በጂቡቲ የስደተኛ መጠለያ ጣቢያ ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያን ፈተና

አብርሃ (ስሙ የተቀየረ) በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተውን የእርስ በእርስ ጦርነትን ሽሽት ሕገ-ወጥ አዘዋዋሪዎች ባበጁት አስቸጋሪ መስመር ተጉዞ ጂቡቲ ከገባ ከአንድ ዓመት በላይ ሆኗል።
ኢትዮጵያ ውስጥ እያለ ራሱን እና ቤተሰቡን በንግድ ሥራ ያስተዳድር የነበረው አብረሃ አሁን በከፍተኛ ስቃይ ውስጥ እንደሚገኝ ይናገራል።
የስደት ሕይወት መራር እንደሚሆን ቢገምትም፣ አሁን ጂቡቲ ውስጥ ባለበት የሆልሆል መጠለያ ካምፕ ውስጥ ያለውን ያህል አስቸጋሪ ይሆናል ብሎ ግን አላሰበም ነበር።
ለአንድ ሰው በአንድ ወር የሚሰጠው ሦስት ኪሎ የስንዴ ዱቄት እና ሁለት ኪሎ ጥሬ ማሽላ እንደሆነም ይናገራል።
በሆልሆል ካምፕ ውስጥ በአሁኑ ወቅት ከ7 ሺህ በላይ ሰዎች ያሉ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥም አንድ ሺህ የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን እንደሚገኙም ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሌሎች የካምፑ ነዋሪዎች ገልጸዋል።
የሚቀርበውን የማሽላ እህል አስፈጭቶ ለመጠቀም የሚያስችል ሁኔታ ባለመኖሩ ፍየል ለሚያረቡ የአካባቢው ነዋሪዎች ሁለቱን ኪሎ በጣም በርካሽ በሆነ ገንዘብ እንደሚሸጡት ስደተኞቹ ይናገራሉ።
በአፍሪካ ቀንድ በቀውስ በተናወጡ አገራት መካከል የምትገኘው ትንሿ ጂቡቲ አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ ያላት ሲሆን 35 ሺህ ስደተኞችን በአራት የስደተኛ መንደሮች ውስጥ ታስተናግዳለች።
አሊ አዴህ ግማሹን ስደተኛ የሚያስተናግድ ሲሆን ሆልሆል 23 በመቶ ስደተኞችን በመያዝ ሁለተኛው ትልቁ የጂቡቲ የስደተኞች ካምፕ ነው። በጂቡቲ ከተማ እንዲሁም ማርካዚ የሚገኙት ሌሎቹ ካምፖች ናቸው።
በሆልሆል ካምፕ የሚገኙት ስደተኞች እንደሚሉት ካለባቸው የመሠረታዊ የአቅርቦት ችግር በተጨማሪ ላለፉት ሦሰት ሳምንታት በጂቡቲ “ካሃምሲን” በመባል የሚጠራው ዓመታዊ ንፋስ በመከሰቱ ለመጠለያ ችግር ተዳርገዋል።
ከባዱ ነፋስ በካምፑውስጥ ያሉ የፕላስቲክ መጠለያዎችን ገነጣጥሎ እያነሳ በርካታ ነዋሪዎችን ያለ መጠለያ ማስቀረቱንም ይናገራሉ።
ንጋት 10 ሰአት ጀምሮ እስከ እኩለ ቀን የሚቆይ ከባድ አቧራ የሚያዝለው ይህ ነፋስ፣ ከፍተኛ አደጋ እንደጋረጠባቸው ስደተኞቹን ይናገራሉ።
ስደተኞቹ በካምፑ ውስጥ ካሉት ዳሶች ከግማሽ በላዩ በነፋሱ መውደማቸውን ብሎም ወደ 12 መጠለያዎች ከጥቅም ውጪ ሆነዋል ሲሉም በምስል በተደረገፈ ማስረጃ ገልጸዋል።
ነፋሱ በዚህ ከቀጠለ በርካታ ነዋሪዎች ያለ መጠለያ ማስቀረቱ እንዳስከፋቸው ይናገራሉ። ይህ የበረሃ ነፋስ እስከ ነሐሴ ወር መጨረሻ ድረስ እንደሚቆይ ትንበያዎች ያሳያሉ።
ነዋሪዎቹ የነፋስ ማዕበሉ መከሰትን ተከትሎ ካምፑን ለሚያስተዳድሩ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ማሳወቃቸውን ብሎም እስካሁን ድረስ ምንም አይነት ምላሽ አለማግኘታቸውን ይናገራሉ።
ቢቢሲ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ድርጅት የአፍሪካ ቀንድ እና የታላላቅ ሐይቆች ቃል አቀባይ የሆኑትን ፌይዝ ካሲናን በጉዳዩ ላይ አነጋገሯል።
