፍ ለመፃፍ የሚያበቃ የጠለቀ የአማርኛ ብቃት ስሌለኝ ወደ እንግሊዝኛው አዘንብያለሁ።

ቢቢሲ- ወደ አማርኛ ለመመለስ እና ለአማርኛ ተደራሲያን የማቅረብ ሃሳብ አለሽ?

ትዕግሥት- እኔ ከዚህ ወዲህ በአማርኛ መጻፍ በጣም ይከብደኛል። መጽሐፍ ውስጥ ለመጠረዝ የማይበቁ ጽሁፎችን በአማርኛ መጻፍ ብችልም ከዚያ ግን አያልፍም። ድፍረት አይሁንብኝና መጽሐፌ በአማርኛ ተተርጉሞ ለአንባቢያን ቢቀርብ የሚሰማኝን ደስታ በቃላት መግለጽ ያቅተኛል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ተወልጄ አማርኛ በደንብ እየተናገርኩ፣ ነገር ግን በአማርኛ ቋንቋ የመፃፍ ብቃቱ ስለሌለኝ ሥራዬን በአማርኛ ተርጉሙልኝ ማለት በጣም ያሳፍራል። ቢሆንም ፈቃደኛ ሰው ከተገኝ በደስታ አደርገዋለሁ።

ቢቢሲ- ከኢትዮጵያ ደራሲያን አንቺ ላይ ተጽዕኖ ያለው ማን ነው? የየትኛዋ/የትኛው ደራሲ አጻጻፍ ተጽዕኖ አሳርፎብኛል ትያለሽ?

ትዕግሥት- አያቴን ታውቃቸው እንደሆን አላውቅም ግን አቶ ማቴዎስ በቀለ ይባላሉ። በ1941ዓ.ም. ሀገር ፍቅር ቴአትር ቤትን ተቀላቀለው እጅግ ብዙ ግጥሞችን እና ከ30 በላይ ተውኔቶችን የፃፉ እና ያዘጋጁ፣ ተጓዥ የአንድነት ትያትር ቡድን የሚባል ኩባንያን በባለቤትነት መሥርተው ለበርካታ ዓመታት ቴአትርን በሁሉም የሀገራችን ክፍል እየተዘዋወሩ ያሳዩ እና ለቴአትር ጥበብ እድገት ጉልህ ሚና የተጫወቱ የጥበብ ሰው ነበሩ።

የእሳቸውን የድርሰት ሥራዎች ማንበብ የጀመርኩት በጣም በልጅነቴ ነበር። በእጅ ተጽፈው በሥነ ሥርዓት ከተጠረዙት ሥራዎቻቸው መካከል ለመጀመሪያ ጊዜ ከሥነ ጽሁፍ ጥበብ ጋር ያስተዋወቀኝ 'ልጃገረድ አስር ያጭሽ፣ አንድ ያግባሽ' የሚለውን ድርሰታቸውን ካነበብኩ በኋላ ነበር።

ከዚያ ቀስ እያልኩኝ ከወንድሞቼ ጋር እየተወያየን በእጃቸዉ ተጽፎ የተጠረዙ ሥራዎቻቸውን በሙሉ አንብበን ጨረስን። ብዙው የቴአትር ድርሰታቸው በግጥም መልክ ስለተጻፈ ለግጥም ያለኝም ፍቅር ከዚያ የመነጨ ነበር። ቤታችን ውስጥ በእሳቸው ጥበብ ያልተለከፈ ጥቂቱ ብቻ ነው። . . .

ከዚያ በተረፈ እውነቱን ለመናገር ከሌሎች ኢትዮጵያን ደራሲዎች ጋር ጥልቅ ትውውቅ ያደረኩት ከአገሬ ከወጣሁ በኋላ ነው። ባለቤቴ ካስተዋወቀኝ ደራሲዎች በጣም የመሰጡኝ እና እስካሁን ድረስ እየተደሰትኩ የማነባቸው የአዳም ረታ እና የስብሐት ገ/እግዚአብሄር ሥራዎች ናቸው።

ቢቢሲ- የድርሰት ተሰጥኦ አለኝ መጻፍ እችላለሁ ያልሽበትን የመጀመሪያ ጊዜ ታስታውሸዋለሽ?

