ሩሲያ ለፊንላንድ የምታቀርበውን የኤሌክትሪክ ኃይል ልታቋርጥ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አርኤኦ ኖርዲክ የተሰኘው የሩሲያ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅራቢ ተቋም ከክፍያ ጋር በተያያዘ ችግር እንደገጠመው በመግለጽ ለፊንላንድ የሚያቀርበውን የኤሌክትሪክ ኃይል ከዛሬ ቅዳሜ ጀምሮ እንደሚያቋርጥ አስታወቀ።
ተቋሙ ከዚህ በፊት ላቀረብኩት አገልገሎት ክፍያ አላገኘሁም ብሏል።
ሆኖም የፊንላንድ የኤሌክትሪክ ኃይል አስተዳዳሪ ተቋም አገሪቱ ከሩሲያ የምታገኘው የኃይል መጠን ድርሻ ዝቅተኛ እና በሌላ አማራጭ ሊተካ የሚችል ነው የሚል ምላሽ ሰጥቷል።
ከቀናት በፊት ፊንላንድ ኔቶን የመቀላቀል ዕቅድ እንዳላት ከገለጸች በኋላ ጎረቤቷ የምዕራባውያኑ የጦር ማኅበር አባል የምትሆን ከሆነ ሩሲያ የበቀል እርምጃ እንደምትወስድ ዝታ ነበር።
ፊንላንድ 1 ሺህ 300 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ድንበርን ከሩሲያ ጋር የምትጋራ ሲሆን ከጎረቤቷ ጋር የሚኖር ጸብን ለማሰቀረት ቀደም ብላ ኔቶን ሳትቀላቀል ቆየታለች።
ሆኖም ሩሲያ ዩክሬንን መውረሯ ፊላንድ ኔቶን እንድትቀላቀል የሕዝብ ድጋፍ አስገኝቶላታል።
ነገ እሁድ ፊንላንድ ኔቶን ለመቀላቀል ያላትን ዕቅድ በይፋ ታሳውቃለች ተብሎ ይጠበቃል።
ታዲያ የሩሲያ ኃይል አቅራቢው ኩባንያ ውሳኔ ከዚህ የፊላንድ ውሳኔ ጋር በግልጽ የተያያዘ አይደለም።
በሩሲያ መንግሥት ቁጥጥር ስር ያለው የኃይል አቅራቢ ተቋሙ ሁኔታው ከዚህ ቀድም አጋጥሞ የማያውቅ እና በሃያ ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ያጋጠመ ነው ብሏል።
ይህ ተቋምም ይሁን የፊንላንድ የኤሌክትሪክ ኃይል አስተዳዳሪ አካል ከክፍያ ጋር የተያያዘ ነው ያሉትን ችግር ምንነት በዝርዝር አላስቀመጡትም።
ባለፈው ወር ከሩሲያ ለሚቀርብላቸው ጋዝ በሩብል አንከፍልም ያሉት ቡልጋሪያ እና ፖላንድ የጋዝ አቅርቦት ተቋርጦባቸዋል። አገራቱ በሩብል መክፈል ሩሲያ ላይ በምዕራባውያን ከተጣለው ማዕቀብ ጋር ይጻረራል የሚል ምክንያት አቅርበዋል።
የሩሲያው የኃይል አቅራቢ ኩባንያ ጋዝፕሮም በፖላንድ በኩል በሚያለፈው የነዳጅ ማስተላለፊያ አማካኝነት የሚያቀርበውን ነዳጅ እንደሚያቋረወጥ በዚህ ሳምንት አሳውቋል።
ፊንላንድ ከሩሲያ የምታገኘው የኃይል አቅርቦት ከጠቅላላው 10 በመቶ እንደሆነ የጠቀሰች ሲሆን ይህ በመቋረጡ የሚፈጠር የኃይል አይኖርም ብላለች።
"ከሩሲያ የምናስገባውን የኤሌክትሪክ ኃይል ከስዊድን የምናገኘውን አቅርቦት በማሳደግ እና በአገር ውስጥ የኃይል ማመንጨት አቅምን በማጎልበት ልንተካው እንችላለን" ሲሉ የፊንላንድ ኤሌክትሪክ ኃይል ከፍተኛ ባለሥልጣን ተናግረዋል።













