አሜሪካ ሩሲያን በኢ-ሞራላዊነት እና በጭካኔ ከሰሰች

ሀዘንተኞች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር የሩሲያውን ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንን፣ በዩክሬን ወረራ "ጭካኔ በመፈፀም" ወነጀሏቸው።

የመከላከያ ቃል አቀባይ የሆኑት ጆን ኪርቢ ሩሲያ የፈፀመቻቸው ወንጀሎች በምን ዓይነት "የሞራል ሚዛን" ተቀባይነት ሊያገኝ ይችላል? ብለው ሲጠይቁ ስሜታዊነት በግልጽ ተነብቦባቸው ነበር።

አርብ ዕለት የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስክ ከፕሬዝዳንት ፑቲን ጋር በሰላም ዙሪያ ለመነጋገር አሁንም ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ነገር ግን በሩሲያ ጠብ አጫሪነት የተነሳ የሰላም ድርድሩ ቢጀመር እንኳ የመቋረጥ ዕድሉ ሰፊ መሆኑንም አንስተዋል።

ዜሌንስኪ ለፖላንድ ሚዲያ በሰጡት ቃለ መጠይቅ ላይ እንዳሉት ፑቲንን ማግኘት የሚፈልጉበት ምክንያት፣ በሩሲያ "አንድ ግለሰብ ሁሉንም ነገር ስለሚወስን ነው" ሲሉ አስረድተዋል።

ነገር ግን ሩሲያ በኃይል በያዘቻቸው የዩክሬን ግዛቶች ባደረሰችው ውድመት የተነሳ የሚካሄደውን ውይይት ፍሬ አልባ ያደርገዋል ሲሉ ስጋታቸውን አስቀምጠዋል።

"ከቡቻ እና ማሪዮፖል በኋላ ሰዎች ዝም ብለው ሊገድሏቸው ነው የሚፈልጉት። እንዲህ ዓይነት አመለካከት ሲሰፍን ደግሞ ስለምንም ነገር መነጋገር ከባድ ይሆናል።"

ዩክሬን ሐሙስ ዕለት በቡቻ የጦር ወንጀል ፈፅመዋል ያለቻቸውን አስር የሩሲያ ወታደሮች የይፈለጋሉ መግለጫ አውጥታ ነበር።

በቡቻ በሩሲያ ወታደሮች ቢያንስ 400 ሰላማዊ ዜጎች ተገድለዋል።

አርብ ዕለት የአሜሪካ መከላከያ ቃል አቀባይ "የተፈፀመውን ጭካኔ እና ደም ማፋሰስ በቸልታ ማለፍ የምንችል አይመስለኝም" ሲሉ ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንት ፑቲን ዩክሬንን ለመውረር "ሩሲያን እና ዩክሬንን ከናዚዎች ለመከላከል" ሲሉ ያቀረቡትን ምክንያት ያጣጣሉት ቃል አቀባዩ፣ "ይህንን ንግግር ለመቀበል የሚከብደው የሩሲያ ጦር በዩክሬን ሰላማዊ ዜጎች ላይ ያደረሰውን በማየት ብቻ ነው። ከጀርባቸው ተተኩሶባቸው የተገደሉ፣ እጃቸው የፊጥኝ ታስሮ የተገደሉ፣ ነፍሰ ጡር ሴቶች እንዲሁም ሆስፒታል በቦምብ ተደብድቧል" ሲሉ አብራርተዋል።

ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረችበት የካቲት ወር አንስቶ ንጹሃን ዜጎችን በግዴታ በድንበር አካባቢ ከሚገኙ ከተሞች ማስወጣቷን ቢቢሲ አረጋግጧል።

የሩሲያ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ቅዳሜ ዕለት በታተመ አንድ ቃለ ምልልስ ላይ እንደተናገሩት ጦርነቱ ከተጀመረበት የካቲት ወር አንስቶ ከዩክሬን ወደ ራሺያ ከአንድ ሚሊዮን ሰዎች በላይ እንዲወጡ ተደርገዋል።

ላቭሮቭ ለቻይናው ዢንዋ፣ በሩሲያ ከሚደገፉት ግዛቶች ዶኔስክ እና ሉሃንስክ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከመውጣታቸው በተጨማሪ፣ 120 ሺህ የውጪ ዜጎችም እንደሚገኙበት ተናግረዋል።

የዩክሬን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ለቢቢሲ፣ ሞስኮ ምርኮኛ ወታደሮቿን በዩክሬን ንጹሃን ዜጎች ልውውጥ እንዲደረግ ትፈልጋለች ብለዋል።

ይህ ደግሞ በጄኔቫ ስምምነት መሠረት የተከለከለ ነው።

ሩሲያ አርብ ዕለት የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ የዩክሬን ዋና ከተማን እየጎበኙ በነበረበት ወቅት የአየር ድብደባ መፈፀሟን ተናግራለች።

በጥቃቱ የሰላማዊ ዜጎች መኖሪያ ሕንጻ ከተመታ በኋላ አንዲት ጋዜጠኛ መሞቷ ታውቋል።

ሁለት ወር ባለፈው ይህ ጦርነት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ኮንግረስን ለዩክሬን ወታደራዊ፣ ኢኮኖሚ እንዲሁም ሰብአዊ እርዳታ ድጋፍ ማድረግ እንዲያስችላቸው 33 ቢሊየን ዶላር እንዲፈቅድላቸው ጠይቀዋል።