ትዕግሥት - ግጥም መጻፍ የጀመርኩት በጣም ልጅ እያለሁ ሲሆን የመጀመሪያ አጭር ልብወለድ በእንግሊዘኛ የጻፍኩት ግን አገር ለቅቄ ከወጣሁ በኋላ ነበር። ለመጀመሪያ ጊዜ የድርሰት ተስጥኦ አለኝ ያልኩበት የተለየ ቀን የለኝም።

ግን አንድ የማስታውሰው ገጠመኝ አለኝ።

አንድ የሆነ ልጅ ወድጄ ነበር። የእስልምና እምነት ተከታይ እና በጣም ዐይን አፋር ነበር። እሱም ወዶኝ ነበር ግን እጄን ከመያዝ በላይ ያለፈ የፍቅር መግለጫ ሊሰጠኝ አልቻለም። ለመሳም ጉጉት ስለነበረኝ እሱን ወደእኔ የምስብበትን ዘዴ አሰላሁ።

በወቅቱ ያገኘሁት ብልሃት ከእርሱ ቁርአን ተውሶ ማንበብ የሚል ነበር። በእንግሊዘኛ የተጻፈ ቁርአን አዋሰኝ። እናቴ ቤት ውስጥ ቁርአን ይዤ ስታየኝ ግን ደስተኛ አልሆነችም። . . . ተገረፍኩ። እናም ካመጣሁበት እንድመልሰው ላከችኝ።

በጣም የምወዳት የሰፈር ጓደኛዬጋ ሄጄ . . . 'የቁርአኑ መዘዝ' የሚል አጭር ታሪክ ፃፍኩ።

ጓደኛዬ ቁርአኑን በጋዜጣ ለብዳ ሌላ መጽሐፍ አስመስላልኝ ቤት ይዤ ተመለስኩና ደበቅኩት።

አባቴ ከስራ ሲመጣ ደብቄ የጻፍኩትን አስነበብኩት።

ታሪኩን አንብቦ ሲጨርስ አንቺ ነሽ የጻፍሽዉ ብሎ አድንቆ ሳመኝ።

በኋላ የዚያኑ ቀን ማታ ሁላችንም ቲቪ እያየን እናቴ 'ልጅህ ብላ ብላ ዛሬ ቁርአን ይዛ መጥታ ካላነበብኩ ብላ አስቸግራ ቁርአኑን አስመልሻታለሁ' አለችው። 'ኧረ' ብሎ ፈገግ ብሎ አየኝ እና ተግባባን። ወደ አልጋ ስንሄድ አባቴ ጠራኝና በሹክሹክታ 'ሚሚ ቁርአኑን አንብበሽ ስትጪርሺ የታሪኩን ሁለተኛ ክፍል መፃፍ እንዳትረሺ' አለኝ።

የዚያን ሌሊት የተሰማኝን ደስታ እስካሁን አስታውሰዋለሁ። የአባቴ ጽሑፌን የተቀበለበት መንገድ በጣም አበረታትቶኛል።

ከአገር ከወጣሁ በኋላ በደንብ መጻፍ ስጀምር ጽሑፌ ያለምንም የጎላ ጥረት ራሱ ቦታ ቦታውን እየያዘ ሲፈስ ተስጥኦው እንዳለኝ ተረድቼው ነበር። በብዛት አነባቸዉ የነበሩ ፀሐፊዎች በአጫጭር ልብወለድ አጻጻፍ የተካኑ ስለነበሩ ከእነሱ ብዙ ተምሬያለሁ።

እነ ማክሲም ጎርኪ፣ ፊዮዶር ዶስቶየቭስኪ፣ አንቷን ሼኮቭ፣ ቶልስቶይ፣ ቻርለስ ቡካዉስኪ እና ኒኮላይ ጎግል በደንብ አሰልጥነውኝ ስለነበር ለመጀመርያ ጊዜ የጻፍኩትን አጭር ታሪክ ጽፌ ጨርሼ ሳነበው ለራሴ በጣም አሳቀኝ። የዚያን ጊዜ የተረዳሁት ነገር የምወዳቸው ፀሐፊዎች ገፀባህሪያቸውን የሚገልፁበት የኩምክና አገላለጽ እኔም ላይ እንደተጋባብኝ ነበር።