በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር የተጠረጠሩ 130 ሰዎች አውሮፓ ውስጥ ተያዙ

የፎቶው ባለመብት, AP
አውሮፓ አገራት ጥምር ፖሊስ ኃይል ባደረገው ዘመቻ በሰዎች ሕገ-ወጥ ዝውውር ተሳታፊ ሳይሆኑ አይቀሩም የተባሉ 130 ሰዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉ ተገለጸ።
በዚህ ሰፊ በተባለ ዘመቻ ከ22 አገራት የተወጣጡ 22 ሺህ 500 ሕግ አስከባሪ አካላት ተሳታፊ እንደነበሩ ሮይተርስ የዜና ወኪል የአውሮፓ የፖሊስ ተቋም የሆነውን ዩሮፖልን ጠቅሶ ዘግቧል።
በአውሮፓ ኅብረት የድንበር ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ ፍሮቴክ የተመራው ጥምር የፖሊስ ኃይል ባደረገው ዘመቻ በሰዎች ዝውውር ከተጠረጠሩት በተጨማሪ፣ በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ተጎጂ ሳይሆኑ አይቀሩም የተባሉ ከ100 በላይ ተጎጂዎች መለየታቸውም ገልጿል።
ፖሊስ በተለያዩ አገራት ድንበር ላይ ባደረገው ክትትል በመቶዎች የሚቆጠሩ ሐሰተኛ የጉዞ ሰነዶችን መያዙን ገልጿል።
በዚህ ኦፕሬሽን በርካታ የአውሮፓ አገራት ተሳታፊ የነበሩ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ቦስኒያ እና ሄርዜጎቪና፣ ሞንቴኔግሮ፣ ሰሜን መቄዶንያ፣ ሰርቢያ፣ ዩክሬን እና ብሪታኒያ ተጠቃሽ ናቸው።
በዚህ ኦፕሬሽን 1 ሚሊዮን ሰዎች ምርመራ የተደረገ ሲሆን፤ ከፍተኛ የሰዎች ሕገ-ወጥ የሰው ዝውውር ይካሄድባቸዋል በተባሉ የድንበር አካባቢዎች ላይ በ200 ሺህ ተሸከርካሪዎች ላይ ምርመራም ተደርጓል።
አውሮፓ አፍሪካን ጨምሮ ከተለያዩ አህጉራት ጥቃቶችን በመሸሽ እንዲሁም የተሻለ ሕይወትን ፍለጋ ቁጥራቸው በርካታ ሰዎች የሚሰደዱባት አህጉር ናት።
በየብስና በባሕር በሚደረጉ ሕገ ወጥ ጉዞዎች አማካይነት ወደ ተለያዩ የአውሮፓ አገራት ለመግባት በሚደረገው ጥረት ውስጥ የበርካታ ሰዎች ሕይወት ሲጠፋ ቆይቷል።
እነዚህ ጉዞዎች በአብዛኛው የሚካሄዱት በሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪ ግለሰቦችና ቡድኖች አማካይነት በመሆኑ፣ የአውሮፓ አገራት ትኩረታቸውን በእነሱ ላይ አድርገዋል።
በዚህም በተለያዩ ጊዜያት በአፍሪካ እና በሌሎች አገራት ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችን የአውሮፓ ፖሊስ ከዓለም አቀፉ የፖሊስ ተቋም ኢንተር ፖል ጋር በመሆን ሲያድኑ ቆይተዋል።












