ጉቴሬዝ ጉብኝት እያደረጉ ሳለ የዩክሬን መዲና በሮኬት ተመታች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ እንቶኒዮ ጉቴሬዝ በዩክሬን መዲና ኪዬቭ ጉብኝት እያደረጉ ባለበት ወቅት ሮኬቶች ተተኩሰዋል።
በጉቴሬዝ ጉብኝት ወቅት ወደ ኪዬቭ ማዕከላዊ ሰፈር ሼቭቼንኮ ሁለት ጊዜ ተተኩሷል። ሦስት ሰዎች ተጎድተው ሆስፒታል እንደተወሰዱም የኪዬቭ ከንቲባ ተናግረዋል።
ጉቴሬዝ በጉብኝታቸው ወቅት የገዛ ድርጅታቸውን የጸጥታ ምክር ቤት ወቅሰዋል።
ምክር ቤቱ የዩክሬኑን ጦርነት ማስቆም ተስኖታል ያሉት ጉቴሬዝ "ይሄ በጣም የሚያሳዝንና የሚያስቆጣ ነው" ሲሉ ተመድን ኮንነዋል።
"በግልጽ ልንገራችሁ፣ ተመድ ጦርነቱን ለማስቆም አቅሙን የሚመጥን ጥረት አላደረገም።"
15 አባላት ያሉት የጸጥታው ምክር ቤት ዋና ሥራው የዓለምን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ ነው።
ሆኖም ግን ድርጅቱ ጦርነቱን መግታት ባለመቻሉ በዩክሬን መንግሥትና በሌሎችም አካላት እየተወቀሰ ነው።
ሩሲያ የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ አባላት ከሆኑ 5 አገራት አንዷ ነች። ስለ ጦርነቱ ረቂቅ የውሳኔ ሐሳብ በላይ ቀርቦ ድምጿን ሰጥታለች።
ጉቴሬዝ ትላንት ከዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ጋር የጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
ዘለንስኪ ከዚህ ቀደም ተመድን ሲተቹ ቆይተዋል።
"ክቡር ፕሬዝዳንት ለእርስዎ እና ለዩክሬን ሕዝብ ተመድ ተስፋ እንዳልቆረጠ ላሳውቅ እወዳለሁ" ብለዋል ጉቴሬዝ።
የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት "ተሽመድምዷል" ብለው ጉቴሬዝ ቢተቹም፣ ድርጅታቸው በተለያዩ መንገዶች ድጋፍ እየሰጠ መሆኑን ሳይጠቅሱ አላለፉም።
ተመድ በዩክሬን 1,400 ሠራተኞቹን አሰማርቶ ምግብ እና ገንዘብን ጨምሮ ሌላም ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ጉቴሬዝ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ጉቴሬዝ ዩክሬንን በጎበኙበት ወቅት፣ በሩሲያ የተፈጸሙ "የጦር ወንጀሎችን" መመልከት እንደሚችሉ ዘለነስኪ ተናግረዋል።
ሩሲያ "የዘር ጭፍጨፋ" እየፈጸመች ነው ሲሉም ዘለነስኪ አክለዋል።
ሩሲያ ይህንን ውንጀላ አትቀበለውም።
ቦሮድያንካ በተባለው ከኪዬቭ በስተ ሰሜን ምዕራብ በሚገኘውን ከተማ የተገኙት ጉቴሬዝ፣ የወደሙ ሕንጻዎቸን ተመልክተዋል።
"በ21ኛው ክፍለ ዘመን የማይታሰብ" ጦርነት ሲሉ ጉቴሬዝ ሐዘናቸውን ገልጸዋል።
ሩሲያ በሳምንታት ያወደመቻትን ማሪፖል ከተማ ከጎበኙ በኋላ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን መታደግ እንደሚያስፈልግ ጥሪ አቅርበዋል።
"አብዛኞቹ ሰዎች አረጋውያን ናቸው። መንቀሳቀስ የማይሉም ይገኙበታል። በሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሀን ዜጎችን ማዳን አለብን" ብለዋል።
ሩሲያ፣ አዞቪስታል በተባለው የኢንዱስትሪ መንደር የሚኖሩ ንጹሀን ዜጎች እንዲሁም የዩክሬን ተዋጊዎች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ መንገድ እንድትከፍት በተደጋጋሚ በዩክሬን ብትጠየቅም በእምቢታዋ ጸንታለች።
ጉቴሬዝ በበኩላቸው የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን "በመርህ ደረጃ" ንጹሀን ዜጎች ከከተማዋ እንዲወጡ መፍቀዳቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።












