አሜሪካ የቀድሞ የጋምቢያ መሪ ቅንጡ መኖሪያ ቤትን ወረሰች

ያህያ ጃሜህ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

አሜሪካ በሜሪላንድ ግዛት የሚገኘውን የጋምቢያ የቀድሞ መሪ ያህያ ጃሜህ ቅንጡ መኖሪያ ቤትን መውረሷን የአሜሪካ ፍትሕ ሚኒስቴር አስታውቀ።

ፍትሕ ሚኒስቴሩ የቀድሞ ፕሬዝደንት ያህያ ጃሜህ በሙስና በተገኘ ገንዘብ በአሜሪካዋ ሜሪላንድ ግዛት በ3.5 ሚሊዮን ዶላር ቅንጡ መኖሪያ ቤት መግዛታቸውን ገልጿል።

የአሜሪካ ፍትሕ መሥሪያ ቤት በመግለጫው የቀድሞው የጋምቢያ ፕሬዝደንት መኖሪያ ቤቱን የገዙት በሙስና በተገኘ ገንዘብ እና በሕዝብ ሀብት ነው ብሏል።

ያህያ ጃሜህ መኖሪያ ቤቱን የገዙት ከ10 ዓመታት በፊት በባለቤታቸው ስም በተመዘገበ ድርጅት አማካይነት መሆኑም ተነግሯል።

አሜሪካ ይህን መኖሪያ ቤት መውረሷን የፍትሕ ሚኒስቴር መግለጫ አስታውቋል።

ከዚህ በተጨማሪ ያህያ ጃሜህ ባለቤት ዘይነብ ጃሜህ የተገዛው መኖሪያ ቤት ጥያቄ ከተነሳበት ከእአአ 2020 ጀምሮ ከኪራይ የሰበሰበው ገንዘብ ይነጠቃል።

“ዩናይትድ ስቴትስ ይህን ንብረት ሽጣ ከሽያጩ የሚገኘውን ገንዘብ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በቀድሞ ፕሬዝደንት ጃሜህ ሙስና እና ብልሹ አሠራር ጉዳት ለደረሰባቸው የዘ ጋምቢያ ሕዝቦች ጥቅም ላይ እንዲውል ይመክራል” ይላል የፍትሕ ሚኒስቴር መግለጫ።

የቀድሞ ፕሬዝደንት በሥልጣን ዘመናቸው በጓደኛ እና በዘመድ አዝማድ ስም በውጭ አገራት ባቋቋሟቸው ሚስጢራዊ ኩባንያዎች የአገር ንብረት ማሸሻቸው ይገለጻል።

የዘ ጋምቢያ መንግሥት በዚህ ሳምንት የያህ ጃሜህ በሥልጣን ዘመናቸው “ስፍር ቁጥር ለሌለው ወንጀላቸው” ክስ ለመመስረት ዝግጁ ነኝ ብሎ ነበር።

ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ በስደት ኢኳቶሪያል ጊኒ እየኖሩ የሚገኙት የ57 ዓመቱ ያህያ ጃሜህ ግን ምንም ጥፋት የለብኝም ይላሉ።

ያህያ ጃሜህ እአአ 1994 በወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን ከያዙ በኋላ እአአ 2017 ላይ በምርጫ ከተሸነፉ በኋላ አገር ጥለው ተሰደዋል።

የጃሜህ ቅንጡ መኖሪያ ቤት

የፎቶው ባለመብት, DUGA

ያህያ ጃሜህ ማን ናቸው?

እአአ 1965 ላይ የተወለዱት ጃሜህ ወደ ሥልጣን የመጡት እአአ 1994 ላይ የ29 ዓመት ወጣት ሳሉ ነበር።

ጃሜህ በሥልጣን ዘመናቸው ተፈጥሯዊ ኃይል እንዳላቸው በተደጋጋሚ ይናገራሉ ነበር። ሰዎችን ከኤችአይቪ የመፈወስ አቅም አለኝ ሲሉ በተደጋጋሚ ተደምጠዋል።

 ጃሜህ እአአ 2017 ላይ በምርጫ መሸነፋቸውን ተከትሎ አገር ጥለው ከመሰደዳቸው በፊት አራት አወዛገቢ የነበሩት አገራዊ ምርጫዎችን ማሸነፋቸው ይታወሳል።

 እአአ 2011 ላይ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቃለ መጠይቅ፤ የሊቢያ መሪው ሞአመር ጋዳፊ እጣ ይደርሰኛል ብለው እንደማይሰጉ ተናግረው፤ "አላህ ካለ የጋምቢያን ሕዝብ አንድ ቢሊዮን ዓመት ልመራ እችላለሁ" ብለዋው ነበር።

ጃሜህ የመጀመሪያ ሚስታቸውን ፈተው በተመሳሳይ ጊዜ ሌሎች ሁለት ሴቶችን አግብተው ነበር።

በጃሜህ የሥልጣን ዘመን ቀዳማዊ እመቤት የሚለውን መጠሪያ ያገኘችው ግን ዘይነብ ያህያ ጃሜህ የምትባለዋ ባለቤታቸው ብቻ ነበረች።