ስዊዲን እና ፊንላንድ ለምን ኔቶን ለመቀላቀል ፈለጉ? የሩሲያ ምላሽስ ምን ይሆናል?

በፊንላንድ በሚከናውን ዓለም አቀፍ የጦር ልምምድ ላይ የሚሳተፍ ወታደር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በፊንላንድ በሚካሄድ የጦር ልምምድ ላይ የሚሳተፍ ወታደር

ፊንላንድ እና ስዊዲን በጦርነት ወቅት ከየትኛውም ወገን ጎን ላለመቆም እና ማንኛውንም ወታደራዊ ጥምረት ያለመቀላቀል ዘመናትን ያስቆጠረ ታሪክ ነበራቸው። ይህ ታሪክ ተቀልብሶ አሁን ኔቶን ለመቀላቀል ከጫፍ ደርሰዋል።

ሩሲያ ይህንን ውሳኔ አጥብቃ ተቃውማለች። የምዕራባውያን የጦር ጥምረት የሆነው የኔቶ መስፋፋት ዩክሬንን ለመውረር እንደ ምክንያት አቅርባለች።

ሞስኮ በጎረቤቷ ዩክሬን ላይ የፈጸመችው ወረራ 73 ዓመት ለሞላው ኔቶ ከውልደቱ በኋላ ትልቁን የራስ ምታት ፈጥሮበታል።

ጦርነቱ በምሥራቃዊ የኔቶ ድንበር እየተከናወነ ነው። አባል የሆኑትም ሆኑ ያልሆኑት የሩሲያ ቀጣይ ዒላማ እንሆናለን ሲሉ ስጋት ገብቷቸዋል።

አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ፈረንሳይን ያካተተው ኔቶ ተጨማሪ ጦር ወደ ምሥራቅ አውሮፓ ልኳል።

ሆኖም አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም ጦር ወደ ዩክሬን የመላክ ዕቅድ አለመኖሩን ገልጸዋል።

ኔቶ ማነው?

ኔቶ በሙሉ ጠሪያው የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት ይባላል። እአአ በ1949 አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ፈረንሳይን ጨምሮ በ12 አገራት የተመሰረተ ነው።

ከአባል አገራት አንዳቸው ወታደራዊ ጥቃት ሲደርስባቸው ሌሎች ድጋፍ የሚያደርጉበት ነው።

ሲመሰረት ዓላማው የድኅረ ጦርነት ሩሲያን መስፋፋት ለመከላከል ነበር።

እአአ በ1995 ሶቪየት ሕብረት ደግሞ የራሷን የጦር ጥምረት መሠረተች፤ የምሥራቅ አውሮፓ አገራት ያሉበትን የዋርሶው ስምምነት የተባለውን።

እአአ በ1991 የሶቪየት ሕብረት መፈራረስን ተከትሎ የቀድሞው የዋርሶው ስምምነት አባል አገራት ተገልብጠው የኔቶ አባል ሆኑ። ኔቶ አሁን 30 አባል አገራትን አካቷል።

የኔቶ ምስረታ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የኔቶ ምስረታ

ሩሲያ ከኔቶ እና ከዩክሬን ጋር ምን ጉዳይ አላት?

ዩክሬን የቀድሞ የሶቪየት ሪፐብሊክ አባል አገር ስትሆን የሩሲያ እና የአውሮፓ ሕብረት ድንበርተኛ ናት።

የሩሲያ ዝርያ ያላቸው እና ከሩሲያ ጋር ማኅበራዊ እና ባህላዊ እሴት የሚጋሩ ሰዎች ቁጥርም ከፍተኛ ነው። ክሬምሊን የራሷ አካል እንደሆነችም ታስባለች። በቅርቡ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ዩክሬን የሩሲያ አካል መሆኗን ተናግረዋል።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ዩክሬን ግን ፊቷን ወደ ምዕራባዊያን አዙራለች። ኔቶ እና የአውሮፓ ሕብረትን ለመቀላለቀል ያላትን ዓላማም በሕገ መንግሥቷ ላይ አስፍራለች።

