የጋምቢያ የቀድሞ የደህንነት ኃላፊ የሞት ፍርድ ተፈረደባቸው

በአንድ አክቲቪሰት ላይ ለፈጸሙት ግድያ የሞት ፍርድ ፈርዶባቸዋል

የፎቶው ባለመብት, The Gambia Coalition

የጋምቢያ ፍርድ ቤት የቀድሞው የአገሪቱ የስለላ መስሪያ-ቤት አለቃ ያንኩባ ባድጂ እና ሌሎች አራት የደህንነት አባላት በአምባገነኑ የፕሬዚዳንት ያህያ ጃሜህ የመጨረሻ የስልጣን ቀናት በአንድ ተሟጋች ላይ ለፈጸሙት ግድያ የሞት ፍርድ ፈርዶባቸዋል። ተሟጋቹ ኤብሪማ ሶሎ ሳንዴንግ በአውሮፓውያኑ 2016 የተገደለ ሲሆን የተቃዋሚው የተባበሩት ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ግንባር ቀደም ሰው ነበር።

ከፍተኛ የጸረ-መንግስት ተቃውሞዎችንም ሲመራ ቆይቷል። በእስር ቤት ውስጥ ለሁለት ቀናት ከቆየ በኋላ በደረሰበት ድብደባ ህይወቱ አልፏል። አምባገነኑ ጃሜህ በአውሮፓውያኑ 1994 በወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን ከያዙ በኋላ እአአ 2017 ላይ በምርጫ ከተሸነፉ በኋላ አገር ጥለው ተሰደዋል።

ጃሜህ በሥልጣን ዘመናቸው ተፈጥሯዊ ኃይል እንዳላቸው በተደጋጋሚ ይናገራሉ ነበር። ሰዎችን ከኤችአይቪ የመፈወስ አቅም አለኝ ሲሉ በተደጋጋሚ ተደምጠዋል።

ጃሜህ እአአ 2017 ላይ በምርጫ መሸነፋቸውን ተከትሎ አገር ጥለው ከመሰደዳቸው በፊት አራት አወዛገቢ የነበሩት አገራዊ ምርጫዎችን ማሸነፋቸው ይታወሳል። እአአ 2011 ላይ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቃለ መጠይቅ፤ የሊቢያ መሪው ሞአመር ጋዳፊ እጣ ይደርሰኛል ብለው እንደማይሰጉ ተናግረው፤ "አላህ ካለ የጋምቢያን ሕዝብ አንድ ቢሊዮን ዓመት ልመራ እችላለሁ" ብለው ነበር። የኤብሪማ ሶሎ ሳንዴንግሞት ቀድሞም የገነፈለውን ህዝባዊ ቁጣን በማባባስ በመጨረሻ ከ22 አመታት የስልጣን ቆይታ በኋላ ፕሬዝዳንት ጃሜህ ከስልጣን እንዲወገዱ ምክንያት ሆኖ ከአንድ አመት ባነሰ ግዜ ውስጥ አገር ጥለው እንዲጠፉ ምክንያት ሆኗል።