የመሬት መንቀጥቀጥ ይደርሳል በማለት ቲክቶክ ላይ ያሠራጨው ግለሰብ በፖሊስ ተያዘ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በሚያንማር አዲስ ርዕደ መሬት ሊነሳ ይችላል ብሎ በቲክቶክ ላይ የተናገረው ኮከብ ቆጣሪ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር መዋሉ ተነገረ።
ከባድ የመሬት መንቀጥቀጥ ገጥሟት በነበረው አገር ውጥ የሚገኘው ቲክቶከሩ ኮከብ ቆጣሪ ርዕደ መሬት ይከሰታል ብሎ የሠራው ቪድዮ በርካታ ሰዎችን አስደንግጧል።
ጆን ሞ የተባለው ይህ ግለሰብ ቪድዮውን በቲክቶክ ላይ የለቀቀው በሚያንማር በርዕደ መሬት መለኪያ 7.7 መጠን ያለው የመሬት መንቀጥቀጥ በተከሰተ በሁለተኛው ሳምንቱ ነበር።
ቀደም ሲል በደረሰው የመሬት ነውጥ ከ3,500 በላይ ሰዎች የሞቱ ሲሆን፣ የአገሪቱ ጥንታዊ ቤተ መቅደሶችም ፈራርሰዋል።
"ሐሰተኛ መረጃ በማሠራጨት ሕዝብን በማስደንገጥ" ተከሶ ቲክቶከሩ በቁጥጥር ሥር እንደዋለ የአገሪቱ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ገልጿል።
በግለሰቡ በቲክቶክ ላይ በሚቀጥለው ግንቦት ወር ቀኑን ጠቅሶ ሌላ ርዕደ መሬት "በሁሉም የሚያንማር ከተሞች ይከሰታል" ሲል ነበር ባሐራጨው ቪድዮ ላይ የተናገረው።
የመሬት መንቀጥቀጥን ለመተንበይ በርካታ ከግምት የሚገቡ ነገሮች በመኖራቸው የአደጋውን መከሰት በእርግጠኛነት ለማወቅ እንደማይቻል ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ይህ በሚያንማር ጠመሬት ነውጥ ይከሰታል ብሎ የተነበየው ቲክቶከሩ ያሠራጨው ቪድዮ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተመልካቾችን አግኝቷል።
"ርዕደ መሬቱ ሲነሳ ዋጋ የምትሰጧቸውን እቃዎች ይዛችሁ መሸሽ አለባችሁ። ትልልቅ ሕንጻዎች ውስጥም እንዳትቀመጡ" ሲል ቲክቶከሩ ተከታዮቹን አስጠንቅቋል።
ያንጎን ከተማ የምትኖር ሴት ለፈረንሳይ ዜና ወኪል ኤኤፍፒ እንደተናገረችው ጎረቤቶቿ ቲክቶከሩን አምነውታል። ቤት ውስጥ አንቀመጥም ብለውም በፍርሃት ከቤታቸው ወጥተዋል።
አሁን የግለሰቡ የቲክቶክ ገጹ ቢታገድም፣ ከ300 ሺህ በላይ ተከታዮች የነበሩት ሲሆን፣ በኮከብ ቆጠራ የወደፊቱን እንደሚተብይ ይናገራል።
ግለሰቡ በማዕከላዊ ሚያንማር ሳጋንግ በሚገኘው መኖሪያው በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውሏል።
ማንዳሊ እና ሳጋንግ ከዚህ ቀደም በተነሳው ርዕደ መሬት ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል።
የመሬት መንቀጥቀጡ ከ1,000 ኪሎ ሜትር በላይ በሚገኙ አካባቢዎች ንዝረቱ በመድረሱ እስከ ጎረቤት አገር ታይላድ ድረስ ጉዳት ደርሷል።
በታይላንድ ዋና ከተማዋ ባንግኮክ በመሬት መንቀጥቀጡ ንዝረት ምክንያት ሕንጻዎች ፈራርሰዋል ለብዙዎች ሞት ምክንያትም ሆኗል።












