የዊክሊክስ መስራች ጁሊያን አሳንጄ ለአሜሪካ ተላልፎ ሊሰጥ እንደሚችል ተገለጸ

የዊክሊክስ መስራች ጁሊያን አሳንጄ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የዊክሊክስ መስራች ጁሊያን አሳንጄ ለአሜሪካ ተላልፎ የመሰጠቱ ጉዳይ በዩናይት ኪንግደም የሃገር ውስጥ ሚኒስትር ፕሪቲ ፓቴል ተቀባይነት እንዳገኘ ተገለጸ።

ጁሊያን አሳንጄ ውሳኔውን ይግባኝ ለማለት 14 ቀናት እንዳለውም የዩናይትድ ኪንግደም ሃገር ውስጥ ፅህፈት ቤት አስታውቋል።

ፍርድ ቤቶች ጁሊያን አሳንጄን አሳልፎ የመስጠት ጉዳይ “ከሰብዓዊ መብቱ ጋር የማይጣጣም” መሆኑን ቢገነዘቡም በአሜሪካ ውስጥ “በተገቢው ሁኔታ እንደሚስተናገድ” ማረጋገጣቸውን ገልጿል።

ጁሊያን አሳንጄ በአውሮፓውያኑ 2010 እና 2011 አሹልኮ ባወጣቸው ሰነዶች ምክንያት በአሜሪካ ባለስልጣናት ይፈለጋል።

በዊክሊክስ የታተሙት እነዚህ ሾልከው የወጡት ሰነዶች ከኢራቅና አፍጋኒስታን ጦርነት ጋር የተያያዙ ናቸው ተብሏል።

የአውስትራሊያ ዜግነት ያለው ጁሊያን በለንደን ቤልማርሽ እስር ቤት የሚገኝ ሲሆን ተላልፎ ላለመሰጠትም ከፍተኛ ትግል አድርጓል።

በሃገር ውስጥ ሚኒስቴር የተላለፈውን ውሳኔም በምላሹ ዊክሊክስ ይግባኝ እንደሚል አረጋግጧል።

የጁሊያን ባለቤት ስቴላ በበኩሏ ባለቤቷ “ምንም ስህተት አልሰራም” እንዲሁም “ምንም ወንጀል አልሰራም” ስትል ተናግራለች።

“ጋዜጠኛ እና አሳታሚ ነው እናም ስራውን በመስራት ብቻ ነው እየተቀጣ ያለው” ብላለች።

የሚዲያ ኩባንያው ዊክሊክክስ፣ ማንነታቸው ባልታወቁ የተሰጡ ሚስጥራዊና አወዛጋቢ መረጃዎችን ይፋ በማውጣት ይታወቃል።

በአውሮፓውያኑ 2019 በዩናይትድ ኪንግደም የዋስትና መብትን በመጣስ የእስር ቅጣት የተላለፈበት ሲሆን በወቅቱም የአሜሪካ የፍትህ ዲፓርትመንት በዊክሊክስ የወጡ መረጃዎች ህይወትን አደጋ ላይ የሚጥሉና የስለላ ህጉን ጥሷል በሚል 17 ክሶችን አቅርቧል።

የአሳንጄ የጠበቆች ቡድን በበኩሉ ከኢራቅ እና አፍጋኒስታን ጦርነት ጋር በተገናኘ በዊኪሊክስ የታተሙ ሚስጥራዊ ሰነዶች የአሜሪካን ጥፋት የሚያጋልጡ እና የህዝብን ጥቅም ያስጠበቁ ናቸው ብሏል።