አሁን የኔቶ "አጋር አገር" ናት። ይህ ማለት ዩክሬን በቀጣይ የጥምረቱ አባል አገር እንድትሆን ሊፈቀድላት ይችላል ማለት ነው።

ሩሲያ ደግሞ ይህ እንደማይሳካ ከምዕራባዊያን መተማመኛ ትፈልጋለች።

አሜሪካ እና አጋሮቿ ደግሞ ዩክሬንን ከኔቶ አባልነት የማገድ ዕቅድ ያላቸው አይመስልም። ዩክሬን እንደ አገር በፈለገችው የጦር ጥምረት ውስጥ መሳተፍ ትችላለች የሚል ምክንያት ያቀርባሉ።

ከዚህ ሌላስ ሩሲያ ምን ስጋት አላት?

ፕሬዝዳንት ፑቲን ምዕራባዊያን አገራት ሩሲያን እየከበቡ ነው ይላሉ። ኔቶ በምሥራቅ አውሮፓ ያለውን ወታደራዊ እንቅስቃሴ እንዲያቆም ይፈልጋሉ።

አሜሪካ እአአ በ1990 ወደ ምሥራቅ አውሮፓ ላለመስፋፋት የደረሰችውን ስምምነት ጥሳለችም ይላሉ። አሜሪካ ደግሞ እንደዚህ ዓይነት ቃል አልገባሁም ስትል ትመልሳለች።

ኔቶ በበኩሉ ትንሽ ቁጥር ያላቸው አባል አገራቱ ከሩሲያ ጋር ድንበር እንደሚጋሩ ይገልጻል። ይህንንም ወታደራዊ ጥምረት ነው ሲል ይገልጸዋል።

የሩሲያ ወታደር በክሬሚያ

የፎቶው ባለመብት, Getty

የምስሉ መግለጫ, የሩሲያ ወታደር በክሬሚያ

በሩሲያ እና በዩክሬን ጉዳይ ኔቶ ምን አደረገ?

እአአ በ2014 ዩክሬናዊያን በሩሲያ ይደገፋል የተባለውን ፕሬዝዳንታቸውን ከሥልጣን አስወገዱ። ሩሲያ ደግሞ የዩክሬን ደቡባዊ ግዛት የሆነችውን ክሬሚያን ወደ ራሷ ግዛት አስገባች። በምሥራቅ ዩክሬን ሰፋፊ ቦታዎችን የተቆጣጠሩ እና የሩሲያ ደጋፊ የሆኑ ተገንጣዮችንም ትደግፋለች።

በዚህ ሁኔታ ውስጥ ኔቶ ጣልቃ አልገባም። በምሥራቅ አውሮፓ አገራት ጥምር ጦሩን በማሰማራት ምላሽ ሰጥቷል። ጦሩ በተጠንቀቅ የቆመው ሩሲያ የኔቶ አባል አገርን ከወረረች በሚል ነው።

በኢስቶኒያ፣ በላቲቪያ፣ በሊቱዌንያ እና ፖላንድ ከተለያዩ አገራት የተውጣጡ አራት ባታሊዮኖች አሉት። በሩሜኒያ ደግሞ አንድ ብርጌድ አለው።

በባልቲካ አገራት እና በምሥራቅ አውሮፓ የአየር ላይ የቁጥጥር ሥራው ተስፋፍቷል። ይህም የአባል አገራትን ድንበር የጣሰን የሩሲያ አውሮፕላን ለመቆጣጠር ነው።

ሩሲያ እነዚህ ጦሮች እንዲወጡ ትፈልጋለች።

በአሁኑ ግጭት ኔቶ ምን አደረገ?

