በሩሲያ በእስር ላይ ያለችው አሜሪካዊት የቅርጫት ኳስ ኮከብ ባይደንን ተማፀነች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በሩሲያ በእስር ላይ የምትገኘው አሜሪካዊት የቅርጫት ኳስ ኮከብ ብሪትኒ ግሪነር የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እንዲረዷት በደብዳቤ ተማጸነች።
ብሪትኒ በአደንዛዥ እፅ ክስ ሩሲያ ውስጥ በቁጥጥር ሥር ከዋለች ከአራት ወራት በላይ ተቆጥረዋል።
ብሪትኒ ለባይደን በጻፈችውና ሰኞ ዕለት በደረሳቸው ደብዳቤ ላይ፣ የአሜሪካን ምድር ዳግም ላልረግጥ እችላለሁ የሚለውን ስጋቷን ገልጻለች።
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የፊኒክስ ሜርኩሪ የቅርጫት ኳስ ቡድን ተጫዋች የሆነችውን የብሪትኒንን ደብዳቤ እንዳነበቡት ዋይት ሐውስ አረጋግጧል።
ሰኞ ዕለት የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ቃል አቀባይ፣ ባይደን ብሪትኒ ግሪነርን ጨምሮ በውጭ አገራት ታግተው አሊያም ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ በእስር ላይ የሚገኙ የአሜሪካ ዜጎች መለቀቅ አለባቸው የሚል አቋም አላቸው ሲሉ ተናግረዋል።
የአሜሪካ ባለሥልጣናት በበኩላቸው ያሉትን ሁሉ መንገዶች ተጠቅመው ብሪትኒን ወደ አገሯ ለመመለስ እየሰሩ መሆናቸውን በተደጋጋሚ ገልጸዋል።
ብሪትኒ ለፕሬዝዳንት ባይደን የጻፈችው ደብዳቤ አብዛኛው ክፍል በምስጢር ተጠብቆ የነበረ ቢሆንም፤ አንዳንድ ተቀንጭበው የወጡ ሃሳቦች በእስር ላይ ያለችበትን የአዕምሮ ጤና ሁኔታዋን ያሳያሉ ተብሏል።
“እዚህ በሩሲያ እስር ቤት ተቀምጬ፣ ያለ ባለቤቴ፣ ቤተሰቦቼ፣ ጓደኞቼ ጥበቃ፣ ያለ ኦሊምፒክ ማሊያ እና ያለ ስኬት ብቻዬን ከሃሳቤ ጋር እየተሟገትኩ ነው ያለሁት። እዚህ ለዘላለም ልቆይ እችላለሁ ብዬ ፈርቻለሁ” ስትል ስጋቷን በደብዳቤዋ ላይ አስፍራለች።
“ባለቤቴ፣ ቤተሰቦቼ፣ የቡድን አባሎቼ ናፍቀውኛል። ከዚህ በላይ ደግሞ አሁን ላይ በእኔ ምክንያት እየተሰቃዩ መሆኑን ማወቄ ደግሞ ጭንቀቴን አባብሶታል። እኔን ወደ ቤት ለመመለስ ለምታደርጉት ጥረት ክብር ይሰማኛል” ብላለች ብሪትኒ።
ከዚህም በተጨማሪ ብሪትኒ ለፕሬዝዳንቱ በጻፈችውና በአሜሪካ የነጻነት ቀን መታሰቢያ ዕለት በደረሰው ደብዳቤ ላይ አባቷ በቬትናም የሰጡትን ወታደራዊ አገልግሎት አስታውሳለች።
ፕሬዝዳንት ባይደን በሩሲያ በእስር ላይ የሚገኙ የአሜሪካ ዜጎችን እንዳይረሱም ብሪትኒ ጠይቃለች።
“እባክዎን ሁላችንንም ወደ አገራችን ውሰዱን። ለመጀመሪያ ጊዜ ምርጫ የመረጥኩት በ2020 ነው ። የመረጥኩትም እርስዎን ነው። በእርስዎ እተማመናለሁ” ብላለች።
ብሪትኒ በቁጥጥር ሥር የዋለችው እንደ አውሮፓውያኑ የካቲት 17 በሞስኮ፣ ሽረሜትየቮ አየር ማረፊያ ውስጥ የካናቢስ እጽ ዘይት ሻንጣዋ ውስጥ መገኘቱን ተከትሎ ነበር።
አሁን ላይ የፍርድ ሂደቷን እየተከታተለች ሲሆን ጥፋተኛ ሆና ከተገኘች እስከ አስር ዓመት በሚደርስ እስራት ልትቀጣ ትችላለች።
በሩሲያ ውስጥ በወንጀል ጉዳዮች ከተከሰሱት ውስጥ ከአንድ በመቶ የሚያንሱት ተከሳሾች ነጻ ናቸው።
ሆኖም ነጻ ብትባልም ከአሜሪካ ፍርድ ቤቶች አሰራር በተለየ የሩሲያ መንግሥት ማንኛውንም ውሳኔ በመሻር ወደ እስር ቤት የመላክ ሥልጣን አለው።
ሰኔ ወር ላይ የአሜሪካ ኮንግረንስ አባል የሆኑት ጆን ጋራሜንዲ “ብሪትኒ በአሁኑ ሰዓት በመላው ዓለም እየተካሄደ ባለው የፖለቲካ ጦርነት መጠቀሚያ እንድትሆን አንፈልግም” ብለው ነበር።
ሩሲያ ግን የቅርጫት ኳስ ተጨዋቿ እስር “በአሜሪካ እና በሩሲያ ውጥረት የተነሳ አይደለም” ስትል አስተባብላለች።