በተለይም የምግብ አቅርቦት ላይ ያለው ችግር በዓለም አቀፍ ደረጃ ካጋጠመው የነዳጅ ዋጋ መናር እና ጦርነት ጋር ተያይዞ የተፈጠረው መስተጓጎል ችግር ለስደተኞቹ በቂ ምግብ ለማቅረብ እንዳላስቻለ አመልክተዋል።
“ሌላው ተቋማችን የፈንድ እጥረት አጋጥሞታል። በያዝነው ዓመት በአገሪቱ ውስጥ ላሉት ስደተኞች አገልግሎት ለመስጠት ከሚያስፈልገን ገንዘብ ውስጥ 27 በመቶውን ብቻ ማግኘት የተቻለ ሲሆን፣ አሁንም ለጋሾች በዘላቂነት ድጋፍ እንዲሰጡ ጥሪ እናቀርባለን” ሲሉ ፌይዝ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በሆልሆል የሚገኘው ጤና ጣቢያ ምንም አይነት መድኃኒቶች፣ የላብራቶሪ አገልግሎት ወይም ሐኪሞች የሌሉት እና ከኤችአይቪ ብሎም ከኮሮናቫይረስ ውጪ ያለ ምርመራ የማይሰራ መሆኑን ስደተኞቹ ይናገራሉ።
ከካምፑ 40 ኪሎ ሜትር ራቅ ብሎ ያለ የህክምና ጣቢያ ሪፈር እንደሚላክ እና እዚያ ለመሄድ ግን ትራንስፖርት ባለመኖሩ ስደተኞች ለበርካታ ችግር ተጋልጠናል ይላሉ። ኮማ ውስጥ የገባ ሰው ብቻ የምታጓጉዘው አምቡላንስ በካምፑ ከምትገኝበት ጊዜ የማትገኝበት ይበልጣል ሲሉም ስደተኞቹ ገልጸዋል።
“ይህንን አልፈን ስንሄድም መድኃኒት ከራስችን አውጥተን እንድንገዛ ይጠበቅብናል። ስደተኛውም ገንዘብ ስሌለው ካለመድኃኒት ተመልሶ መጥቶ ይተኛል” ሲል አብርሃ ያስረዳል።
“ከሆልሆል ወደ አቅራቢያው አልሴቤህ የሕዝብ ትራንስፖርት የለም። መሄድ እንደማይቻል እየታወቀ ሪፈር መጻፍ በራሱ ትርጉም አይሰጥም'' ይላል አብረሃ። በቀን አንዴ የምትመጣ የጫት መኪና ወደ ምትገኝበት አቅራቢያ ቦታ በእግራቸው በመጓዝ በመለመን ህክምና ለማግኘት የሚሞክሩ ስደተኞችም አሉ።
ሌላው በቂ ውሃ በካምፑ እንደሌለ እና ያሉት የውሃ ታንከሮች በተለይ ባለፈው አምስት ወር በሦስት ቀን አንዴ እንደሚሞሉ እና እንደሚዘጉ የሚናገሩት ስደተኞቹ፣ የውሃ አቅርቦቱ በቂ ባለመሆኑ የተነሳ በሳምንት አንዴ ብቻ ውሃ የሚደርሰው እንዳለም ይናገራሉ።
በዚህም የተነሳ የተወሰኑ አቅም ያላቸው ሰዎች በእግራቸው ሦስት ሰዓት ያህል በእግር መጓዝ የምንጭ ውሃ እንደሚቀዱ ይናገራሉ። ይህም ለተላላፊ በሽታዎች እየዳረጋቸው እንደሚገኝ ስደተኞቹ ያክላሉ።
ታዲያ እነዚህ ሁሉ ችግሮች እያጋጠሟቸው የሚገኙት በተለይም ከኦሮሚያ እና ከትግራይ ክልል ተሰደው የሚሄዱ ኢትዮጵያውያን ዜጎች፣ በዋናነት በረሃብ ምክንያት ወደ አረብ አገራት ለመሰደድ እንደሚነሱ እና በቅርቡም ወደ የመን የተሰደዱ ሦስት ኢትዮጵያውያን ሕይወታቸው ማለፉን የሟቾቹን ማንነት ከሚያሳይ ማስረጃ ጋር ለቢሲ አሳይተዋል።
የመንግሥታቱ ድርጅት የስደተኞች ተቋም የሚያስፈልገውን አስቸኳይ ድጋፍ ካላገኘ የስደተኞቹን አንገብጋቢ ፍላጎቶች ለማሟላት ችግር እንደሚገጥመው እና ከዓለም የምግብ ፕሮግራም ጋር በመሆን ለጋሾች ገንዘብ እንዲለቁ ጥረት እያደረጉ እንደሚገኝ ፌይዝ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ተጨማሪ፡ ተቐሙ ይሕ ዘገባ ከተጠናቀረ በሗላ በሆልሆል ካምፕ ውስጥ በተለይም ለኢዮጵያዊያን ስደተኛ ቤተሰቦች የመጠለያ ሼዶችን ማከፋፋል መጀመሩን ለቢቢሲ አስታውቐል። ስደተኞች በበኩላቸው የተመድ ስደተኞች ተቐም ልዩ ችግር ላለባቸው እና ቤተሰብ ለሆኑ ስደተኞች መጠለያውን ማከፋፈል መጀመራቸውን ነገር ግን ለሁሉም ስደተኞች መጠለያው እየቀረበ አለመሆኑን ተናግረዋል።