የምሥራቅ አውሮፓ አገራትን ድንበር ለማጠናከር አሜሪካ በሺዎች የሚቆጠር ጦር ወደ ፖላንድ አና ሩሜኒያ ልካለች። ሌሎችን ደግሞ በተጠንቀቅ እንዲቆሙ አዛለች፤ ነገር ግን ወደ ዩክሬን ጦር የመላክ ዕቅድ ግን የላትም።

ፀረ-ታንክ እና ፀረ-አውሮፕላን ሚሳኤሎችን ጨምሮ በመቶ ሚሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር መሣሪያ ልካለች። ሌሎች የኔቶ አባል አገራትም አሜሪካ ሠራሽ መሣሪያዎችን ወደ ዩክሬን እንዲልኩ ፈቅዳለች።

ዩናትድ ኪንግደም በበኩሏ ለዩክሬን አጭር ርቀት ተወንጫፊ ፀረ ታንክ ሚሳኤሎችን አስታጥቃለች። ወደ ፖላንድ ተጨማሪ 250 ጦር ልካለች። በኢስቶኒያ ያላትን ጦር ለማጠናከረም 900 ተጨማሪ ወታደሮችን ልካለች።

የቱርክ ጄቶች በፖላንድ ሠማይ ላይ

የፎቶው ባለመብት, Anadolu via Getty

የምስሉ መግለጫ, ኔቶ በምሥራቅ አውሮፓ ያለውን ጦር እያጠናከረ ነው

ተጨማሪ የጦር ጄቶችን ወደ ደቡብ አውሮፓ ስትልክ ከሌሎች አባል አገራት ጋር የባሕር ኃይሏ ምሥራቅ ሜድትራኒያንን እንዲቃኝ አድርጋለች።

የዩክሬንን ወረራ ተከትሎ ሊፈጠር የሚችለው ሰብዓዊ ቀውስን ለመቆጣጠር አንድ ሺህ ወታደሮቿ ዝግጁ ሆነው እንዲጠብቁ አዛለች።

ዴንማርክ፣ ስፔን፣ ፈረንሳይ እና ኔዘርላንድ ተዋጊ ጄቶችን እና የጦር መርከቦችን ወደ ምሥራቅ አውሮፓ እና ምሥራቅ ሜዲትራኒያን ልከዋል።

ስዊዲን እና ፊንላንድ ለምን አሁን ኔቶን መቀላቀል አሰቡ?

የቭላድሚር ፑቲን ውሳኔ በሰሜን አውሮፓ ለዘመናት የዘለቀውን መረጋጋት ንዷል። ስዊዲን እና ፊንላንድ ደግሞ ስጋት ገብቷቸዋል።

የቀድሞው የፊንላንድ ጠቅላይ ሚንስትር አሌክሳንደር ስተብ በበኩላቸው ሩሲያ ዩክሬንን በወረረችበት ቅጽበት ነው አገራቸው ኔቶን የመቀላቀል ውሳኔ "ያለቀለት ጉዳይ" የሆነው ይላሉ።

የስዊዲን የመከላከያ ሚኒስትር ፒተር ሃልቪስት ደግሞ ዕለቱን የሩሲያው መሪ "የማይገመቱ፣ የማይታመኑ እና ደም አፋሳሽ ጦርነት የሚያውጁ መሆናቸውን" ያስመሰከሩበት ሲሉ ገልጸውታል።

ኅዳር ወር ላይ ስዊዲን ኔቶን እንደማትቀላቀል የገለጹ ቢሆንም አሁን ደግሞ ሁለቱ አገራት አባል ከሆኑ የኖርዲክ አገራት የመከላከያ አቋም እንደሚጠናከር እየገለጹ ነው።

ብዙ ስዊዲን እና የፊንላንድ ዜጎች መረጋጋት በሌለው አውሮፓ ውስጥ ኔቶ እንደሚታደጋቸው ተስፋ አድርገዋል።