ሩሲያ ያሰረቻትን የቅርጫት ኳስ ተጫዋች አሜሪካ ባለእስረኛ የመለዋወጥ ፍላጎት እንዳላት ተነገረ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሩሲያ ጉዳይዋ በፍርድ ቤት እየታየ የምትገኘውን ታዋቂ አሜሪካዊት የቅርጫት ኳስ ተጫዋችን አሜሪካ ውስጥ በሚገኝ እስረኛ ለመለዋወጥ ፍላጎት እንዳላት ተነገረ።
አደንዛዥ ዕጽ ይዛ ተገኝታለች በሚል ከወራት በፊት ሩሲያ ውስጥ በእስር ላይ የምትገኘውን የቅርጫት ኳስ ተጫዋች ብሪትኒ ግሪነር፣ በሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ተፈርደቦት አሜሪካ ውስጥ በሚገኘው ቪክቶር ባውት የመቀየር ፍላጎት በሩሲያ በኩል እንዳለ ስማቸው ያልተጠቀሰን ባለሥልጣን ጠቅሶ የሩሲያ የዜና ወኪል ዘግቧል።
በቀጠሮ ፍርድ ቤት ቀርባ የነበረችው የቅርጫት ኳስ ተጨዋቿ ተጨማሪ የአንድ ወር የጊዜ ቀጠሮ ተሰጥቶባታል።
የ31 ዓመቷ ብሪትኒ ግሪነር በሩሲያ ከነበራት ጨዋታ በኋላ ወደ አገሯ ስትመለስ ካናቢስ የተባለ ዕጽ ሻንጣ ውስጥ ተግኝቶባታል በሚል ነበር በቁጥጥር ስር የዋለችው።
የአሜሪካ ባለሥልጣናት የስፖርተኛዋ እስር ተገቢ አይደለም፤ መለቀቅ አለባት በማለት ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ ቆይተዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ምርጥ ሴት የቅርጫት ኳስ ተጨዋች ከሚባሉት አንዷ የሆነችው ግሪነር በቀረበባት ክስ ጥፋተኛ ከተባለች እስከ 10 ዓመት የሚደርስ ቅጣት ይጠብቃታል ተብሏል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ተጨዋቿ ከሞስኮ ወጣ ብላ በምትገኝ ከተማ በነበራት ችሎት ላይ የቆንስላ ኃላፊዎች መታደማቸውን እና እርሷንም እንዳነጋገሯት ገልጿል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሩሲያ በእስር ላይ ያለችውን ብሪትኒ ግሪነር አሜሪካ ውስጥ በሚገኝ እስር ቤት ባለ ሩሲያዊ ታሳሪ የመቀየር ፍላጎት እንዳላት ተሰምቷል።
"የሞት ነጋዴው" በሚለው መጠሪያ በስፋት የሚታወቀው ቪክቶር ባውት በሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ነበር የተፈረደበት። ቦውት እንደ አውሮፓውያኑ በ2008 ታይላንድ ውስጥ በቁጥጥር ስር ውሎ ነው ለአሜሪካ ተላልፎ የተሰጠው።
ግለሰቡ በኮሎምቢያ የሚገኙ አማጽያንን በማስታጠቅ የአሜሪካ ዜጎች ላይ ጥቃት እንዲያደርሱ አድርጓል የሚል ክስ ቀርቦበት ነበር እንደ አውሮፓውያኑ በ2012 በኒው ዮርክ ውስጥ የ25 ዓመታት እስር የተፈረደበት።
ባለፈው የካቲት ወር ሩሲያ ውስጥ በተካሄደ የቅርጫት ኳስ ውድድር ላይ ተሳትፋ ወደ አገሯ ልትመለስ ስትል አየር ማረፊያ ውስጥ የተያዘችው አሜሪካዊቷ ግሪነር፣ ይዛው በነበረው ሻንጣዋ ውስጥ ቅባታማ ሃሺሽ በአነፍናፊ ውሻ እንደተለየ በወቅቱ የሩሲያ ባለሥልጣናት ገልጸው ነበር።
ባለሥልጣናቱ የቅርጫት ኳስ ተጨዋቿን መታሰር ያረጋገጡትም ከሳምንታት በኋላ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, AFP












