ሩሲያ ሃሺሽ አዘዋውሯል ባለችው አሜሪካዊ ላይ የ14 ዓመት እስር ፈረደች

በአየር ማረፊያ ውስጥ የማርክ ሻንጣ ሲፈተሽ

የፎቶው ባለመብት, RUSSIAN INTERIOR MINISTRY

የምስሉ መግለጫ, እጾቹ ሻንጣው ውስጥ ሊገኙ የቻሉት እንደ አውሮፓውያኑ 2021 በሞስኮ አየር ማረፊያ በተደረገ ፍተሻ ነው።

የሩሲያ ፍርድ ቤት ከፍተኛ መጠን ያለው ሃሺሽ ሲያዘዋውር ተገኝቷል ባለው የቀድሞ የአሜሪካ ዲፕሎማት ላይ የ14 ዓመት እስር ፈረደ።

ማርክ ፎገል የተባለው ግለሰብ ከዚህ ቀደም ሞስኮ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ውስጥ ይሰራ ነበር።በቁጥጥር ሥር በሚውልበት ጊዜ ግን በዚያው ከተማ በእንግሊዝኛ ቋንቋ መምህርነት ተቀጥሮ እየሠራ ነበር።

ማርክ ፍርዱ የተላለፈበት፣ ከማሪዋና እፅ ጋር በተያያዘ በአሜሪካዊቷ የቅርጫት ኳስ ኮከብ ተጨዋች ብሪትኒ ግሪነር ላይ የቀረበባትን ክስ እየሰማ ባለው ፍርድ ቤት ነው።

ሃሺሽ በአብዛኞቹ የአሜሪካ ግዛቶች ሕጋዊ ቢሆንም በሩሲያ ውስጥ ግን ሕገ ወጥ ነው።

ከዋና ከተማዋ ሞስኮ ወጣ ብሎ ክሂምኪ ውስጥ የሚገኘው ፍርድ ቤቱ ያስተላለፈውን ብይን በተመለከተ ባወጣው መግለጫ “አሜሪካዊ ዜግነት ያለው ማርክ ጥፋተኛ ሆኖ ተገኝቷል” ብሏል።

የእንግሊዝኛ ቋንቋ መምህሩ፣ ከፍተኛ መጠን ያለው እፅ እንዳዘዋወረ እና ከንግድ ዓላማ ውጪ የሆነ ብዛት ያለው እፅ አከማችቶ መገኘቱንም ጨምሮ ገልጿል።

የ60 ዓመቱ ማርክ እንደ አውሮፓውያኑ ነሐሴ 15/2021 በሽረሜትየቮ አየር ማረፊያ በቁጥጥር ሥር ሲውል 17 ግራም የሚመዝን ሃሺሽ ሻንጣው ውስጥ እንደነበረ ለጠበቆቹ ተናግሯል።

የአካባቢው ባለሥልጣናት ግን ማርክ ይዞ የነበረው የእፅ መጠን ምን ያህል እንደነበር አልገለጹም። ሆኖም የሩሲያ ሕግ ‘ከፍተኛ መጠን ያለው’ ማሪዋና ቢያንስ 100 ግራም እንደሆነ ያስቀምጣል።

ማርክ እፁ የአከርካሪ አጥንት ቀዶ ሕክምና ካደረገ በኋላ በሐኪም የታዘዘለት እንደሆነና በሩሲያ የተከለከለ መሆኑን እንደማያውቅ ተናግሯል።

የሩሲያው አንተርፋክስ የዜና ወኪል ማርክ አደንዛዥ እፆችን በማዘዋወር፣ በማከማቸት፣ በማጓጓዝ፣ በማምረትና በማዘጋጀት ጥፋተኛ መባሉንና የእስር ጊዜውን ደኅንነቱ በተጠበቀ እና ከማኅበረሰቡ በተገለለ ሩቅ ሥፍራ እንዲያሳልፍ መወሰኑን ዘግቧል።

በማርክ ላይ የተካሄደውን ምርመራ ተከትሎም ፖሊስ ማርክ ይሰራበት በነበረው አንግሎ አሜሪካን ትምህርት ቤት በመርማሪዎች የተካሄደውን ፍተሻ የሚያሳይ ቪዲዮ አውጥቷል።

የክሂምኪ ፍርድ ቤት በአሜሪካዊው መምህር ላይ ውሳኔ ያሳለፈው በቅርጫት ኳስ ተጨዋቿ ብሪትኒ ጉዳይ ላይ የፍርድ ሂደቱን ካዘገየ ከሁለት ቀናት በኋላ ነው።

የፊኒክስ ሜርኩሪ የቅርጫት ኳስ ቡድን ኮከብ ተጫዋች የሆነችው ብሪትኒ፣ የካናቢስ ዘይት ወደ ሩሲያ ይዛ ገብታለች በሚል ተጠርጥራ በቁጥጥር ሥር የዋለችው ባለፈው የካቲው ወር ላይ ነበር።

በአሁኑ ወቅትም በርካታ አሜሪካውያን በሩሲያ በእስር ላይ ይገኛሉ። ከእነዚህ መካከል በአውሮፓውያኑ 2020 በስለላ ወንጀል የ16 ዓመት እስር የተበየነበት የአሜሪካ የቀድሞ ባሕር ኃይል አባል ፖል ዌላን ይገኝበታል።

ሚያዝያ ላይ ሁለቱ አገራት የቀድሞ የአሜሪካ የባሕር ኃይል አባልን በአሜሪካ ከአውሮፓውያኑ 2010 ጀምሮ በእስር ላይ በሚገኘው ሩሲያዊ አብራሪ ለመለዋወጥ ተስማምተው ነበር።